ትክክለኛውን የስዊፍት መክፈያ መልዕክት መለያ ቁጥር፣ የተቀባይን ስምና አድራሻ በማስተካከል፣ ሌሎችንና ራሳቸውንም ለመጥቀም በአቢሲኒያ ባንክ ላይ ከፍተኛ የገንዘብ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው የተከሰሱ አራት ሠራተኞች ጥፋተኛና ነፃ ተባሉ፡፡
የወንጀል ድርጊቱን ፈጽመዋል ተብለው በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩት፣ በኢቢሲኒያ ባንክ አክሲዮን ማኅበር ዓለም አቀፍ የባንኮች ግንኙነት መምርያ የትራንስፈር ሰርቪስና ኮሮስፖንዲንግ ባንኪንግ ኦፊሰር ወ/ሮ ሔለን አሰፋ፣ የትራንስፈር ሰርቪስና ኮሮስፖንዲንግ ኦፊሰር አቶ እሱባለው ሲሳይ፣ የውጭ ባንኮች ግንኙነት መምርያ ውስጥ ሲኒየር ትሬድ ሰርቪስ ኦፊሰር አቶ አለልኝ ጽጌና በአቢሲኒያ ባንክ ዋናው መሥሪያ ቤት የውጭ ባንኮች ግንኙነት መምርያ ውስጥ የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎትና ኮሮስፖንዳንት ባንኪንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ ሰዒድ ናቸው፡፡
ዓቃቤ ሕግ በክሱ እንዳስረዳው፣ ኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ በትክክለኛ የስዊፍት መክፈያ መልዕክት መለያ ቁጥር ለተቀባይ ኔላ ሮዝ ሀርዲ (Nella Rose Hardy)9,001 ዶላር በስዊፍት ክፍያ መልዕክት ቋት ውስጥ ያለን ክፍያ በማስተካከል፣ የሚጠቀሙበት ኮምፒዩተር የስዊፍት ተጠቃሚ ስም (User Name) እና የሚስጥር ኮድ (Password) በመጠቀም የማስተካከል ሥራ መሠራታቸውን አብራርቷል፡፡ የመለያ ቁጥሩን በመቀየር የሚላከውን ገንዘብ መጠን ወደ 190,501 ዶላርና የተቀባይን ስም ወደ ክሪስታል ሞብል ግሎባል በመቀየር ወደ እሱባለው መጠቀሚያ ኮምፒዩተር መቀየራቸውን አክሏል፡፡ ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ እሱባለውም በወ/ሮ ሔለን ኮምፒዩተር የራሳቸውን ስዊፍት የተጠቃሚ ስምና ሚስጥር ኮድ በመጠቀም፣ እንዲፀድቅላቸው ለአቶ አለልኝ መጠቀሚያ መላካቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ አቶ አለልኝም የወ/ሮ ሔለንን ኮምፒዩተርና የራሳቸውን ስዊፍት ተጠቃሚ ስምና ሚስጥር ኮድ በመጠቀም መልዕክቱን በማፅደቅ፣ በስዊፍት መክፈያ ለመላክ ዝግጁ ማድረጋቸውን አብራርቷል፡፡ ተከሳሾቹ ድርጊቱን የፈጸሙት በምሽት መሆኑን ጠቁሞ፣ ስዊፍቱ ጠዋት ላይ ሲገናኝ (ኮኔክት ሲደረግ) 190,501 ዶላር ክፍያ ያላግባብ መላኩንና የክፍያ ማረጋገጫ መምጣቱን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ ተከሳሾቹ የሌላ ድርጅቶች ስዊፍት መክፈያ መልዕክት ላይ ተመሳሳይ ሁኔታ በመጠቀም፣ በአጠቃላይ 558,001 ዶላር ወይም በወቅቱ በነበረው ምንዛሪ 12,903,047 ብር ለራሳቸውና ለሌላ አካል መውሰዳቸውን አስረድቷል፡፡
በባንኩ የውጭ ባንኮች ግንኙነት መምርያ ውስጥ የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎትና ኮሮስፖንዳንት ባንኪንግ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ መሐመድ ሰዒድም የማይገባ ጥቅም ለማግኘትና ለማስገኘት በማሰብ፣ ከላይ በተጠቀሱ የተጭበረበሩ ስዊፍት ክፍያ መልዕክቶች ለተቀባይ ክፍያ ከመፈጸሙ በፊት ክፍያ ለሚፈጽሙት ሲቲ ባንክ ኒዮርክና ኮሜርስ ባንክ ፍራንክፈርት ተወካዮች በኢሜይል ማሳወቅ እየቻሉ አለማድረጋቸውን አስረድቷል፡፡ በመሆኑም የሕዝባዊ ድርጅት ሥራን በማያመች አኳኋን በመምራት የሙስና ወንጀል መፈጸማቸውን አብራርቷል፡፡
ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ ያስረዱልኛል ያላቸውን የሰነድና የሰዎች ማስረጃ አቅርቦ ለፍርድ ቤቱ ያስረዳ መሆኑንም የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይገልጻል፡፡ ወ/ሮ ሔለን፣ አቶ እሱባለውና አቶ አለልኝ የቀረበባቸውን ክስና የቀረበባቸውን ማስረጃ በብቃት ማስተባበል በመቻላቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ነገር ግን አቶ መሐመድ ያቀረቡት ማስረጃ የዓቃቤ ሕግን የሰነድም ሆነ የሰው ማስረጃ ከማጠናከር ባለፈ ማስተባበል ባለመቻላቸው በተከሰሱበት አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 13(1ሐ) እና (2) ሥር የተደነገገውነን መተላለፋቸው መረጋገጡን ገልጾ፣ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 142(1) መሠረት ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለጥር 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
Average Rating