www.maledatimes.com የነዳጅ ኩባንያዎች በዱቤ የወሰዱትን በቢሊዮን የሚቆጠር ዕዳ እየከፈሉ አለመሆኑ ተገለጸ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የነዳጅ ኩባንያዎች በዱቤ የወሰዱትን በቢሊዮን የሚቆጠር ዕዳ እየከፈሉ አለመሆኑ ተገለጸ

By   /   January 20, 2019  /   Comments Off on የነዳጅ ኩባንያዎች በዱቤ የወሰዱትን በቢሊዮን የሚቆጠር ዕዳ እየከፈሉ አለመሆኑ ተገለጸ

    Print       Email
0 0
Read Time:2 Minute, 28 Second

ነዳጅ ድርጅት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጋር እየተነጋገርኩ ነው ብሏል

ለዓመታት ነዳጅ በዱቤ እየተረከቡ ሲያከፋፍሉ የቆዩ የነዳጅ ኩባንያዎች በዱቤ የወሰዱትን ነዳጅ ከሸጡ በኋላ ገንዘቡን እየመለሱ ባለመሆኑ፣ በቢሊዮን የሚቆጠር የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ለመሰብሰብ ከፍተኛ ችግር ማጋጠሙ ተመለከተ፡፡

ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ድርጅቱ ለግል ነዳጅ አከፋፋይ ኩባያዎች ነዳጅ በዱቤ ሲሸጥ ቆይቷል፡፡ በዚህ መሠረትም በገበያ ውስጥ ያሉ ነዳጅ አከፋፋይ ድርጅቶች በውላቸው መሠረት በዱቤ የሚወስዱትን ነዳጅ በወቅቱ እየከፈሉ ሥራቸውን ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እንዳለው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ኩባንያዎቹ ያለባቸውን ዕዳ በወቅቱ ባለመክፈላቸው ምክንያት በድርጅቱ ፋይናንስ ላይ ከፍተኛ ጫና እያስከተለ ከመምጣቱም በላይ፣ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት የሆነውን ገንዘብ ለመሰብሰብ ከፍተኛ ችግር ሆኗል፡፡

ድርጅቱ ይህ የተለመደ አሠራር ችግር እየፈጠረ ነው በሚል ምክንያት፣ ጫናውን ለመቋቋምና ሳይሰበሰብ የቆየውን የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት በወቅቱ ለመሰብሰብ፣ ኩባንያዎች ከሚያስይዙት ዋስትና በላይ ነዳጅ እንዳይሸጥላቸው ማድረግ ብቸኛ አማራጭ ሆኖ እንዳገኘው አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ነዳጅ እያቀረቡ የሚገኙ ኩባንያዎች 26 ደርሰዋል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች እንዲያሲዙ የሚጠበቀው 16 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህን ገንዘብ ካስያዙ በኋላ በመቶ ሚሊዮን ብሮች የሚቆጠር ነዳጅ በዱቤ እየወሰዱ ያከፋፍላሉ፡፡

አንድ የነዳጅ ተሽከርካሪ ጂቡቲ ተጉዞ አንድ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ነዳጅ ቢያመጣ፣ በወር 30 ተሽከርካሪዎች ቢያጓጉዝ የሰላሳ ሚሊዮን ብር ዱቤ አገልግሎት ያገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት ትልልቆቹ ነዳጅ አከፋፋዮች እያንዳንዳቸው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ፣ አዳዲሶቹ ደግሞ እስከ 500 ሚሊዮን ብር ድረስ ዕዳ እንዳለባቸው የድርጅቱ መረጃ ያሳያል፡፡

ይህ ችግር ጎልቶ የወጣው በቅርብ ገበያውን የተቀላቀለው ባሮ ኦይል ኢትዮጵያ የዱቤ አገልግሎት ከተከለከለ በኋላ ነው፡፡  

ባሮ ኦይል መስከረም 10 ቀን 2011 ዓ.ም. የነዳጅ ዘርፉን የተቀላቀለ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዴፖና ስድስት ማደያዎችን ከፍቶ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

ባሮ ኦይል ታኅሳስ 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅቱ በጻፈው ደብዳቤ፣ ሌሎች ነዳጅ ኩባንያዎች ለዋስትና ካስያዙት 16 ሚሊዮን ብር የበለጠ 24 ሚሊዮን ብር እንዲያሲዝ ከተደረገ በኋላ፣ ለሌሎቹ የተፈቀደው የዱቤ አሠራር መከልከሉን ተቃውሟል፡፡

ኩባንያው በጻፈው ደብዳቤ ነዳጅ አቅራቢው ድርጅት የወሰደው ዕርምጃ፣ ሁሉም በሕግ ፊት እኩል ነው የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ በግልጽ ይፃረራል ብሏል፡፡

‹‹መንግሥት በብቸኝነት በሚያቀርበው አገልግሎት ሁሉም በእኩልነት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያደርግ ፖሊሲና ከአድልኦ የፀዳ ሕግ ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በኩባንያችን ላይ ብቻ የተጣለው የውል ገደብ ፍትሐዊነት የሚጎድለው በመሆኑ መነሳት አለበት፤›› ሲል ባሮ ኦይል ኢትዮጵያ በጻፈው ደብዳቤ ፍትሕ ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባሮ ኦይል ያቀረበው የፍትሐዊነት ጥያቄ ልክ ነው፡፡

አቶ ታደሰ እንዳሉት፣ አዳዲስ የመጡት የነዳጅ ኩባያዎች የዱቤ አገልግሎቱን በአግባቡ አልተጠቀሙበትም፡፡ በወቅቱ እየከፈሉ ባለመሆኑ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት ለመሰብሰብ አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

የነዳጅ ማደያዎች ለሥራ ብቁ መሆናቸውን በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የብቃት ማረጋገጫ፣ እንዲሁም ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ፈቃድ ካመጡ ድርጅቱ አገልግሎቱን ይሰጣል በማለት የገለጹት አቶ ታደሰ፣ ‹‹ከነባሮቹ ይልቅ አዳዲሶቹ በግልጽነት ባለመሥራታቸው ተቸግረናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ጉዳዩን በምን መንገድ እንደምንይዘው ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጋር መነጋገር ጀምረናል፤›› ሲሉ አቶ ታደሰ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ 26 የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎችና 800 ሺሕ የነዳጅ ማደያዎች ይገኛሉ፡፡ ከማደያዎቹ ውስጥ 100 የሚሆኑት በአዲስ አበባ ከተማ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ 900 ሺሕ ያህል ተሽከርካሪዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 400 ሺሕ የሚሆኑት አዲስ አበባ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በዓመት ለተሽከርካሪዎችና ለተለያዩ አገልግሎቶች ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ወደ አገር የሚገባ ሲሆን፣ ይህንን ነዳጅ ለመግዛት ከ2.8 ቢሊዮን እስከ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ድረስ መንግሥት ወጪ እንደሚያደርግ ይታወቃል፡፡       FacebookTwitterLinkedInShare

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 6 years ago on January 20, 2019
  • By:
  • Last Modified: January 20, 2019 @ 1:16 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar