እንደ ስደተኛ እየኖሩ እንደዜጋ መሞት እስከመቼ?
ሰሎሞን ሹምዬ መኮንን
ቁም ነገር መጽሔት (27 ታህሳስ 2011)
“እትብቴ የተቀበረበት” ይላል ያገሬ ሰው ከመሬት ጋር የለውን ቁርኝነት ሲገልፅ:: እትብት የተቀበረበት መሬት እንግዲህ ሰው የኔ ነው ብሎ የሚገልፀው ነው:: – ቀዬ ነው፤ አገር ነው፤ ማንነት ነው፤ የህልውና መሰረት ነው:: አንዳንዴ የእትብት መቀበር ብቻ በራሱ ለነዚ ሁሉ መገለጫዎች ዋስትና እንዳልሆነ ብናውቅም፡፡ የተነሳሁበትን የነገር አቅጣጫ ላለመሳት፤ ወይንም ወጌን ላለማምቦርቀቅ ወደ ምክንያቶቹ አልገባም:: የዛሬው ጉዳዬ መሬት ነው:: መሬት የግል ይሁን ወይስ የመንግስት? ከሁለቱም እንፃር ለኔ የሚታዩኝን አንዳንድ ነጥቦች ላንሳ::
መሬት የግል ይሁን ብንል ከሚፈጠረው እንጀምር፡፡ መሬት የግል ቢሆን ሰዎች (ባለመሬቶች) የባለቤትነት ስሜታቸው ስለሚጨምር እስከመጨረሻው አቅም አልምተው ለራሳቸውና ለሌሎች (ለአገር) ጥቅም ላይ ስለሚያውሉት የአገር እድገት ይፈጥናል ብዬ አምናለሁ:: ባለሃብቶች ትውልድ የሚሻገር ራዕይ እንዲኖራቸውና እነርሱ የጀመሩትን ስራ በልጆቻቸው አለዛም በልጅ ልጆቻቸው እንዲያልቅ ለመወጠን ይበረታታሉ:: ለምሳሌ አንድ ገበሬ በእጁ ያለውን መሬት ለእርሻ መጠቀም ቢፈልግ እርሻውን ውጤታማና ዘላቂ ለማድረግ ረጅም አመታት የሚፈጁ ጥረቶችንና ኢንቨስትመንቶችን ሊያካሂድ ይችላል:: ለማሳው እርከን መስራት ወይንም ከርቀት የመስኖ ውሃ መሳብ፣ ዙርያ ገብ ደን መትከል፣ አዳዲስና ውድ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ወ.ዘ.ተ.፡፡ ይህን እንግዲህ በአጠቃላዩ ህዝብ መጠን መደመር ነው:: የእያንዳንዱ ዜጋ መበልፀግ የአገሩ ብልፅግና ይሆናል:: እዚህ ላይ የመንግስት ሚና የሚሆነው የሚያስችል ከባቢን በህግና ፖሊሲ ድጋፍ መፍፈጠር ብቻ ይሆናል::
በአገራችን “መሬት የህዝብና የመንግስት ነው” ቢባልም እኛ በተጨባጭ የምናውቀው መሬት የመንግስትና የመንግስት ብቻ ሆኖ ነው:: በውጤቱም ግለሰቦች በእጃቸው ያለን መሬት መቼ እንደሚነጠቁ /ለሰፊው ህዝብ ጥቅምi/ ስለማያውቁ የሩቅ ዘመን ኢንቨስትመንትም ሆነ ትውልድ ተሻጋሪ ራዕይ አይኖራቸውም:: በእጥረት አስተሳሰብ ተገድበው ትኩረታቸውን ቶሎ ውጤት በሚያመጡ ጊዜያዊ ጥረቶችና ኢንቨስትመንቶች ላይ ወስነው ለመኖር ይገደዳሉ::
መሬት የመንግስት ሲሆን የሚያስከትለውን ችግር ለማየት ሩቅ መሄድ አይጠበቅብንም፡፡ አሁን በአገራችን ለተከሰተው የለውጥ ሂደት ዋነኛ መነሻ በአዲስ አበባ ዙርያ የተከሰተው አመፅ እንደነበር እና አመፁም ከመሬት ይዞታ ባለቤትነት ጋር ተያይዞ እንደተቀሰቀሰ የምናስታውሰው ነው:: ከአዲስ አበባ ከተማ መስፋፋት ጋር በተያያዘ የገበሬዎች መፈናቀል እስከ አሁን ተገቢውን ካሳ ያላገኘ በደል እንደሆነ በተለያዩ የፖለቲካ መሪዎችና አክቲቪስቶች ይጠቀሳል:: መንግስት በመኖሪያ ቤትና ልዩ ልዩ የልማት ስራዎች ሳቢያ ከሚያርሱት መሬት የነቀላቸው ገበሬዎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም:: የተሰጣቸው ካሳም ቢሆን ገበያው ሊያስገኝ ከሚችለው ዋጋ ጋር ሲነፃፀር እዚ ግባ የሚባል አይደለም:: ሌላ ቢቀር ራሱ መንግስት ለባለሃብቶች በሚሸጥበት ዋጋ መጠን አለመሆኑ፤ ፍቃዳቸውን ካለመጠየቁ ጋር ተደምሮ በደል እንዲሰማቸው አድርጓል::
ገበሬዎቹ መሬቱ የግላቸው ቢሆንና የመሸጥ የመለወጥ መብት ቢኖራቸው ኖሮ ራሳቸው በገበያ ዋጋ ሸጠው በሌላ የስራ መስክ በመሰማራት ወይም ሌላ ቦታ ሄደው እንደገና ኢንቨስት በማድረግ ተጠቃሚ ይሆኑ ነበር:: ባይጠቀሙም እንኳን መሬቱ ከእጃቸው የወጣው ተገደው ሳይሆን በራሳቸው ፍቃድና ውሳኔ ሸጠውት ስለሚሆን መንግስትን ጨምሮ ሌላ ተወቃሽና ተጠያቂ የሚያደርጉት አካል አይኖርም:: አሁን የምናየው አይነት ቅሬታና አመፅም አይከሰትም ነበር::
መንግስት የትኛውንም በግለሰብ ይዞታ ስር ያለ የከተማም ይሁን የገጠር መሬት ለህዝብ ጥቅም ለማዋል ከማሰቡ በፊት ሌሎች በራሱ ቁጥጥር ስር ያሉ አማራጮችን ማስቀደም አለበት:: አማራጭ ከሌለው ደግሞ ማስገደድ ሳይሆን ከባለ ይዞታው ጋር ቢደራደር የተሻለ ነው:: ምናልባትም ከወቅታዊው የገበያ ዋጋ እስከ እጥፍ በሚደርስ ክፍያ/ማካካሻ በማግባባት:: ከዚህ ሁሉ ጥረት በኋላ እና አማራጭ ሲያጣ ብቻ ነው የባለይዞታውን ጥቅምና መብት ጠብቆ ማስገደድ ያለበት:: አለዚያ ስልጣን ላይ ያሉ አካላት ከፖለቲካ ፍላጎትና ቂም በቀል በመነጨ ምክንያት ዜጎችን በሰበብ አስባብ እንዲያፈናቅሉ የተመቸ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ መሬት የመንግስት ሲሆን ተፅዕኖው ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊም ነው፡፡ የመሬት ይዞታና ተጠቀሚነትን ለዜጎች መፍቀዱን እንደ አንድ መሣሪያ ተጠቅሞ ስልጣን ላይ ለመቆየትና ድምፅ ለመግዛት ሊጠቀምበት እንደሚችል ልብ ይሏል፡፡
መንግስት የመሬት ባለቤት በሆነ ጊዜ በመሬት ላይ የዜጎች ሚና ጭሰኝነት ይሆናል:: የመሬቱን እጣ ፋንታ የሚወስነው “ጉልተኛ” የሚል ስም በይፋ ባይሰጠውም የጉልተኝነት ሚና ያለው መንግስት ነው:: ቀደም ብዬ ባነሳሁት የገበሬ ምሳሌ እንቀጥልና መሬት የግሉ ቢሆን ለሌላ ግለሰብ ሸጦ ወደ ከተማ በመሄድ ለከተማው ተስማሚ በሆነ ሌላ የኢንቨስትመንት ዓይነት ላይ መሰማራት አለዚያም እዚያው ገጠሩ /መሬቱ/ ላይ ባለ ሶስት ኮከብ ይሁን ባለ ሶስት መኝታ ሆቴል መስራት /ቢያዋጣውም ባያዋጣውም/ የራሱና የራሱ ብቻ ውሳኔ ነው:: መሬት የመንግስት በሆነበት እንደ አገራችን ባለ ሁኔታ ግን ይህን አይነት ውሳኔ ላይ መድረስ አስቸጋሪ ነው፡፡
በኢትዮጵያ፣ መንግስት ብቸኛ የመሬት ባለቤት ቢሆንም መሬት ይሸ፡ጣል፤ ይለወጣል፡፡ አምሳ ሺህ ብር የማያወጣ ሁለት ክፍል ያለው የጭቃ ቤት አንድ ሺህ ካሬ መሬት ላይ ሰርቶ በሚሊዮን ብሮች መሸጥ እና ሕጋዊ የስም ዝውውር ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ እንዲያ በናረ ዋጋ የሚሸጠው ቤቱ እንዳልሆነ ሻጭም፣ ገዥም፣ መንግስትም ያውቃሉ፡፡ – ‹ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ› እንዲሉ፡፡ ሻጭም ሆነ ገዢ እንደ ዜጋ ንብረታቸው ሊሆንና በነፃነት ሊሸጡ ወይም ሊለውጡ ይገባቸው የነበረውን መሬት እንደሌባ ተሸማቀው ይፋ ባልሆነ ድርድር በናረ ዋጋ ይገበያያሉ፡፡ -የመሬት ጥቁር ገበያ፡፡ መንግስት ደግሞ ባልወጣ ባልወረደበት የተፈጥሮ ሃብት ተገቢ ያልሆነ ኪራይ ከሁለቱም ይሰበስባል፤ አለዚያም የቤቱን ግምት ብቻ ታሳቢ በማድረግ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም አጥቶ ለሙሰኛ ቢሮክራቶቹ የዘረፋ እድል ያመቻቻል፡፡
ጥቅምና ጉዳቱን ለጊዜው ተወት እናድርግና የመንግስት ይሁን የግል በሚል ለሚነሳ ክርክር ሌላ መሰረታዊ ጥያቄ እናንሳ:: መሬት የግልም ይሁን የመንግስት ስንል እንዴት? የሚሸጥና የሚለውጠውስ ማነው? ጥያቄው የአፈፃፀም ብቻ ሳይሆን የፍሃታዊነትም ነው:: ያ ደግሞ በሁለቱም የይዞታ ሁኔታዎች የእያንዳንዱ ዜጋ /ጐዳና ከሚያድረው እስከ ባለፀጋው/ ድርሻ ምን ይሆናል? ለሚለው ምላሽ መጠየቅ ነው፡፡
መሬት የመንግስት በሆነበት ሁኔታ አቅርቦቱ የሰው ሰራሽ እጥረት ሰለባ ሆኖ ከዓመት ዓመት ዋጋው እየናረ ስለመሄዱ የሌላ አገር ምሳሌ መጥቀስ የሚያስፈልግ አይመስለኝም:: በእጥረት አስተሳሰብ /scarcity mentality/ በየጊዜው እየተቆነጠረ ወደ ገበያ የሚገባው /በተለይ የከተማ/ መሬት፣ ራሱ መንግስት “ኪራይ ሰብሳቢ” ለሚላቸው ባለሃብቶችና ቢሮክራቶች ካልሆነ ለብዙሃን ኢትዮጵያዊያን የእድገትና ብልፅግና መሰረት ሲሆን አልታየም:: በተጋነነ የኪራይ /lease/ ዋጋ መሬቱን በእጃቸው ያስገቡ ጥቂቶችም ቢሆኑ ዘላቂ የመሬት ባለቤትነት መብት የላቸውም:: እርግጠኛ ሆነው ከትውልድ ትውልድ በሚተላለፍ ኢንቨስትመንት ላይ ከመሰማራት ይልቅ በአቋራጭ ወጪያቸውን የሚመልስ እና ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያስገኝ የቢዝነስ ዓይነት ሲመርጡ ይስተዋላል፡፡
አሁን ካለው ሁኔታ ወጣ እንበልና መሬት እንዴት ነው የግል የሚሆነው? ብለን ደግሞ በመላምት እናስብ፡፡ መቼም ለእያንዳንዱ ዜጋ (ለተጣሉ ባልና ሚስት እንደሚካፈል የቀበሌ ቤት) ተሸንሽኖ መዳረስ አለበት የሚል ሃሳብ የለኝም:: ሆኖም መሬት የመግዛት እድሉን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት መስጠት ይቻላል ብዬ አምናለሁ፡፡ ራሱ መንግስትም እንኳን ቢሆን ተቋማቱን ለማስፋፋት እና ትላልቅ ልማቶችን ለማከናወን እንደ ማንኛውም ዜጋ ከባለመሬቶች ተደራድሮና ተወዳድሮ መግዛት አለበት ባይ ነኝ:: ግልፅ ለማድረግ፣ መንግስት በአደራና በሃላፊነት የያዘውን መሬት ለባለቤቱ /ለህዝብ/ በሽያጭ መልክ ለሁሉም ዜጋ እኩል እድል ሰጥቶ መመለስ አለበት:: ከዚያ በኋላ የመሬትን ዕጣ ፋንታ የሚወስነው በዜጐች መካከል የሚካሄድ የገበያ ልውውጥ ይሆናል:: ያን ጊዜ ያለው ተጨማሪ እንዲኖረው፣ የሌለውም የራሱ የሆነ መሬት ለመያዝ ለመወዳደር እና ጠንክሮ ለመስራት ይገደዳል:: ጥብቅ ደኖች፣ በረሃማ አካባቢዎች፣ ፓርኮችና ሌሎችም ሰው ያልደረሰባቸው መሬቶች በመንግስት ይዞታ ስር የሚቆዩ ናቸው፡፡ የከርሰ ምድር ሃብቶችም እንዲሁ /የከርሰ ምድር ሃብቶቹ ተለይተው በሽያጭ ወደ ግል ባለሃብት እስካልተዛወሩ/፡፡
አሁን አሁን አገራችን ኢትዮጵያ በጎሳ ፖለቲካ አራማጅ ምሁራንና ባለስልጣናት መሪነት በብሔር ተሸንሽና ሰፊው ‹ብሔርና ብሔረሰብ› የኔ እና የአንተ ክልል በሚል ደም እየተቃባ ሲያፈናቅልና ሲፈናቀል ማየት የተለመደ ተደጋጋሚ ክስተት እየሆነ ነው፡፡ የሚገርመው ግን ዜጎች የኔ ብለው ደማቸውን የሚያፈሱለት እና የሌሎች ወንድሞቻቸውንም ደም የሚያፈሱበት መሬት የራሳቸው እንዳልሆነ አለመረዳታቸው ነው፡፡ እያንዳንዱን ዜጋ ትርጉም ያለው ተጠቃሚ የሚያደርገው ‹ኦሮሚያ/አማራ/ሶማሌ/ትግራይ … ክልል ከየት እስከየት ነው?› የሚል የወረቀት ይሁን የምድር ካርታና ድምበር ወሰን ሳይሆን በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ የኔ የሚለው እና ሃብት ንብረት ለማፍራት መሠረታዊ የሆነው መሬት ባለቤት መሆን ነው፡፡
በነገራችን ላይ ባለ አገርነት ከሚለካባቸው ጉዳዮች አንዱ “የኔ” የሚሉት መሬት እና መጠለያ /የዜግነት ድርሻ/ መኖር ነው:: በሊዝማ /በኪራይ/ የትም አገር ሄዶ መሬት ማግኘት ይቻላል:: – ዜግነት ሳይኖር:: ለምሳሌ ጎረቤታችን ኬንያ ኢትዮጵያውያን በገዛ አገራችን የሚሰጠንን ከዘጠና ዘጠኝ ዓመት የማይበልጥ የሊዝ መብት የምትሰጠው የኬንያ ዜግነት ለሌላቸው የውጭ አገር ሰዎች ነው፡፡ ሳጠቃልለው በመሬት ጉዳይ መንግስት ባለ አገር /ባለቤት/ ሆኖ እኛ ስደተኞች /ተከራዮች/ መሆን ያለብን አይመስለኝም:: የኔ የምትለው ኩርማን የመሬት ድርሻ ሳይኖርህ ያንተ ተብሎ በተነገረህ የብሔርና የክልል ካርታ ደም መፋሰስ ለፖለቲከኞች የስልጣን መወጣጫና ማረጋጊያ ሰበብ ከመሆን ያለፈ እርባና የለውም፡፡ እንደ ስደተኛ እየኖሩ እንደ ዜጋ መሞት የጋራ ችግራችን ይመስለኛል፡፡ በሰበብ አስባብ ተለያይተን በሌለን ነገር ከመዋጋት መጀመሪያ በጋራ የምንጠቀምባት እና የእኔም የኛም የምትሆን ሃገር ብትኖረን አይሻልም? – ሰላም!
Average Rating