ከዚህ ቀደም ሲል “የአርቲስቱ ጠላቱ ቲያትር ቤቱ” የሚል ትንሽ ፅሁፍ የላኩላቸዉ ሰዎች፤ “አርቲስቱ ነፃ የሚወጣዉ ሲታመምና ሲቀበር መዋጮ እንዳይለመንለት ከሆነ፤ ዝም ብሎ የተሻለ የደመወዝ ምደባ ተጠይቆለት አሁን ባለበት ስርአት መቀጠል ቢችልስ” የሚልና “ይሄማ ቤቱን ሽጠዉ ይካፈሉት፤ መሬቱንም እየተቀበሉ ይቸብችቡት እንደማለት የሚቆጠር ፅንፈኛ ነገር ነዉ” የሚል ሃሳብ አድምጬ፤ ችግሩ ከኤኮኖሚዉ ጋር ብቻ እንዳይያያዝ እና የአርቲስቱ ከተፅዕኖ ስር መዉጣት ከሁላችንም ነፃ መዉጣት ጋር ያለዉን ተያያዥነት በመጠኑ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
አርቲስቶች ራሳቸዉን በማህበር እያደራጁ፤ በክፍለ ከተሞች እየታገዙ ተጠቃሚ ይሁኑ ማለትም፤ ምንም አደናጋሪ ነገር አልመሰለኝም ነበር፡፡ አሁን ዛሬ አስር ሆነዉ ከአንድ ወረዳ የባህል ማዕከል ጋር በመተባባር ቲያትር ቤት የሚመሰርቱት አርቲስቶች ሲከፋቸዉ ወይም ሲጣሉ የተገነባዉን ቤት ሽጠዉ የሚካፈሉት ሳይሆን፤ ንብረትነቱ የዛዉ ወረዳ ህዝብ፤ ቁጥሩንም የሚወስነዉ በወረዳዉ የሚፈጠረዉ ጥበባቸዉን የማየት ፍላጎት በመሆኑ ተጨማሪ ሰዎች ሊገቡበት፤ ላይገቡበት፤ ካቃታቸዉም የጀመሩትም ሊወጡበት የሚችል በመሆኑ፤ የአንዳንዶች ስጋት ከመሬት/ ንብረት ባለቤትነት ጋር ማያያዛቸዉ ተገቢ እና ሰፊ ዉይይትን የሚጠይቅ ነገር መሆኑ ይሰማኛል፡፡ ዋናዉ ጉዳይ ግን መስራት ለሚችልና ለሚፈልገዉ ሰፊ ምርጫ ይኖራል፤ ከሚያገኘዉ ላቅ ያለ ገቢ ሌላ፤ አሁን ከሚስተዋለዉ የመንግስት ተፅእኖ ይላቀቃል፡፡ ቀደም ባለዉ ፅሁፌም ፤ የቤተ-ክህነት አገልጋዮች ቢጣሉ ለአገልጋዮቹ ደመወዝ የሚያገኙበትን ፎቁን ሽጠዉ ተካፍለዉ መቅደሱን ዘግተዉ ይሄዳሉ፤ የሚል ነገር የለም፡፡
በርግጥ መሰረታዊ ለዉጥ ካልተደረገ፤ ስርአት በተቀየረ ቁጥር፤ “ኃይለ ሥላሴ ለዘላለም ይነገስ” ብለሃል፤ “ቀይ-ሽብርን ይፋፋም ብለህ አድንቀሃል”፤ “አንተ አገር ሲዘረፍ፤ ኩራዝ ከእንግዲህ በአገራችን ቀርቷል!” ብለሃል” “ጀግናዉ ባለሁለት ጭንቅላት አሳቢ” እያልክ አደናግረሃል” እየተባባሉ መካሰሱም ላይቀር ነዉ ማለት ነዉ፡፡
“አባቴ፤ የጅብ ስጋ ይበላል ወይስ አይበላም?” ብሎ አንድ ጎበዝ ለጠየቀዉ ጥያቄ አዛዉንቱ ሲመልሱ “ሲርብ ነዉ ወይስ ሳይርብ?” ብለዉ አሉ”፤ የተባለዉን ተምሳሌት ካስተዋልነዉ ብዙ ማብራሪያ አይጠይቅም፡፡ የዛሬዉ ስጋቴም ጥበብና ባሕል ይበላሽብናል ሳይሆን “በዚሁ ከቀጠልን ለልጆቻችን የምናሳልፈዉ አገር አይኖረንም” የሚባለዉን ስጋት አፅንኦት ለመስጠት እፈልጋለሁ፡፡
ከሁለት አመት በፊት ከአንድ ወዳጄ ጋር ፒያሳ አካባቢ ምሳችንን ስንበላ፤ በሬዲዮ የዜና አቅራቢዋ ያቀረበችዉ ዜና ከሞላ ጎደል… “በደቡብ ክልል የሚታየዉን የድድ መድማት እና የቫይታሚን ሲ እጥረት ለመከላከል ሲባል፤ በብዛት በሚበቅለዉንና በህዝቡም ዘንድ በብዛት እየተመረተ በሚበላዉ ሙዝ ዉስጥ “ቫይታሚን ሲ” የተባለዉን ንጥረ-ነገር ጨምሮ ለማብቀል፤ ኖርወይ ከተባለ አገር የመጣ የሳይንቲስቶች ቡድን ከክልሉ መስተዳዳር ጋር ተፈራረመ”…የሚል ስለነበር አሳሳቢም አደናጋሪም ነበር፡፡
መቼም ሙዝ ዉስጥ ቫይታሚ ሲ የሚባለዉን መጨመር የሚችል ሳይንስ አለ/የለም የሚለዉን ጉዳይ ወደ ጎን ትተን፤ እዛ አካባቢ ያለዉ ህዝብ፤ በሁለት እጁ ነዉ ሙዙን የሚይዘዉ?፤ በአንድ እጁ ቃሪያ ወይ ብርቱካን መያዝ አይችልም?…ከኖርወይ ድረስ የመጡት ሳይንቲሰቶች፤ ሙዝ ዛፉ ላይ ወጥተዉ ነዉ በመርፌ ቫይታሚኑን የሚጨምሩለት? ወይስ ከማዳበሪያ ጋር ቀላቅለዉ አፈር ዉስጥ ነዉ የሚጨምሩት?…ከእነኚህ ድዳቸዉ እየደማ ከሚቸገሩት ሰዎች ላይ ግማሹን ሙዝ ወስዶ በመሸጥ ከሌላ ቦታ የፍራፍሬ ድርጅት ለምን ብርቱካን አያመጣላቸዉም?….መቼም ትልቅ ንቀተም ያለበት ስለሚመስል ብዙ ጆክ የሚወጣዉ ክስተት ነዉ፡፡ አሳሳቢዉ ጎኑ ደግሞ፡- ከማዳበሪያዉ ዉስጥ የጨመሩት ይሄ “ቫይታሚን ሲ”ን ከፖታሲየም የሚቀላቅለዉ “ማጅከኛዉ ኬሚካል” በዝናብ ጎርፍ ተጠርጎ ወደ ሐይቁ ሲገባ አሳዎቹን ይገላቸዉና፤ ህዝቡ ድዱ መድማቱ ሳያንሰዉ የሚበላዉ አጥቶ ከተማ ይሰደድና፤ ሎተሪ አዟሪነት፤ ጫማ ጠራጊነት፤ ወያላነት፤ ማጅራት መቺነት ዉስጥ ይገባ ይሆን?…በርቀት የምንኖረዉም ይሄንኑ አሣ በየሆቴሉ በመብላታችን የሆድ-ዕቃ ካንሰር ያስይዘናል ወይስ ኩላሊታችንን ብቻ ነዉ የሚያበሰብሰዉ?…የስኳር በሽታ ያመጣ ይሆን?… መቼም ጉዳዩን ትንሽ ሰፋ አድርገን ከወዳጄ ጋር ስቀንበት ስንጨርስ፤ ለምን ይሄንን እንደማይፅፈዉ አንስተን ስናወራ፤ ጭራሽ ቦታ የሌለዉ “ጆክ” መሆኑንና አደገኛም ሊሆን እንደሚችል ነበር የተረዳሁት፡፡ “የወንፈሌዉ ጥጥ” የተሰኘዉ ገበሬዉ የሚስቱን ዉሽማ በጅራፍ መድረክ ላይ የሚዠልጥበት ጆክ የበለጠ ተወዳጅ/ አትራፊ ሆኖ ሳለ ይህ አይነቱ ነገር ገንዘብ አለማምጣቱ ብቻ ሳይሆን “ሰዎችን ማስቀየም” እንዳይሆን ጭምር በማሰብ ቦታ ማጣቱ፤ ለአርቲስቱ ነፃነት መለመኑ ለተቀረነዉም የህልዉናችንም መሰረት እንደሚሆን ሁሉም የሚረዳዉ ይመስለኛል፡፡
በዛዉ ሰሞን “ቡርኪና ፋሶ” የተባለች በጥጥ ምርት ጥራት ተወዳዳሪ የሌላት ትንሽ የአፍሪካ አገር ዉስጥ “በርካታ ጥጥ ታመርታላችሁ” በሚል ማደናገሪያ የተነሳ መሬታቸዉ ላይ የተነሰነሰዉ “ዘመናዊ ማዳበሪያ”፤ እንደተባለዉ ጥጡን ቢያበዛዉም ጭራሽ በአለም ገበያ በጥራቱ የማይፈለግ ነገር በማምረታቸዉና ድጋሚ እንዳያመርቱም አፈሩ በመበላሸቱ በፍርድ ቤት ከትልቅ ኩባንያ /ሞንሳንቶ/ ጋር ክስ ከፍተዉ የሚጨቃጨቁበትና፤ የተራበዉ ወጣት ገበሬም በስደት አዉሮፓ ለመሄድ ሜድትራንያን ባህር ዉስጥ እየሰጠሙ ማለቃቸዉ በስፋት የሚነገርበት ሰሞን በመሆኑ የዚህ ሙዝ ዜና አስፈሪም ነበር፡፡ እንደ እኛ አገር በመሰለ በግብርና የሚተዳደር አገር፤ ትልቁ ንብረቱ አፈሩና ዉሃዉ በመሆኑ፤ ሰበታ የተዘራዉን “የሙከራ እህል” አበባ የነኩት ንቦች ወልቂጤ ድረስ ሄደዉ እዛም የሚበቅለዉን እህል ሳያፈራ ስለሚነኩት መዘዙ የማንቆጣጠረዉ መሆኑን ለመገንዘብ የእርሻ ሊቅ መሆን አያሻም፡፡ የራሳችንን ብቻ ሳይሆን ለልጆቻችንም አገሩ እንዲያልፍ እንዲህ ያለዉ “ጆክ” በስፋት በየቀበሌዉ/ከተማዉ/ወረዳዉ ሊተወን/ሊዘፈን እና ራስን ቅጥ ካጣ መንገብገብ ገድቦ አገር ማዳንም ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡
መቼም ዛሬ የሚያነበዉ ካለ ብዙ መረጃዎች በስፋት የሚወጡበት ዘመን በመሆኑ ማንኛዉም ሰዉ በያዘዉ ስልክ፤ ማንበብ ማወቅና ራሱን እና ልጆቹን ከሚሰጣቸዉ የታሸገ ጁስ አንስቶ፤ እስከ ትልቁ የቅኝ ገዢ ሃይሎች አክሳሪ ፕሮፓጋንዳ ድረስ ብዙ ሳይደክም መረዳት የሚችልበት ዘመን በመሆኑ፤ ጉዳዩ ለ“ኤክስፐርቶች” ብቻ የሚተዉ ነገር አይመስለኝም፡፡ በርካታ ቀና ሰዎች ጥቅሙ ቢቀርባቸዉም፤ ለህይወታቸዉም ጭምር አደገኛ ቢሆንም፤ አዉጥተዉ የሚናገሩት ብዙ ሚስጥር፤ አንዱ ደብቆ ባያቀርበዉ በሌላዉ የመገናኛ ብዙሃን በስፋት የሚለቀቅ ዜና በመሆኑ የዘመናችንን አደገኛነት መመልከቱ አዳጋች አይሆንም፡፡ ጥበቡም ከአዳናጋሪነት እና ድግስ አድማቂነት ተላቆ ህዝባዊ ጠቀሜታ ያለዉ አገራዊ ተልእኮ የሚኖረዉ፤ አማክለዉ ሊቆጣጠሩት ከሚችሉት ሃይሎች በርቀት በተን ብሎ መቀመጥ ሲችል ብቻ ይመስለኛል፡፡
ከስድስት ወር በፊት፤ ዛምቢያ በሚባለዉ የአፍሪካ አገር፤ ምንም የማይረባ ከተማ የሚያጣብብ ፎቅና፤ የትም የማይወስዱ ድልድይ እና መንገዶች፤ በአጠቃላይ ዘላቂ የኤኮኖሚ ፋይዳ የሌለዉ “ኢንቨስትመንት ብድር” ዉስጥ ገብተዉ እዳዉንም መክፈል ሳይችሉ ስለቀሩ፤ የመብራት ኃይል ባለስልጣን የሆነዉን መስሪያ ቤታቸዉን ለዉጭ አበዳሪዎች በክፍያ መልክ መስጠታቸዉ ትልቅ ዜና ሆኖ ነበር የከረመዉ፡፡ ጎረቤታችን ኬንያም ሞምባሳ ያለዉን ወደብ፤ እዳቸዉን መክፈል ስላቃታቸዉ፤ ለእነኚሁ አበዳሪዎች በዕዳ ክፍያ መልክ መልቀቅ እንደተገደዱ ስንሰማ፤ ናይጀሪያ ዉስጥ ለሰዉ ልጅ ጤና ጭራሽ ጠንቅ የሆነ “-ኮላ” የፈጠረዉን የፍርድ ቤት ድራማ ያስተዋለ፤ የቴታነስ ክትባት ተብሎ ከ14-49 አመት ድረስ ያሉ ኬንያዉያን ሴቶች እንዲወስዱት የተደረገዉ ክትባት ጭራሽ ከተባለዉ ችግር ጋር የማይገናኝ መሆኑ ለሚሰማዉ ሰዉ፤ “አገሬ እየተበላች ዘፈን ይቅርብኝ” ብሎ ከማለት ወደኋላ እንደማይል ይታሰበኛል፡፡ ይሁን እንጂ አዲሶቹ ኮሎኒያሊስቶች ሁላችንንም በረቀቀ ዘዴ ለመቆጣጠርና ህዝቡ ራሱን የሚችልባቸዉን የተፈጥሮ ሃብቶች እንዳይጠቀምበት፤ በራሱ አገር በራሱ ሰዎች/ በተለይ የአርቲስቶቹን እና የፖለቲከኞቹን ክህሎትና መንገብገብ/ጉልበት ተጠቅመዉ ሁላችንንም ጥገኛ ለማኝ አድርገዉ ለስደትና እልቂት እያመቻቹት መሆኑ ማንም ማንብብ ለሚፈልገዉ ብዙ ምርምር የሚጠይቅ እዉነታ አይደለም፡፡
ከጥቂት አመታት በፊት፤ ቤተሰቤን ይዤ እቃዬን ጠቅልዬ አገሬ ገብቼ ነበር፡፡ በእርግጥ ለእኔ የሚሆን ሥራ አገሬ አልነፈገችኝም፡፡ የ”መንግስት” የሚባለዉ ስላልተስማማኝም ጥሩ ደመወዝ፤ መኪና እና በሳምንት አርባ ሊትር ነዳጅ በነፃ የሚሰጠኝ የግል ድርጅት ተቀጥሬ በስደት ያፈራኋቸዉን ልጆቼን ከህዝቡ ቀላቅዬ ደስ የሚል ኑሮ ጀምሬ ነበር፡፡ በወቅቱ /ርዕሱ ጠፋኝ/ እሁድ እሁድ ከሰአት በኋላ የሚታይ ተከታታይ የቲቪ ድራማ ነበር፡፡ ሰራተኛችንም ስራዋን በፍጥነት ጨራርሳ አይኗን ሳትነቅል በመገረም ነበር የምትመለከተዉ፡፡ በታሪኩ “ግፍ የሚፈጸምባት ሰራተኛ” ስለነበረችበት፤ ድራማዉ ያለባትን ችግር በመጠኑም ቢሆን ስለሚያሳያት፤ ከእኔ ይልቅ ለእሷ በጣም የቀረበ ነበር፡፡
ይቺ ሰራተኛችን፤ የካርኔሽን አባባ እርሻ ዉስጥ አንድ አመት ሰርታ፤ የዉስጥ ደዌዋን ባላዉቀዉም፤ ፊቷ እጆቿና አንገቷ በእሳት የተለበለበ ነበር የሚመስለዉ፤ /መጀመሪያ ላይ እኔም ተጠይፌ፤ የእሷን ፊትና እጅ ከማየት ሌላ ሰራተኛ ቢገኝ በማለት፤ አከላክዬ ነበር፡፡ ግና ይሄዉ የአበባ እርሻ ብዙዎችን/ያልሰሙትን በተሻለ ገንዘብ ስለሚቀጥር፤ የቤት ሰራተኛ ማግኘት በጣም ችግር የነበረበት ጊዜ ስለነበር ምርጫ እንደሌለ ሳዉቀዉ ብቻ የተቀበልኩት እንጂ፤ በጎ የማድረግ ፍቃድ እንዳልነበረኝም መግለፅ እወዳለሁ፡፡ ስለ ሁኔታዉ የበለጠ ስረዳዉ ግን እኔም እሷም ጉዳተኞች መሆናችን ግልፅ ነበር፡፡ ይቺ ልጅ ወደፊት የምትወልዳቸዉ ልጆች በእርግጥ እኔ ጡረታ ስወጣ አርሰዉ እህል ወደ ገበያ በማምጣት ወይ በሌላ በሚጠቅመኝ ነገር ላይ ይሳተፉ ይሆን? ብትፈልግስ በጤና መዉለድስ ትችል ይሆን?…ይሄ ኬሚካልም በዛዉ በላስቲክ በተከለለዉ ሜዳ ቀርቶ ስለማይቀር የዝናቡ ጎርፍ የምንጠጣዉ ዉሃ ዉስጥ ይከተዉ ይሆን?፤ የአካባቢዉን ሳር የበሉት በጎች፤ ላሞች ስጋ ወተት፤ አይን የሚያጠፋና ኩላሊታችንን የሚያበሰብሰዉ ይሆን? ወይስ የስኳር በሽታ ነዉ የሚሰጠን? እነኚህን ልጆቼን አገር፤ ቋንቋ አስለምዳለሁ ብዬ አደጋ ዉስጥ ይሆን የከተትኳቸዉ?…እኔስ ይሄንን ፍርሃትና ሌላም ነገር በማሰብ ምርጫዉም ስለነበረኝ ልጆቼን ይዤ ተመልሼ ወጣሁ፤ የእሷን ግን አላዉቅም፡፡ ፍርሃቴ ተገቢም ሆነ አልሆነ ከእሷ መበደል ጋር ደምረዉ መንገር የሚፈልጉ ቢኖሩ በርግጥ መድረኩ አላቸዉ? ከዛዉ ቀበሌ/ወረዳ ጋር ትስስር ያለዉ የአርቲስት ቡድን ቢኖር እናቱ/እህቱ/ጎረቤቶቹ ሰዉነታቸዉ በኬሚካል እየተጠበሰች ይሄንን እዉነታ በብልሃት ሳይነግርላቸዉ በዝምታ ይቀመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡
ሁላችሁም እንደምትታዘቡት በዚህ ዘመን የሚነገረዉ “ዜና” ፈጠራ/ፊክሽን ነዉ የሚመስለዉ፡፡ መቸም ትክክል ይሁን አይሁን በቦታዉ ያጣራሁት ነገር ባይኖርም፤… በቡራዩ አካባቢ አስተዳደሩ የማያዉቀዉ፤ የአንድ ግሎባል ድርጅት ንብረቶች የሆኑ “ሄሊኮፕተርና መለስተኛ አዉሮፕላን ተገኘ” የሚል ዜናም በቅርቡ ሰምቼ ነበር፡፡ መቸም መጀመሪያ የመጣብኝ ሃሳብ “ምን ይሆን ሲሰሩ/ሲበትኑ የቆዩት?…እዛ አካባቢ ወንዝ ነበር?፤ ከእነኚህ የበረራ ማሽኖች የሚደፋዉ ኬሚካል ወደ ወንዝ ነበር የሚሄደዉ? ከላይ ከዝናቡ ጋር ነበር የሚለቁት?፤ ሰዎች ከብቶች ይጠጡት ነበር?፤ በአካባቢዉ ሰዉ አይኑ እየጠፋ፤ የአይን መነፅር “በነፃ” የሚያከፋፍል “በጎ አድራጊ” ድርጅት ገብቶ ይሆን? …በአጠቃላይ ዛሬ በአለም ላይ የሚደረገዉን የተለያየ እኩይ ሙከራዎችን ያስተዋለ (ሄግሊያን ዲያሌክቲክ) እጅግ ብዙ ጥያቄዎችን ሊያነሳ ይችላል፡፡ መቼም የቡራዩ አስተዳደደር የአቪየሽን/ በረራ ፍቃድ ሰጪ ይሁን፤ ባይባልም፤ ይሄን ፈቃድ የሚሰጠዉ የበላይ መስሪያ ቤት ከቡራዩ አስተዳደር ጋር ተነጋግሮ፤ እዛ ያለዉ ህዝብም በመሬቱ በከብቶቹ የሚደርሰዉን ጉዳትና ጥቅም አዉቆት ለማድረግም ላለማድረግም ሳይጠየቅ… “ድንገት በተደረገ ጥቆማ ሄሊኮፕተር ቡራዩ ተገኘ” ሲባል አገሬ የትሄዳ ነበር፤ ያሰኛል፡፡
ኮሎኒያሊስቶች በጠመንጃ አስገድደዉ ከአገር እንደማያፈናቅሉን ሰለሚያዉቁት፤ የሚመጡበት መንገድ የተለየ መሆኑን ዛሬ ብዙዉ የሚያዉቀዉ ጉዳይ ነዉ፡፡ ይሄንን ማደናገር ለመቋቋም ሰዎችን በተናጠልም በጋራም የሚያገናኝና የሚያነጋገር ነፃ የጥበብ መድረክ መኖሩም እጅግ ወሳኝ በመሆኑ፤ ሁላችንም ተገቢዉን እርዳታ በማድረግ፤ የጥበብ ቤቶችም አሁን ከሚታዩት ቁጥራቸዉ በዝቶ አርቲስቶችም ስራዎቻቸዉን “ይሄ ብር አለዉ፤ የለዉም፤ ያከስረኛል፤ ያሳስረኛል” ሳይሉ የሚሰሩበት ስርአት ለመፍጠር መረዳዳት የሚኖርብን ይመስለኛል፡፡
አሁን ከርቀት እንደሚታየኝም ስልጣን ወደ ቀበሌ /ወደ ህዝብ እየተመለሰ ነዉ፡፡ “ማዕከላዊ መንግስት” የሚባለዉ ቡድን፤ ያለ ቀበሌዉ እና ነዋሪዉ እዉቀት እንደፈቀደዉ ለሄሊኮፕተር መሳረፊያ ወይም “የወይዘሮ ማንደፍሮሽ እርሻ ነዉ” የሚባልና በደፈናዉ “መንግስት ነዉ ያጠረዉ፤ እኛን አይመለከተንም” የሚባል ነገር የማይኖርበት ዘመን ይመጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ እንዲህ አይነት ማደናገርም እንዳይቀጥል፤ ነፃ ሆኖ የሚናገርልኝ እዛዉ ከቀበሌዉ/ከወረዳዉ የባህል ማእከል ጋር የተቀናጀዉ ነፃዉ የሕዝቡ አጋር አርቲስቱ ነዉ፡፡
ማዕከላዊዉ መንግስት ከአንድ ሁሉንም አድራጊ/መለኮታዊ “ባለ ጭንቅላት” ባለስልጣን ወይም ቡድን እጅ ወጥቶ በቀላሉ ሕዝቡ አኩርፎ ድንጋይ መወርወር ሲጀምር /የድሃ አገር “ቮት ኦፍ ኖ-ኮንፊደንስ”/ የሚፈርስ ደካማ ተቋም መሆን እንደሚኖርበትም ፅኑ እምነትና ምኞትም አለኝ፡፡ (መንግስት ቶሎ ቶሎ እንደ ዳይፐር መቀየር ያለበት ነገር ነዉ፤ ይላሉ አንዳንድ ተመራማሪዎች) በመሆኑም አርቲስቱን ከዚህ አይነት ተለዋዋጭ መንግስት ህልዉና ጋር በማያያዝ፤ የማያምንበትን ግጥም በቁንጥጫ እየፃፈ፤ እዚህ በፈረንጅ አገር ያሉት የሆሊዉድ ካድሬዎች እንደሚያደርጉት፤ እርስ በእርስ ዋንጫ እየተሸላለሙ ያደናግሩልን ማለቱ አግባብ አይመስለኝም፡፡
መቼም ብዙ ሰዎች፤ በከተማ ዉስጥ ከሚታዩት ትላልቅ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች መሐል፤ ያለብንን እዳና፤ ዉለን ለማደር የሚያስፈልገንን እርዳታ፤ በአገር ከምናመርተዉ ጋር ያለዉን ሬሺዮ/ልዩነት የሚያመለክት ቁጥር የሚያሳይ ትልቅ ዲጂታል-ሰሌዳ በየአደባባዩ ተሰቅሎ ቢታይ፤ ኑሯችን ከትናንትናዉ መሻል/ አለመሻሉን ብናየዉና፤ አገሩ ለልጆቻችን ማለፍ ይችል እንደሆነ/ እንዳልሆነ ማየት ቢቻል እጅግ የሚወዱት ይመስለኛል፡፡ ነፃ የሆነዉ አርቲስት ተግባርም ከዲጂታል ሰሌዳዉ ያልተለየ እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም፡፡
አርቲስቱ ነፃ ሆኖ “ይሄን ያደርጋል ይሰራል ስል” ምንም ተቃዉሞ የለበትም፤ በህይወቱም በኑሮዉም የሚያሰጋዉ ነገር ሁሉ ሙልጭ ብሎ ጭራሽ ይጠፋል፤ በደፈናዉ አሁን “አርቲስት” የሚል መታወቂያ የያዘዉም ሁሉ ፈተናዉ ይቀርለታል ማለትም አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ፤ የአርቲስቱ ከወረዳ/ ከክፍለ-ከተማ ጋር ተያይዞ፤ ከህዝብ የባህል ማዕከል ዉስጥ መታቀፉ ራሱን ከመከላከል አልፎ የተቀረነዉንም ከመራብና ከመሰደድ፤ ከእርስ በእርስ ሽኩቻ/ ጦርነት ሊያድነን እና አገራችንንም ለልጆቻችን ለማሳለፍ ይረዳናል የሚል ፅኑ እምነት ስላለኝ ነዉ፡፡ በጎ ማድረግ ለሚፈልገዉም ወገን ቀረቤታን፤ ባለቤትነትን ይፈጥርለታል፡፡ ስለ ልብስ፤ ቀለቡ፤ መታከሚያዉ፤ ስለ ልጆቹን ማሳደጊያ የማይለምን ነፃ የሆነ አርቲስት፤ ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ከሙኒሲፓል የቦንድ ሽያጭ ጋር /ከታክስ አሰባሰብ ስርዓት ጋር የተያያዘ አፈጣጠር ያለዉ፤ የየአካባቢዉ የባህልና ስፖርት ማእክል አቅም የሚያረጋግጠዉ እዉነታ መሆን ይኖርበታል፡፡
ለአርቲስቱ የተሻለ ዋስትና ያለዉ ስርአት ሲጠየቅ ይህ የመጀመሪያዉ እንዳለሆነ ብዙዎች የሚያዉቁት ይመስለኛል፤ በጣም አጨቃጫቂና በአንድ ወቅት የተጠየቀላቸዉ ልዩ የደመወዝ ስኬል ዉድቅ በመደረጉ ምክንያትም፤ ብዙ ደም ያፋሰሰ ጉዳይ እንደነበርም ሲነገር አድምጫለሁ፡፡ እኔም ዛሬ ሃሳቡን ስደግመዉ እንዲህ በቀላሉ ይፈታል የሚል እምነትም የለኝም፡፡ የማእከላዊዉ መንግስትም ይሄንን በምኒስቴር ደረጃ የተዋቀረዉን ሃይል ነፃ ማዉጣቱ፤ ትልቅ የማደናገሪያ ጉልበቱን ማጣት ሊሆን ስለሚችል ማከላከሉ እንደማይቀር ይሰማኛል፡፡ ይሁን እንጂ ዘመኑ ብዙ “አይሆንም” የተባሉ ነገሮች የሚሆኑበት በመሆኑ፤ ምናልባት ዛሬ የሰፋ ዉይይት በሚመለከታቸዉ ተካሂዶ፤ ሃሳብ መሆኑ ቀርቶ ተግባራዊ ይሆናል የሚል ምኞት አለኝ፡፡
ከአክብሮት ሠላምታ ጋር
ጌታቸዉ ታረቀኝ
Average Rating