የዛሬው ኢህአዴግ ሹማምንቶች ሆይ፡- ድራማችሁ ይብቃ!
መርጦ እያሰሩና ፈርቶ እየተው፣ የሕግ የበላይነትን ማስከበር የለም!
“ተታኩሱን አንይዝም፤ ክልሉም ጌታቸው አሰፋን አስልፎ ለመስጠት አልተባበረም” የሚል አንድምታ ያለው ምላሽን ጠቅላይ ዐቃቤ አቶ ብርሃኑ ለፓርላማ መናገራቸውን ሰምተናል። …ያው በእነጌታቸው አሰፋ ላይ አቅመ-ቢስ መሆናቸውን በገደምዳሜ ማመናቸው ነው።
አንድ ተጠርጣሪ በጸጥታ ሃይሎች ሊያዝ ሲታሰብ፣ ምን አይነት አካሃድ እንደሚደረግ የሚታወቅ ነው፤ ኖረውበታልና በደንብ ያውቁታል። የታጠቁ የጸጥታ ሃይሎች ከህጋዊ አሳሪዎች ጋር አብረው የሚሄዱት ተጠረጣሪው ለመያዝ ተባባሪ ካልሆነ ተመጣጣኝ ሃይል ተጠቅሞ አስሮ ለህግ ለማቅረብ ነው – ብዙም ሰምና ወርቅ የለውም። …
የአሁኑ ኢህአዴግ በከባድ ሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠረውን ጌታቸው አሰፋን አስሮ ለህግ ለማቅረብ “ቅዱስ መንገድ” የምከተል ነኝ አይነት ትርክቱን ነው ያሳየን።
ያው በበኩሌ ውሸትን እያየሁ ዝም አልልም!
የብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ የግፍ እስር ሁኔታ ተዘርዝሮ አያልቅም። ግን ትንሽ ምሳሌ ልጥቀስ። እስክንድር ነጋን በልጁ ፊት ነበር በካቴና አስሮ ወደግፍ እስር የከተቱት።
በጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ፣ እነውብሸት ታዬን፣ በርዕዩት ዓለሙን፣ …ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔርን፣ ሂሩት ክፍሌን …እንዴት አድርገው ሰብዓዊ መብቶቻቸውን በአሳፈሪ ሁኔታ ጥሰው እንዳሰሯቸው ይታወቃል። እነእንዷለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ አንዷለም አያሌው፣ ክንፈሚካኤል ደበበ፣ ባህሩ ደጉ፣ ዮናታን፣ ዘላለም ወርቃገኘሁ፣ ሃብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺ፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ፣ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች …በሂደት የዞን 9 ጦማሪያና ጋዜጠኞች …ወዘተ …በምን መልኩ እንደታሰሩ ይታወቃል።
የነጻነት ታጋዩን አንዳርጋቸው ጽጌን ከየመን ሰንዓ በምን አይነት እንስሳዊ መንገድ ይዘው በማሰርና በጆንያ በመሸፈን አስረው በማምጣት እንዳሰቃዩት ይታወቃል። …ብዙ መዘረዘር ይቻላል።
የህወሃት/ኢህአዴግ ክፋ ስራ ይደገም አልልም። ግን በሕግ አግባብ፣ አንድን በከባድ ወንጀል የሚጠረጠርን ግለሰብ መያዝ ከበደኝ አይነት ድራማ ማየት በምንም አይነት አግባብ ነው ብዬ አላምንም! ጠቅላይ አቃቤ ህጉ የትግራይ ክልል ጌታቸው አሰፋን አሳልፎ ለህግ ለማቅረብ ተባባሪ አይደለም ይልህና አብይ አህመድ የክልሉን ም/ርዐሰ መስተዳደር ከሆኑት ደብረፂዬንን ጋር በቀናት ልዩነት እጅና ጓንት ሆነው ሲጓዙ ታያቸዋለህ።
…መቼም በሀገራችን ተቃርኖሽና አስመሳይነት በሽበሽ ነው። አሳዛኙ ነገር፡- ብዙ አድርባይ ሰው፣ ተቃርኖውን አይቶ እንዳላየ በመሆን፤ እውነትን ክዶ በውሸት መታለልን ብሂሉ አድርጎታል። ..ከብዙ ጥፋት በኋላም፣ ነገ ላይ “አሃ” ብሎ ሲቆጭ ታገኘዋለህ! …ከረፈድ በኋላ!
ተቀምሮ አጀንዳ ይሰጠዋል። ለአጀንዳዎች እልል ይላል። መልሶ ይረሳል። ሌላም አጀንዳ ይሰጠዋል። ለዚያም እልል ይላል …የአጀንዳ አዙሪቱና እልልታው ይቀጥላል። …በመልስም ዘመን የአጀንዳ ጋጋታው ይታወቃል። …የጌታቸው አሰፋም ሊታሰር ነው የዜና ርዐሰ ጉዳይ አጀንዳ አንድ ሰሞን ተናፈሰ። ዛሬ አጀንዳው መሆኑ ተረስቶ ሌላ ጉዳይ ላይ ተገብቷል። …
የአሁኑ ኢህአዴግ፣ ለብዙሃን ንጹሃን ዜጎች የግፍ ሞት፣ እስር፣ የአካል መጉደል፣ ስቃይ …እጁ እንዳለበት ታምኖ በከባድ ወንጀል የሚጠረጠርን ሰው (ጌታቸው አሰፋ …ሌሎችም አሉ) አዘናግቶና አረሳስቶ ዝም ማለቱ ከተጠያቂነት አያስመልጠውም! …ድራማው ይብቃ እላለሁ!
Average Rating