ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር ዞን በተፈጠረ ግጭት ሳቢያ፣ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ነዳጅ የሚያመላልሱ የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች መተማ ከተማ ለመቆም እንደተገደዱ ተገለጸ፡፡
ማክሰኞ ታኅሳስ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ በመከላከያ ሠራዊት አባላትና በአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ግጭት ተፈጥሮ የሰው ሕይወት ከጠፋ በኋላ የፀጥታ ሥጋት በመጋረጡ ምክንያት፣ ከሱዳን ቤንዚን ጭነው ወደ መሀል አገር በመጓዝ ላይ የነበሩ ተሽከርካሪዎች በመተማ ከተማ ለቀናት ለመቆም ተገደዋል፡፡ ሰላሳ ያህል የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች መተማ ከተማ እንደቆሙ ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ይህም በአገሪቱ የቤንዚን አቅርቦት ላይ ችግር እንዳይፈጥር ያላቸውን ሥጋት ገልጸዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም፣ ያጋጠመው ጊዜያዊ ችግር በመሆኑ በነዳጅ አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ እንደማይኖረው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህ በጊዜያዊ የፀጥታ ችግር የተፈጠረ በመሆኑ በጥቂት ቀናት ውስጥ ይስተካከላል፤›› ያሉት አቶ ታደሰ፣ የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በኮንቮይ ታጅበው ከእሑድ ጥር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ጉዟቸውን የሚቀጥሉ ስለሆነ በነዳጅ አቅርቦት ላይ የጎላ ችግር እንደማይፈጠር አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዓመታዊ የቤንዚን ፍጆታ 494,000 ሜትሪክ ቶን ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 40 በመቶ የሚሆነውን የሱዳን ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን ያቀርባል፡፡ 60 በመቶ የሚሆነውን የቤንዚን ፍጆታ ከዓለም አቀፍ የነዳጅ ኩባንያዎች በጨረታ የሚገዛ በመሆኑ፣ ከ2011 እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ የነዳጅ ግዥ ጨረታ ያሸነፈው ፔትሮ ቻይና ኩባንያ የነዳጅ ውጤቶችን ማቅረብ ጀምሯል፡፡ ፔትሮ ቻይና 350,000 ሜትሪክ ቶን ቤንዚን በጂቡቲ ወደብ በኩል እንደሚያቀርብ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች የተጣራ ቤንዚን የሚጭኑት ካርቱም አቅራቢያ ከሚገኝ ፒሊ ከተባለ የነዳጅ ማጣሪያ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሱዳን የተቀጣጠለው ሕዝባዊ አመፅ ወደ ኢትዮጵያ በሚጓጓዘው ቤንዚን ላይ ተፅዕኖ አለመፍጠሩን የገለጹት አቶ ታደሰ፣ የነዳጅ ቦቴዎቹ ለራሳቸው የሚጠቀሙት የናፍጣ አቅርቦት ችግር ግን እንደገጠማቸው አልሸሸጉም፡፡
በአጠቃላይ ሱዳን ውስጥ በተፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት ቢፈጠርም፣ ለኢትዮጵያ ለማቅረብ ቃል የተገባው የቤንዚን ምርት በመቅረብ ላይ እንደሆነ አቶ ታደሰ አስረድተዋል፡፡
Average Rating