www.maledatimes.com አዲስ አበባን እየፈተኑ ያሉ ወንጀሎች በስንታየሁ አባተ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

አዲስ አበባን እየፈተኑ ያሉ ወንጀሎች በስንታየሁ አባተ

By   /   January 19, 2019  /   Comments Off on አዲስ አበባን እየፈተኑ ያሉ ወንጀሎች በስንታየሁ አባተ

    Print       Email
0 0
Read Time:5 Minute, 58 Second

ቦታው ፒያሳ ሠዓሊ ግብረክርስቶስ ሰለሞን በላቸው የጥበባት ሱቅ አጠገብ ነው። አንዲት ትነሽ በላሜራ የተሰራችና ቢጫ በጥቁር የተቀባች ክፍል ትታያለች። ወደ ውስጥ ሲገቡም ክፍሏ ኹለት በኹለት ካሬ እንኳን እንደማትሞላ ይረዳሉ። በአንጻሩ ጠባብ የሚለው ቃል የማይገልጻት ክፍል አንድ ወንበርና አሮጌ ጠረጴዛ እንድትይዝ ተፈርዶባታል። ይህ አልበቃ ብሎም ለ12 ሰዎች በቢሮነት እንድታገለግል ኃላፊነት የተጣለባት ክፍል እንድትሆን ተገድዳለች። ዕለቱ ረቡዕ ጥር 1/2011 ሲሆን ሰዓቱ ከረፋዱ 4፡30 ሆኗል። ወደዚህች ክፍል ስንገባ አንድ ሰው ወንበር ላይ ተቀምጦ፣ አራት ሰዎች ደግሞ በአሮጌው ጠረጴዛ ጠርዝ ጠርዝ ላይ ሰፍረው አገኘን። ከእነዚህ መካከል አንዱ መልካሙ ተፈራ ናቸው። መልካሙ ዓመታትን ‹‹የፖሊስ አጋዥ›› በሚል የሚጠሩትና የአዲስ አበባ ነዋሪ በየወሩ ለአካባቢ ጸጥታ ጥበቃ አገልግሎት በሚል እየከፈለ ደመወዛቸውን ከሚደጉማቸው ፀጥታ አስከባሪዎች አንዱ ናቸው። ከላይ የጠቀስናት ክፍልም ያገኘናቸው አምስት ሰዎች ከቀሪ ሰባት አባላት ጋር ሆነው ስለ አካባቢው (ፒያሳ) የጸጥታ ሁኔታ ሪፖርት የሚለዋወጡባትና መረጃ የሚቀባበሉባት ቢሮ መሆኗ ነው።
እንደ መልካሙ ገለጻ በአዲስ አበባ በተለይም ፒያሳ የተለያዩ ዓይነት ወንጀሎች እየበረከቱ መጥተዋል። ወንጀሎቹ ከንብረት ቅሚያ እስከ ግድያ የሚደርሱም ናቸው። ‹‹መንግሥት በተለይ ፒያሳን ዞሮ አላያትም፤ ረስቷታል›› የሚሉት መልካሙ ፒያሳ ላይ በዚህ ወር ቀንሷል ከተባለ በትንሹ 50 የስርቆት ወንጀሎች እንደሚፈጸሙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የእሳቸውን ሐሳብ አብረን ያገኘናቸው አራት አጋሮቻቸውም ይጋሩታል። የስርቆት ወንጀልን በስንት ጣዕሙ የሚያስብል ድርጊት መደጋገሙ ደግሞ ለነመልካሙ ሥራ ከባድ ሆኗል። በቅርብ በሚባል ጊዜ ውስጥ ‹‹ፒያሳ የሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ ጓደኛው መሆኗን ተናግሮ አልጋ ይዞ ያደረ ሰው በነጋታው ልጅቱን ገድሏት ተገኝቷል፣ ሌላ ደግሞ ከዛሬ ኹለት ወር በዲህ ከገደሉ በኋላ በመኪና ጭነው አምጥተው ፒያሳ ላይ ጥለዋት የተገኘች ሴት አለች፣ ሌላ ልጨምርልህ ደብድቧት በመኪና አምጥቶ ሊጥላት ሲል ከነመኪናው የተያዘና ልጅቱም ከሞት የተረፈች አለች እዚሁ ፒያሳ›› ሲሉ የወንጀሉን ድርጊት ዓይነት በላይ በላዩ የሚያትቱት መልካሙ ፒያሳ ላይ ወንጀል መበርከቱን ያነሳሉ። ለዚህ ምክንያት የሚሉት ደግሞ የጎዳናና ሴተኛ አዳሪዎች መብዛትን ነው። የጎዳና አዳሪዎቹ ከተለያዩ ክልሎች እየመጡ ቀኑን ለመልሶ ማልማት ተብሎ በፈረሰውና እስካሁን ባለመልማቱ ዳዋ በልቶት በሚገኘው አሮጌው ቄራ እንደሚያሳልፉና ምሽት ወደ ተንሰራፉት የፒያሳ ጭፈራና ምሽት ቤቶች ደጃፍ እንደሚተሙ የሚናገሩት እነመልካሙ ሰው ሲጠጣና ሲጨፍር አምሽቶ ሌሊት ወደ ቤቱ በስካር መንፈስ ሲጓዝ እዚያው እያፈኑ እንደሚዘርፉት አልፎም አካላዊ ጥቃት እንደሚደርሱ በመጥቀስ ይወቅሳሉ።
ሴተኛ አዳሪዎችም ቢሆኑ እየተሻረኩ ከጭፈራ ቤት የሚወጡ ሰዎችን ይዘዋቸው እንዲያድሩ በማድረግ እንደሚያዘርፉ የገጠማቸውን በማንሳት የነገሩን የፖሊስ አጋዥ የጸጥታ አስከባሪዎቹ መንግሥት እንደ አሸን የፈሉትን የከተማዋን ምሽትና ዕርቃን ጭፈራ ቤቶች መቆጣጠር ባለመቻሉ የወንጀል ድርጊትና አይነቶቹም እየበዙ እንዲመጡ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ያምናሉ። ጭፈራ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ መዝጋትና ማገድ እንኳን ቢቀር እንዴት ገድብ እንዲኖራቸውና በተወሰነ ጊዜ ብቻ እንዲሰሩ ማድረግ ያቅታል ሲሉም ይጠይቃሉ።
ስለዚህ ጉዳይ የጠየቅናቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ የፖሊስ አጋዦቹ ችግሩን ውጪያዊ ከማድረግ ይልቅ ራሳቸው ፖሊስን ተክተው መሥራትና ጸጥታን ማስከበር እንደሚገባቸው ያነሳሉ። እነመልካሙ ግን ወንጀል እየረቀቀና እየሰፋ በመጣበት ጊዜ ፒያሳን በ12 ሰው 24 ሰዓት መቆጣጠርና ከወንጀል ነጻ ማድረግ እንደማይቻል ይሞግታሉ። ለአብነትም ‹‹እኛ እስከ ሌሊቱ 9፡00 ስንዞር እንቆይና ደክሞን አንድ ጥግ ላይ ስንቆም በሌላ ጥግ ወንጀል ተፈጽሞ ይገኛል›› ሲሉም ያስረዳሉ። ኮማንደሩ በበኩላቸው ቀን ላይ ደህና ሰው እየመሰሉ ሌሊት በእርቃን ጭፈራና ምሽት ቤቶች እየገቡ ከኢትዮጵያ ባሕል ውጭ የሆነ ተግባራትንና ወንጀልን የሚፈጽሙ ሰዎች ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ በመግለጽ ከንግድ እንዲሁም ከባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር እየለዩ እርምጃ የመውሰድ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል።
አዲስ አበባ የሰው ሕይወት በዋዛ የሚያልፍባት ከተማ?
በአዲስ አበባ እየተፈጸሙ ያሉ የግድያ ወንጀሎች እነመልካሙ ከገለጿቸውም በላይ መሆናቸውን የሚስረዱ አብነቶች አሉ። ሰለሞን አድማሱ በጫማ ንግድ ሥራ የተሰማሩ ጎልማሳ ሲሆኑ፣ ታኅሣሥ 4/2011 ከቅርብ ቤተሰባቸው የምትመደበው የአክስታቸው ልጅ እስካሁን በማን እንደተገደለች ሳይታወቅ ከመኖሪያ ቤቷ (ኮልፌ 18 ማዞሪያ ቀበሌ 06 አካባቢ) በግምት 600 ሜትር በሚርቅና ‹‹ኮምፕርኼንሲቭ›› በሚሰኝ ወንዝ ውስጥ ተጥላ መገኘቷን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የአክስታቸው ልጅ ከመኖሪያ ቤቷ ሐሙሰ ሌሊት ወጥታ ሳትመለስ መቅረቷንና አስከሬኗ ቅዳሜ የተጠቀሰው ወንዝ ውስጥ መገኘቱን የነገሩን ሰለሞን ገንዘብን ጨምሮ ስልክና ሌሎች ንብረቶችን የያዘው የእጅ ቦርሳዋ መኖሪያ ቤቷ ውስጥ መገኘቱንና ቤቱም እደተቆለፈ እንደነበር በመግለጽም ድርጊቱ ግራ አጋቢ መሆኑን ያነሳሉ። ሌሎች ሰዎችም እዚሁ አዲስ አበባ በተለያየ መንገድ ሕይወታቸውን አጥተው የመገኘታቸው ዜና በተለያየ ወቅት ይሰማል።
‹‹የሥርዓት አልበኝነት መንገሥ፣ ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት መጨመርና የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ ፣ የወንጀል ባህርይ እየረቀቀ መምጣት፣ በዲሽ አማካይነት ኢት ዮጵያ ውስጥ የሚሰራጩ የተለያዩ አገራት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በአንድ በኩል ወንጀልን አስተማሪ መሆናቸው፣ መንግሥት በአደንዛዥ ዕፅና ሱሰኝት ላይ በትኩረት አለመስራቱ በተለይም ሕፃናት የሱሰ ተጠቂ እየሆኑ ማደግ›› ሰለሞን በከተማዋ ወንጀል እንዲበዛ አድርገዋል ከሚሏቸው ምክንያቶች መካከል ናቸው።
ኮማንደር ፋሲካም ቢሆኑ የወንጀል ዓይነቱ መቀያየርና መለዋወጥ እንዳለ ሆኖ አገሪቱ ያለችበት የወቅቱ የፖለቲካ ሁኔታ ለወንጀል ድርጊት አንዱ ምክንያት እንደሆነም ያስረዳሉ። በተለይም በወንጀል ፈጻሚዎች ዘንድ ከክልሎች እየመጡ አዲስ አበባ ላይ ወንጀል መፈጸም እንዲሁም ክልሎች ላይም ወንጀል ሰርተው አዲሰ አበባን እንደመሸሸጊያ የመጠቀም ፍላጎት ማየሉንም ያነሳሉ። በከተማዋ ከወትሮው ጨምሮ የነበረው ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ የኮንትሮባድ እንቅስቃሴ፣ የሕገ ወጥና የሐሰተኛ ገንዘብ ዝውውርም ለወንጀል ድርጊቶች አጋዥ መሆኑን ያስረዳሉ።
በከተማዋ እየተፈጸሙ ነው ስለሚባሉት የግድያ ወንጀሎች የጠየቅናቸው ኮማንደሩ በግድያ ወንጀሎች እየተጠረጠሩ በሕግ ጥላ ስር የዋሉ እንዳሉ በመጥቀስ፣ ያልተያዙና በማጣራት ሒደት ላይ ያሉ ተጠርጣዎች ስለሚገኙም ኮሚሽኑ መረጃውን ለመገናኛ ብዙኃን በመግለጽ ተጠርጣዎችን ማሸሽና ማንቃት እንደማይፈልግ ገልጸዋል።
በተሸከርካሪ ነጥቆ መፈትለክ አዲሱ የወንጀል ‹‹ፋሽን››?
የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በሰኔ 2010 አንድ እኁድ ከላምበረት መናኸሪያ አደባባይ እስከ አቢሲኒያ ተብሎ የሚጠራው አጭር ርቀት ውስጥ ከረፋድ 3፡00 እስከ 6፡30 ባለው ጊዜ ሦስት ተበዳዮች በባለሦስት እግር ተሸርካሪዎች ‹የእንሸኛችሁ› ጥያቄ ገንዘብና ስልክ እንደተዘረፉ በመጥቀስ በአቅራቢው ለሚገኘው የላምበረትና አካባቢው ፖሊስ ጣቢያ ሲያመለክቱ አግኝቶ አነጋግሯቸው ነበር። ሦስቱም ተበዳዮች ባበለሦስት እግር ተሸከርካሪዎቹ የእንሸኛችሁ ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን ከትንሽ ጉዞ በኋላ ውረዱ ልንመለስ ነው በሚል አስወርደዋቸዋል። ‹‹የሆነ ነገርማ አስነክተውን ነበር›› የሚሉት ተበዳዮቹ ‹‹ካስነኩን ነገር ስንባንን ገንዘብና ስልካችን በኪሳችን የለም›› ሲሉም ይናገራሉ። በዕለቱ በፖሊስ ጣቢው የያገኘናቸው የፖሊስ አባላት እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት መለመዱን በመጥቀስ ፖሊስ ተደጋጋሚ ትምህርትና ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ኅብረተሰቡ እየተጠነቀቀ አለመሆኑን በትካዜ ሲነግሩንም ነበር።
ስለዚህ ጉዳይ የሚያስረዱት ኮማንደር ፋሲካ በሞተር ሳይክል፣ በባለሦስት እግርና ሌሎችም ተሽከርካሪዎች ከእግረኞች ላይ ንብረት ነጥቆ የማምለጥ እንዲሁም እንሸኛችሁ በማለት የመዝረፍ ወንጀል ድርጊት መኖሩን በመጥቀስ ባለፉት ስድስት ወራት በቦሌ ክፍለ ከተማ ብቻ 1928 ክስ ተመዝግቦ 1953 ተጠርጣሪዎች የተለዩ ሲሆን 1227ቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለአብነት በሚል ያነሳሉ። ከእነዚህ ውስጥ 802ቱ በኅብረተሰቡ እጅ ከፍንጅ የተያዙ ሲሆን ቀሪዎቹ በፖሊስ አባላት ስለመያዛቸውም አክለዋል። ኅብረተሰቡ ከያዛቸው ተጠርጣዎች ጋር ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚገመት ንብረት (ገንዘብን ጨምሮ) በኤግዚቢትነት መያዙንም ነግረውናል።
እንደ ኮማንደሩ ማብራሪያ ባለፉት ስድስት ወራት በጦር መሣሪያ ዘረፋ፣ በውንብድና ወንጀል፣ በመኪና ስርቆት፣ በመሣሪያ አስፈራርቶ መዝረፍ (በቅርቡ በቦሌ ሰሚት አካባቢ የተፈጸመውን በመኪናና ጦር መሣሪያ ታግዞ የመዝረፍ ሙከራ ማንሳት ይቻላል) ወንጀሎች ኮሚሽኑ ባደረገው ጥናት 21 ተጠርጣዎችን ይዟል። የዋስትና መብት ተከልክለው በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ ካሉት 21ዱ ተጠርጣዎች ጋርም 9 ተሽከርካሪዎች፣ 6 ሽጉጦች፣ 4 ተንቀሳቃሽ ስልኮችና 1 ፕላዝማ መያዙን ኮማንደሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ባለፈው ስድስት ወር ከብሔራዊ መረጃና ደኅንንት አገልግሎት ጋር በጥምረት በተወሰዱ እርምጃዎች ስምንት ሚሊዮን ብር፣ 88 ሺህ የአሜሪካን ዶላር፣ ከ12 ሺህ በላይ የእንግሊዝ ፓወንድ እና ሌሎችም ገንዘቦች መያዛቸውን ያነሱት የሥራ ኃላፊው ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውሩ ከፍ ያለ እንደነበር አስረድተዋል።
ይሁንና ሁሉም ተሸከርካሪዎች ወንጀል መፈጸሚያ ሆነዋል ተብሎ እንደማይወሰድ የሚገልጹት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አጥፊዎችን እየተከታተሉ እንደያዙና እስካሁንም የተሽከርካሪዎቹ ባለቤት ነኝ ብሎ የቀረበላቸው ግለሰብ ያላገኙ ተሽከርካሪዎች ተይዘው እንደሚገኙም አክለዋል።
የወንጀል ቁጥር በአዲስ አበባ ወዴት?
የወንጀል ድርጊት ሲሳይ የሆኑ ከተማዋ ነዋሪዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ወንጀል ስለመስፋፋቱ ሲናገሩ ይሰማል። ፖሊሰ ኮሚሽኑ ግን የወንጀል ድርጊቱ በቁጥርም ይሁን በዓይነት ቀንሷል ይላል። ኅብረተሰቡ ጨምሯል ቢል ተሳስቷል እንደማይባል በመጥቀስ ኮሚሽኑ የሚናገረው ሪፖርት ተደርጎለት የመዘገባቸውን የወንጀል ድርጊቶች ድምር በመሆኑ ከአምናውም ይሁን ካለፈው የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ጋር ሲነጻጸር ቁጥርና ዓይነቱ በአንጻራዊነት መቀነሱን የሚያመለክት ሆኖ መገኘቱን ኮማንደሩ አስረድተዋል። ይሁንና ተበዳዮች ለአካባቢያቸው ፖሊስ አመልክተው ወንጀለኞች በሕግ እንዲፈለጉ የማድረጉን ሥራ ሪፖርት በማድረግ መተባበር እደሚጠበቅባቸውም ያስገነዝባሉ።
የአሜሪካ ኤምባሲ ‹‹ Ethiopia 2018 Crime & Safety Report ›› በሚል ርዕስ በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያትተው ከሆነ በአዲስ አበባ የስርቆትና ንጥቂያ ወንጀሎች በከፍተኛ መጠን የሚጠቀሱ ናቸው። ሪፖርቱ በቡድን በሚንቀሳቀሱ ወጣቶች ሳይቀር የሚፈጸመው ዝርፊያና ስርቆት በተሽከርካሪዎች የሚታጀብ እስከ መሆን መድረሱን በመግለጽም ሰለባዎቹ የሌላ አገራት ዜጎችም ጭምር መሆናቸውን ያስገነዝብና፣ ዜጎቹ እንዲጠነቀቁለት ይመክራል። በውጭ አገራት ዜጎች ላይ ሳይቀር ጾታዊ ጥቃትና አስገድዶ መድፈርን ያሉ ወንጀሎች እንደሚያጋጥሙ በመጥቀስም በኢትዮጵያ ባሕልና ሕግ መሰረት ውጉዝ የሚባለው ግብረሰዶማዊነት ሳይቀር የሚፈጸምባት ከተማ ከሆነች ውላ ማደሯን ያነሳል።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 6 years ago on January 19, 2019
  • By:
  • Last Modified: January 19, 2019 @ 11:28 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar