www.maledatimes.com የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የመገንባት ኃላፊነት የተሰጠው ቤቶች ኮርፖሬሽን አዲስ አደረጃጀት ሊያዋቅር ነው - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የመገንባት ኃላፊነት የተሰጠው ቤቶች ኮርፖሬሽን አዲስ አደረጃጀት ሊያዋቅር ነው

By   /   January 13, 2019  /   Comments Off on የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የመገንባት ኃላፊነት የተሰጠው ቤቶች ኮርፖሬሽን አዲስ አደረጃጀት ሊያዋቅር ነው

    Print       Email
0 0
Read Time:2 Minute, 15 Second

የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የመገንባት ኃላፊነት የተሰጠው ቤቶች ኮርፖሬሽን አዲስ አደረጃጀት ሊያዋቅር ነው
የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ኮርፖሬሽን የ20/80 እና የ40/60 ቤቶች ግንባታ ኃላፊነት ይረከባል

በበጀት ዓመቱ የአዳዲስ ቤቶች ግንባታ ባለመጀመሩ አላስፈላጊ ወጪ  እየጨመረ ነው

በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ መስክ ግዙፍ ሥልጣን ተሰጥቶት የተቋቋመው የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ኮርፖሬሽን አዲስ አደረጃጀት ሊያዋቅር ነው፡፡  

ከአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮና በሥሩ ካሉ ተቋማት የተውጣጣ የባለሙያዎች ቡድን፣ በዚህ ሳምንት አዲስ አደረጃጀት ለማዋቀር የሚያስችሉ ሥራዎችን መሥራት ይጀምራል ተብሏል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ እስካሁን የተካሄዱ የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታዎች በሁለት ተቋማት ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ የመጀመርያው 10/90፣ 20/80 ፕሮግራሞች ግንባታ በአዲስ አበባ ከተማ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ ሁለተኛው ደግሞ የ40/60 ፕሮግራም ግንባታ በአዲስ አበባ ከተማ የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ሲካሄዱ ቆይቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ይህ አሠራር አመቺ አይደለም በሚል ምክንያት፣ ሁለቱ ተቋማት ተዋህደው ራሱን የቻለ የቤቶች ኮርፖሬሽን እንዲቋቋም ወስኗል፡፡

በዚህ መሠረት ሁለቱ ተቋማት የተለያየ የሥራ ፀባይ ስለነበራቸውና በአዲስ አደረጃጀት ማጣጣም የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ ባለሙያዎቹ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ በቢሾፍቱ ከተማ አዲሱን አደረጃጀት ዕውን እንዲያደርጉ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው ታውቋል፡፡

የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ተጠሪነቱ ለቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ በርካታ ኃላፊነቶች የተሰጡት ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ኮርፖሬሽኑ ለቤቶች ልማት በከተማ አስተዳደሩ ዋስትና ከባንክ ይበደራል፡፡ ተመዝግበው የሚቆጥቡ ነዋሪዎች ገንዘብ የብድር ወለድ ምጣኔ ከባንኮች ጋር ይደረጋል፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በተገቢ ውል መሠረት የጥራት ደረጃ፣ የጊዜና የዋጋ ገደብ ተጠብቆ መካሄዱን ያረጋግጣል፡፡ ግንባታ የሚያከናውኑ አማካሪዎችንና ሥራ ተቋራጮችን በኮርፖሬሽኑ የግዥ ሕግ መሠረት ይመዘግባል፣ ይመለምላል፣ ወደ ሥራም ያሰማራል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ2010 ዓ.ም. በፊት የ20/80 እና ለኪራይ አገልግሎት የሚውሉ 95,832 ቤቶችን በኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አማካይነት፣ 38,240 የ40/60 ቤቶችን ደግሞ በቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ አማካይነት እየገነባ ነው፡፡

እነዚህ ቤቶች በአጠቃላይ 134,072 ቤቶች ሲሆኑ፣ የግንባታውን ኃላፊነት ደግሞ ከሁለቱ ተቋማት አዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ኮርፖሬሽን ይረከባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት በማስፋፊያ ቦታዎች በሚገኝ 500 ሔክታር መሬት ላይ 48 ሺሕ ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ ተይዞ ነበር፡፡ ነገር ግን ግንባታው ሳይጀመር የበጀት ዓመቱ የመጀመርያው ስድስት ወራት ተጠናቀዋል፡፡

በተለይ በቦሌ አራብሳና በኮዬ ፊጬ አካባቢ ለሚገኙ ስምንት ቦታዎች የተለያዩ ክፍያዎች ተፈጽመው፣ እንዲሁም ለጥበቃና ለመሳሰሉት አገልግሎቶች ክፍያ እየተፈጸመ ቢሆንም፣ ቦታዎቹ ላይ ግንባታ ባለመካሄዱ እየወጣ ያለው ገንዘብ አላስፈላጊ ወጪ ተብሎ ተመዝግቧል፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተካሄደ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ግንባታ ባለመጀመሩ እየወጣ ያለው አላስፈላጊ ወጪ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ መገምገሙን ምንጮች ገልጸዋል፡፡  

ከዚህ በተጨማሪ ሥራውን ማካሄድ የነበረባቸው የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቶች ያለ ሥራ መቀመጣቸውም ተመልክቷል፡፡

በቅርብ ለከተማው ምክር ቤት የስድስት ወራት ሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ ግንባታ ያልተጀመረበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው እንዳሉት፣ በማስፋፊያ አካባቢዎች የተገነቡ ቤቶች ለተጠቃሚዎች እስካሁን ያልተላለፉት ከኦሮሚያ ክልልና ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር አለመግባባት በመፈጠሩ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ አርሶ አደሩ መፈናቀል የለበትም፣ የሚካሄደው ልማት ሁሉንም ተዋናዮች አቅፎ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

የቤቶች ግንባታ መካሄድ ያለበትም በመሀል ከተማ በሚገኙ የመልሶ ማልማት ቦታዎች ላይ መሆን እንደሚኖርበት፣ የሚነሱ የመሀል ከተማ ነዋሪዎችም በልማቱ ተጠቃሚ እየሆኑ ተግባራዊ መሆን እንዳለበት ምክትል ከንቲባው አስረድተዋል፡፡  

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 6 years ago on January 13, 2019
  • By:
  • Last Modified: January 13, 2019 @ 11:48 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar