የማንኛውም መንግሥት ቅቡልነት ማረጋገጫው በዴሞክራሲያዊ ምርጫ አብላጫ ድምፅ ማግኘት ነው። ምርጫ ማካሔድ አንዱ የዴሞክራሲ መገለጫ መንገድ እንጂ ብቸኛው እንዳልሆነ ከግንዛቤ እንዲገባ ያስፈልጋል። ሕዝባዊ ተቃውሞዎች፣ በገዢው ግንባር ውስጥ የፖለቲካ ትግል በመፍጠራቸው፣ እንዲሁም ሌሎች ድምር ገፊ ምክንያቶች በመጋቢት ወር 2010 በኃይለማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የሚመራውን መንግሥት ከሥልጣን እንዲወርድ እና በምትኩም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራ አዲስ መንግሥት እንዲሰየም ሆኗል።
የዐቢይ አስተዳደር የተጀመረውን የሽግግር ዘመን በማስቀጠልና ከፍተኛ ቁርጠኝነት የሚጠይቁ ውሳኔዎችን እና እርምጃዎችን እየወሰነ አገር የመምራቱን ሚና ቀጥሎበታል። አዲስ ማለዳ እስከ ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ድረስ የዐቢይ አስተዳደር ‘ሊከውናቸው የሚገቡ ወሳኝ ሥራዎች ምንድን ናቸው?’ በሚል ለተደራሲዎቿ ባቀረበችው የበይነመረብ የአስተያየት መጠይቅ ባገኘችው ግብረ መልስ መንግሥት በቅደም ተከተል ሊያከናውናቸው የሚገቡ ናቸው የተባሉትን አምስት ዐቢይ ጉዳዮች መለየት ችላለች። እነዚህም፦ ሰላምና መረጋጋትን ማስጠበቅ፣ ብሔርተኝነት ላይ መሥራት፣ የምጣኔ ሀብት መነቃቃት መፍጠር፣ ሕዝባዊ ውይይትና ተቋማዊ መሻሻል ማድረግ እና ለውጡ እንዳይደናቀፍ መሥራት የሚሉት ናቸው።
እነዚህን አምስት ነጥቦች በመንተራስ እና ለጉዳዮቹ ቅርበት ያላቸውን ባለሙያዎችና ግለሰቦች በማናገር የአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ የሚከተለውን ሐተታ ዘ ማለዳ አሰናድቷል።
በተለያዩ አገራት ውስጥ የተካሔዱ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የሚደረጉ መንግሥታዊ ለውጦችን ለማፅናት፣ እንዲሁም የተረጋጋ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማስፈን የሽግግር ወቅት ሥራዎች ወሳኝ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመራው “የለውጡ መሪ መንግሥት” በሕዝባዊው ተቃውሞ እና ከፍተኛ ጫና እንዲሁም በገዢው ግንባር ውስጥ በተካሔደው የውስጥ ትግል የተወለደ ነው።
ባለፉት ዐሥር ወራት ኢትዮጵያ ውስጥ ሊታሰብ የማይችል የሚመስል፣ በቅርቡም ይሆናሉ ተብለው ያልተጠረጠሩ፣ ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች በመንግሥት ተወስደዋል። የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፣ በትጥቅ ትግል መንግሥት ለመገልበጥ ሲሠሩ የነበሩ ቡድኖችን ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ሕጋዊ ዋስትና መስጠት፣ አፋኝ ሕጎችን መከለስ (በሥራ ላይ ያለ)፣ የመገናኛ ብዙኀን ምኅዳሩን መክፈት፣ በሰብኣዊ መብቶች ጥሰትና በከፍተኛ ሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለፍርድ ማቅረብ ከተወሰዱት ዘርፈ ብዙ እርምጃዎ ጥቂቶቹ ናቸው። የውጪ ግንኙነትን በተመለከተ ከኤርትራ ጋር ሥምምነት ላይ መደረሱ እንዲሁም ከጎረቤት አገራት፣ መካከለኛው ምሥራቅ እና አውሮፓ መንግሥታት ጋር በኹለትዮሽ ጉዳዮች ላይ አብሮ የመሥራት ሥምምነት ተደርሷል፤ በጥቅሉ፣ ከአገር ገጽታ ግንባታ አንፃር ይበል የሚያሰኙ ሥራዎች ተሠርተዋል።
ይሁን እንጂ በሌላ በኩል ደግሞ የተስፋ ጅማሮውን ሥጋት ላይ የሚጥሉ ብሎም የሚያጨልሙ ብዙ ተግባራቶችም እንዲሁ እየተከሰቱ ነው፤ በመከሰትም ላይ ናቸው። “መጤና ነባር” በሚባሉ ትርክቶች እና ግጭቶች ሳቢያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከቀዬቸው መፈናቀላቸው፣ የደቦ ፍርድ (“የመንገድ ፍትሕ”) እና ግድያዎች፣ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውሮች፣ “ትጥቅ መፍታት ከነበረበት” ድርጅት ጋር ዳግም የ”ውጊያ” ፕሮፓጋንዳ መግጠም፣ የምጣኔ ሀብት “አሻጥሮች” እና መቀዛቀዞች እንዲሁም የፌደራሉ መንግሥት ከክልል መንግሥታት ጋር ባለው ግንኙነት “የተዳከመ መምሰል” ጎልተው መታየታቸው የአገሪቱ ዘላቂ ዕጣ ፈንታ ላይ ስጋት እንዲያንዣብብ መንስዔ ሆነዋል።
የዴሞክራሲ ሽግግሩን በተሳካ ሁኔታ ለማስኬድ፥ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ‘መንግሥት ቅድሚያ ሰጥቷቸው መሥራት የሚገባቸው ጉዳዮች ምን ምን ናቸው?’ ብለን በበይነመረብ ላይ ባቀረብነው ጥያቄ መሠረት የተሰጡንን መልሶች በመጭመቅ በባለሙያዎች አስተንትነናቸዋል።
1ኛ. ሰላም እና መረጋጋትን ማስፈን
ለአዲስ ማለዳ የበይነመረብ መጠይቅ ምላሽ ከሰጡጥ ተደራስያን ውስጥ ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ መንግሥት እስከ ቀጣዩ ምርጫ ድረስ ትኩረት አድርጎ መሥራት ከሚገባቸው ወሳኝ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚውን ሥፍራ የያዘው ‘ሰላምና መረጋጋት ማስጠበቅ’ የሚለው ነው። በርግጥም በተለያዩ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች እየተስተዋሉ ያሉት ደም አፋሳሽ ግጭቶች፣ የዜጎች ከቀዬቸው መፈናቀሎች፣ የመሣሪያ ዝውውሮች እና ሌሎችም ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ያደረጉበትን ሁኔታ በዕለት ዜና ውስጥ መስማት የተለመደ ነገር ነው።
የቀድሞው የሙስሊሞች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ቃል አቀባይ የነበሩ እና አሁን ደግሞ የተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ አባል የሆኑት አሕመዲን ጀበል የመንግሥትን ሰላም ማስከበር አስፈላጊነት ሳይዘነጉ፥ “ለእኔ ወሳኙ ጉዳይ ‘እውነት ዴሞክራሲ እንፈልጋለን ወይ? ውጤቱንስ ለመቀበል ዝግጁ ነን ወይ?’ የሚለው ነው” በማለት ይጠይቃሉ።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው እና ሥማቸው እንዳይገለጽ ያሳሰቡት የሰላምና ደኅንነት ባለሙያ የአዲሱ አመራር ወደ ሥልጣን መምጣት በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የለውጥ ተስፋና መነቀቃትን የፈጠረ መሆኑን ገልጸው፥ በሰላምና መረጋጋት ዙሪያ ግን መንግሥት ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ያለበት ጉዳይ መሆኑን አሥምረውበታል።
መንግሥት ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ሦስት ነገር ላይ ማተኮር ይገባዋል ያሉት ባለሙያዋ፣ እነሱም በሁሉም እርከኖች ላይ በሚገኙ የፌደራልም ይሁን የክልል መንግሥታት አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣታቸውን ማረጋገጥ፣ ከዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ጋር በተያያዘ ሥራዎች በፍጥነት መሬት ላይ ወርደው እንዲተገበሩ፣ እንዲሁም ኅብረተሰቡ ሰላሙን በራሱ መጠበቅ እንዲችል የማኅበረስብ ፖሊስ ሥራ አጠናክሮ በአዲስ መልክ እንዲከናወን ማድረግ የአገር ሰላምና ደኅንነትን ለመጠበቅ ያስችላል ብለዋል፤ ለዚህም እንደ አዲስ በተነቃቃ መልኩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት መምህር ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር) የሰላም እና ደኅንነት ባለሙያዋን ሐሳብ ይደግፋሉ። “በዜጎች መካከል የትብብር ፖለቲካ፣ የጉርብትና ፖለቲካ፣ የማኅበረሰብ ፖለቲካ መሠራት ይገባዋል” ያሉት ዮናስ “በትክክል መዋቅራዊው ሥራ እየተሠራ ከተሔደ ማኅበረሰብ ተደራጅቶ አካባቢውን በመጠበቅ የመንግሥትን ሥራ ማገዝ ከቻለ፣ በለውጥ ሒደት ውስጥ የሚኖሩ መንገራገጮች እየቀነሱ ይሔዳሉ” ሲሉም አክለዋል።
ሰለሞን መብሬ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት መምህር ናቸው። እርሳቸውም በበኩላቸው ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን ሕግን ማክበርና ማስከበር መሠረታዊ የመንግሥት ኃላፊነት ነው ይላሉ።
ሰላምና መረጋጋትን በዘላቂነት ለማስፈን የሰላምና ደኅንነት ባለሙያዋ በአፅንዖት እንደተናገሩት፥ የወጣቶች ትምህርት ላይ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ እንደሚገባ እና በውጤቱም “በትምህርት፣ በሥነ ምግባርና ራስን በመግለጽ” የታነፀ ወጣት ለመፍጠር እንደሚቻል ገልጸዋል።
2ኛ. ጠርዘኛ ብሔርተኝነትን መቆጣጠር
ብሔርተኝነት ከብያኔው ጀምሮ ብዙ አጨቃጫቂነትና ስሱነት ያለበት ፅንሰ ሐሳብ መሆኑን በዙሪያው የተጻፉት ጽሑፎች ይመሰክራሉ። ብሔርተኝነትም ሆነ ዴሞክራሲ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚከናወኑ ማኅበረ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በተደራጀ መልኩ የሚመሩባቸው ርዕዮታዊና ሥርዓታዊ ዕሳቤዎች ምንጭ መሆናቸውን ዓለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) “ምሁር” በሚለው መጽሐፋቸው ጽፈዋል። ‘ሁለቱም የብሔርተኝነት እና ዴሞክራሲያዊነት ፅንሰ ሐሳቦች መሠረት የሚያደርጉባቸው ፖለቲካዊ እሴቶች ‘እኩልነትና ሉዓላዊነት’ ናቸው። ልዩነታቸው ግልጽ የሚሆነው ‘የማን እኩልነት? የማንስ ሉዓላዊነት?’ የሚሉ ጥያቄዎች ሲነሱ ነው’ ይላሉ ዓለማየሁ።
ሰለሞንም ጉዳዩ በጥንቃቄ መታየት እንዳለበት ያሳስባሉ። ይሁንና ብሔርተኝነት በባሕሪው አግላይ መሆኑን እና ወገን ለይቶ መደራጀቱና ማቀንቀኑ ተገቢ ባይሆንም፥ መሬት ላይ ያለ እውነት መሆኑን ከመግለጽ ወደኋላ አላሉም። ዮናስም በበኩላቸው ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ በሌሎች ሰዎች ጥቃት የሚደርስባቸው መሆኑ እንዲሁም የመጤና የነባር ትርክቶች መነሾ መሠረቱን ብሔር ያደረገው የመንግሥታዊ ሥርዓት አወቃቀር መሆኑን ይናገራሉ።
ከመጪው ምርጫው በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ትኩረት አድርጎ ሊሠራባቸው ከሚገቡ ነገሮች በማለት ከተጠቀሱት አንዱ ጠርዝ የያዘ ብሔርተኝነት መሆኑን የአዲስ ማለዳ ተደራሲያን ያሳስባሉ። ሰለሞንም በበኩላቸው “ይህንን ጠርዝ የያዘ ብሔርተኝነት ተይዞ ነው ወይ ወደ ምርጫ የሚገባው?” ሲሉ ያጠይቃሉ።
3ኛ. ምጣኔ ሀብታዊ መነቃቃት መፍጠር
አዲስ ማለዳ በታኅሣሥ 27 እትሟ በኢትዮጵያ ትልቁ የገበያ ማዕከል በሆነው እና የምጣኔ ሀብቱ እንቅስቃሴ እንብርት በሆነው መርካቶ ባደረገችው ቅኝት እና እንዲሁም ባሰባሰበችው መረጃ መሠረት የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ መቀዛቀዝ መኖሩን ተረድታለች። መርካቶ ትልቁ የኢትዮጵያ የገበያ ማዕከል እንደመሆኑ መጠን በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ ማሳያ ሆኖ እንዲያገለግል በማለት ለማሳያነት በትንታኔዋ ተጠቅማበታለች።
በጉዳዩ ላይ የባለሙያ አስተያየታቸውን የሰጡን የምጣኔ ሀብት ባለሙያ መሰለ ወልደማርያም (ዶ/ር) “ምጣኔ ሀብቱን ነጥለን ብቻ መመልከት አይገባንም፤ ምክንያቱም ጉዳዩ ከብዙ ነገር ጋር ስለሚያያዝ። እነዚህ ተያያዥ ጉዳዮች ወይ የኢኮኖሚ መቀዛቀዙ መንስዔ አልያም መፍትሔ ሊሆኑ ይችላሉ” የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
“ምጣኔ ሀብት ከሰላም ጋር የተያያዘ ነው። ምጣኔ ሀብቱ እንዲነቃቃ ከተፈለገ ሰላም መጠበቅ አለበት” ያሉት መሰለ ለአንድ አገር ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ የደም ሥር ከሚባሉት መካከል ትራንስፖርት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አስታውሰዋል። “ወቅታዊ ከሆነው የኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በነጻነት መንቀሳቀስ አለመቻል፣ በአከፋፋዮች፣ ሻጭና ገዥ መካከል የሚኖረውን ትምምን ከማሳጣቱም ባሻገር የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴውን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀዛቀዝ አድርጎታል” በማለት መንግሥት አፋጣኝ እርምጃዎች መውሰድ ይገባዋል በማለት ያሳስባሉ።
ዓለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) የአዲስ ማለዳ እህት መጽሔት ‘ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው’ ላይ “ኢትዮጵያ ዳግም በመስቀለኛ መንገድ ላይ፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ተግዳሮቶች” በሚል ርዕስ ባስነበቡት መጣጥፍ የወጣቶች ሥራ አጥነትና ድኽነት የኢትዮጵያ ነባራዊ ችግር ብቻ ሳይሆኑ ዐቢይ ወደ ሥልጣን እንዲመጡ ካደረጓቸው ገፊ ምክንያቶች መካከል ከፊት መሥመር ላይ የሚቀመጡ መሆኑን ጠቅሰዋል። ከጠቀሷቸው አምስት አንኳር ተግዳሮቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት የጠቀሱት ይህንኑ ሲሆን መንግሥት በዚህ ላይ ከፍተኛ ሥራ መሥራት እንዳለበትም አሳስበዋል።
4ኛ. ተቋማዊ መሻሻልና ሕዝባዊ ውይይት
በኢትዮጵያ የቅድመ ምርጫ ዝግጅትን ወሳኝ ከሚያደርጉት ጉዳዮች መካከል እየታየ ያለው የፖለቲካ ምኅዳር መስፋት ዘላቂነት ኖሮት ይበልጥ እንዲጠናከር ከተፈለገ፥ ለውጡን አስተማማኝ፣ ሕጋዊና ተቋማዊ መሠረት እንዲኖረው ማድረግ እንደ ዋነኛ የመንግሥት ሥራ አድርገው የሚያስቡት የአዲስ ማለዳ ተደራስያን በርካቶች ናቸው።
የቅድመ ምርጫ መሻሻል/ተሐድሶ ከሚያስፈልጋቸው ተቋማት መካከል ፍርድ ቤቶች በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሾች ናቸው። ሌሎች ደግሞ የዴሞክራሲ ተቋማት በመባል የሚታወቁት እንደ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የዕምባ ጠባቂ ተቋም እና ሌሎችም በገለልተኝነት እና በብቃት መልሰው ተዋቅረው እና ተጠናክረው መውጣት ተጠቃሽ ከሚባሉት ወሳኝ መሻሽሎች መካከል እንደሚመደቡ የአዲስ ማለዳ አስተያየት ሰጪዎች አንዱ የትኩረት አቅጣጫ ነው።
በአዲስ ማለዳ የበይነ መረብ ጥያቄ መሠረት መንግሥት ሊሠራቸው ከሚገባቸው እና በአራተኝነት ጨምቀን ያስቀመጥናቸው ወሳኝ የቅድመ ምርጫ ሥራዎች መካከል ከኅብረተሰቡ ጋር መወያያ መድረኮችን ማመቻቸትም ይገኝበታል። ከተቋማዊ መልሶ ማዋቀሮች ጎን ለጎን ሕዝባዊ ጥያቄዎችን ለመረዳት እና በመልሶ ማዋቀሮቹ ላይ ሕዝባዊ ይሁንታን ለማግኘት አሳታፊነት ችላ ሊባል የማይገባው እንደሆነ ተደራስያኑ አመላክተዋል።
ሰለሞን ወሳኝ ወይም ወካይ ከሆኑ ‘የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሚደረግ ውይይት ቢቀድም፣ ከዚያም ተያያዥ የዴሞክራሲ ተቋማት ሥማቸው በሚመጥናቸው ጠንካራና ገለልተኛ ቁመና እንዲገኙ ቢደረግ መልካም ነው’ የሚል ምክራቸውን ለግሰዋል።
5ኛ. ለውጡ እንዳይደናቀፍ መሥራት
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ መምጣት አለበት ከሚሉ ወገኖች መካከል ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ጥሩ ጅምር ስለሆነ የሚያስፈልገው ከሰብዓዊ መብቶች አያያዝ፣ ሕገ መንግሥቱን ከመተግበር፣ ፌዴራላዊ ሥርዓቱን ሙሉ ለሙሉ መሬት ከማውረድ ጋር ተያያይዞ የሚነሱ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያስችል ጥገናዊ ለውጥ ነው የሚሉ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ሥርዓቱ ሙሉ ለሙሉ መቀየር አለበት የሚሉ ወገኖች አንዳንዶቹ የኢሕአዴግ መንግሥት ጨርሶ እንዲወገድ፣ ሌሎቹ ደግሞ በማንነት ላይ የተመሠረተው ፌዴራላዊ ስሥርዓት ጭምር ሊቀየር ይገባል ይላሉ። ለውጡ በምን መንገድ መምጣት አለበት የሚለው ላይም ልዩነቶች እንዳሉ ሁሉ ጨርሶውኑ ለውጡን የማይፈልጉ ብሎም ከማደናቀፍ ወደኋላ የማይሉ መኖራቸው በተደጋጋሚ ሲነገር ይሰማል።
በአዲስ ማለዳ የበይነ መረብ መጠይቅ መሠረት መንግሥት ሊሠራቸው ከሚገባቸው ሥራዎች በአምስተኝነት ደረጃ ብዙዎች ያስቀመጡት ወሳኝ ሥራ በቅድመ ምርጫው ወቅት ለውጡን ያደናቅፋሉ የተባሉ አንዳንድ የቀድሞ ባለሥልጣናት [አሉታዊ] ተፅዕኖ እንዲቀንስ በወንጀል የሚጠየቁት እና የሥርዓቱ ብልሹነት ተጠቃሚዎችን ለሕግ ተጠያቂነት ማቅረብ የሚለው አንዱ ነው።
ለዮናስ “ትልቁ ችግር ግን ተጋላጭነቱ ነው። ለእንደዚህ ዓይነት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች መጠቀሚያነት ወይም ሴራ የማይጋለጥ ማኅበረሰብ መፍጠር ላይ ነው ሊተኮር የሚገባው” ይላል። እንደ ዮናስ አባባል “መንግሥት ራሱን ሲያጠናክር፣ ማኅበራት ሲደራጁና ሲጠናከሩ የውጪውንም ሆነ የውስጡን ችግሮች ማብረድ ይቻላል” በሚል የመከራከሪያ ነጥቡን ያሰማል።
መደምደሚያ
ዮናስ ‘መንግሥት እንደ አገር አስተዳዳሪ በአንድ ጊዜ በርካታ ነገሮችን ማከናወን ይገባዋል’ ይላል። የአዲስ ማለዳ ተደራስያንም ሆኑ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ግለሰቦች ኢትዮጵያ እንደ አገር ለመቀጠል ሰላሟ መጠበቅ እንደሚያስፈልገው በአፅንዖት የገለጹ ሲሆን፥ ይህንንም ለማድረግ የሕግ ልዕልና መከበር ለድርድር መቅረብ እንደሌለበት ያሠምሩበታል። የቅድመ ምርጫ፣ የምርጫው ወቅት እንዲሁም የድኅረ ምርጫው አካሔዶች ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆኑ መንግሥት ከወዲሁ የቤት ሥራውን በመሥራት መንገዱን መጥረግ ይጠበቅበታል።
ከላይ የተዘረዙት አምስት የመንግሥት ተጠባቂ ቅድመ ምርጫ ዋና ዋና ሥራዎች አዲስ ማለዳ ባሰባሰበችው የበይነመረብ አስተያየት የተለዩ ሲሆኑ፥ ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች እና ጉዳዮችም ሊነሱ ይችላሉ። ስለሆነም፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ የጥናት ተቋማት እና የፖሊሲ አማካሪዎች፣ ሕዝባዊ አስተያየቶች እና ወቅታዊ ፍላጎቶችን በመምርመር ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸውን በመለየት መሥራት ይገባል በማለት እናሳስባለን።
Average Rating