ማለዳ ታይምስ መረጃ ማእከል
የአሜሪካ መንግስት መሪዎቹ ባለመስማማታቸው ምክንያት በከፊል ከተዘጋ አንድ ወር ሊሆነው ነው። በወቅቱ መዘጋቱ የሚያመጣው የጎላ ችግር እንደማይኖር ሲገለጽ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ቀኑ በተራዘመ ቁጥር፣ በከፊል የመዘጋቱ እና ከ400ሺ ያላነሱ የፌዴራል መንግስት ሰራተኞች ከሥራና ከደሞዝ ውጭ መሆናቸው የጎላ ችግር እያመጣ ይገኛል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ፣ ከድንበር አጥር መስሪያ 5 ቢሊዮን ዶላር ካልተሰጠኝ፣ ይለቀቅ በተባለው በጀት አልስማማም በማለታቸው፣ ዲሞክራቶችም ፕሬዚዳንቱ የጠየቁትን ገንዘብ በበጀት ውስጥ አናካትትም በማለታቸው ውጥረቱ አይሎ ይገኛል።
ይህን አስመልክቶ ዛሬ ማምሻውን ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለአሜሪካ ህዝብ የቀጥታ የቴሌቪዥን ንግግር እንደሚያደርጉ ታውቋል። ፕሬዚዳንቱ በዚህ ንግግራቸው የሚያተኩሩት፣ 5 ቢሊዮን ዶላር ለድንበርና ተያያዥ ጉዳዮች የጠየቁት እንዲሁ እንዳልሆነና በደቡቡ የሜክሲኮ – አሜሪካ ድንበር አካባቢ ያለውን የስደተኞች ፍልሰት ስጋት ለማብራራት እንደሆነ ተገምቷል።

ፕሬዚዳንቱ በማታው ንግግራቸው “አገራቸው ትልቅ የስደተኞች ወረራ እንዳጋጠማትና፣ የደቡቡን ድንበሯን በሚገባ ማጠር፣ የኢሚግሬሽን ዳኞችን ማብዛት፣ የማሰሪያ ቦታዎችን መጨመር፣ የ ዕጽ ማስተላለፊያ መንገደችን ማብዛትና መቆጣጠሪያውን ዘመናዊ ማድረግ” በመግለጽ “የጠየኩት 5 ቢሊዮን ዶላር ለዚህ ነውና የአሜሪካ ህዝብ ፍረደኝ” እንደሚሉ ይገመታል።
አያይዘውም “ይህ የማይሆን ከሆነና፣ ዲሞክራቶች ገንዘቡን በጀትን ውስጥ አልለቅም ካሉ፣ ከሌላ የመከላከያ የተለቀቀ በጀት ላይ በመቀነስ የድንበር ግንቡን ለመስራት እንደሚገደዱ” በመግለጽ ለዚህም ደግሞ አስቸኳይ ጊዜ ማወጅ አስፈላጊነቱን ይገልጻሉ ተብሎ ይጠበቃል።
Average Rating