ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ ክስ የተመሰረተባቸው 11 ተጠርጣሪዎች እነማን ናቸው?
1ኛ.ሜ/ጄኔራል ክንፈ ዳኘው፣
2ኛ.ኮ/ል በርሀ ወልደሚካኤል ገብሩ (ያልተያዘ)፣
3ኛ.ኮ/ል ሙሉ ወ/ገብርኤል ፣
4ኛ.ብ/ጄኔራል ብርሀ በየነ ፣
5ኛ. ሌ/ኮሎኔል ስለሺ ቤዛ ሱላ (ያልተያዘ)፣
6ኛ.ወ/ሮ ሲሳይ ገ/መስቀል ሐረጎት (ያልተያዘች)፣
7ኛ.ዓለም ፍፁም ገብረሥላሴ ፣
8ኛ. ሌ/ኮለኔል አስምረት ኪዳነ አብረሃ፣
9ኛ.ሌ/ኮሎኔል ግርማ መንዘርጊያ ዳምጤ፣
10ኛ.ሻ/ል አግዘዉ አልታዬ አብሬ እና
11ኛ. ኤርሚያስ አመልጋ ናቸው፡፡
የክሱ መዝገብ ምን ይላል?
የክስ መዝገቡ እንደሚያስረዳው ተጠርጣሪዎች የወንጀል ሕግ አንቀዕ 32(1) (ሀ) ፣ 33 እና 407 (1) ሀ ፣ለ እና (3) ስር የተጠቀሰዉን በመተላለፍ በ1ኛ ክስ ከ1ኛ-7ኛ ባሉት ተከሳሾች ላይ የሚመለከት ሲሆን ሪቬራ ኢንተርናሽናል ሆቴል እና ፒ.ቪ.ሲ ፕሮፋይል ፋብሪካን ጨምሮ ግዥ በሚፈጸምበት ወቅት ኮርፖሬሽኑ ያለበትን የእንግዳ መቀበያና ማረፊያ እጥረት ለማቃለል በሚል በሽያጭ ውሉ አንቀጽ ሁለት የውሉ ስምምነት ዓላማ ላይ የተገለጸ ቢሆንም ከጥቅምት 04 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ ምንም ዓይነት የሆቴል ስራ ያልሰራ ፣ ለኮርፖሬሽኑ ለማያስፈልግ ግዢ ያለአግባብ በብር 128,000,000 (አንድ መቶ ሃያ ስምንት ሚሊየን ብር) ግዢው እንዲፈጸም በማድረግ በአጠቃላይ የብር 415,222,069.45 (አራት መቶ አስራ አምስት ሚሊየን ሁለት መቶ ሃያ ሁለት ሺህ ስልሳ ዘጠኝ ብር ከአርባ አምስት ሳንቲም) ከፍተኛ ጉዳት በማድረሳቸው ከ1ኛ እስከ 6ኛ የተጠቀሱት ተከሣሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት 7ኛ ተከሣሽ ደግሞ በልዩ ወንጀል ተካፋይነት በፈጸሙት በስልጣን አላግባብ መገልገል በከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በ2ኛ ክስ 1ኛን ፣ 2ኛን እና ከ8ኛ-11ኛ ያሉትን ተከሳሾች የሚመለከት ሲሆን የኢምፔሪያል ሆቴሉ በወቅቱ ከነበረው የገበያ ዋጋ አንጻር ሲታይ ታክስን ጨምሮ ከብር 41,000,000.00 (አርባ አንድ ሚሊየን ብር) እስከ 51,000,000.0 (ሃምሳ አንድ ሚሊየን ብር) ዋጋ ብቻ ሊያወጣ የሚችል ሆኖ እያለ ያለአግባብ ታክስን ጨምሮ በተጋነነ ዋጋ በብር 72,000,000.00 (ሰባ ሁለት ሚሊዮን ብር) ግዢ በመፈጸም በመንግሥት ላይ በልዩነት የብር 21,000,000.00 (ሃያ አንድ ሚሊየን ብር) ከባድ ጉዳት በማድረሳቸው እንዲሁም የ11ኛ ተከሳሽ ድርጅት ያለአግባብ በልዩነት የተጠቀሰዉን ገንዘብ እንዲጠቀም በማድረጋቸው 1ኛ ፣ 2ኛ እና ከ8ኛ-10ኛ ያሉት ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት 11ኛ ተከሳሽ ደግሞ በልዩ ወንጀል ተካፋይነት በፈጸሙት በሥልጣን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል።
የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
Average Rating