በግንባታ ሥራ የሚሳተፉ ተቋራጮች ምዘና ይካሄድባቸዋል ተብሏል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እስካሁን ሲያጋጥሙ የቆዩትን የመሠረተ ልማት ግንባታዎች መጓተት ለማስቀረት የሚረዳውን አሠራር ይፋ በማድረግ፣ ከዚህ ቀደም በቦርድ ይመሩ የነበሩ የቤቶች ልማት፣ የመንገድና የግንባታ ተቋማትን በከንቲባ ጽሕፈት ቤት ሥር እንዲመሩ መወሰኑን ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) አስታወቁ፡፡
በቤቶች፣ በውኃና በመንገድ ግንባታ መስክ ከተሰማሩ ተቋራጮችና አማካሪዎች ጋር በተካሄዱ ውይይቶች ወቅት አቶ ታከለ ይፋ እንዳደረጉት፣ እነዚህ ተቋማት ሲመሩበት የነበረው አሠራር በመንግሥትና በሕዝብ ሀብት ላይ ኪሳራ እያስከተለ ቆይቷል፡፡ ሐሙስ ጥር 9 ቀን 2011 ዓ.ም. የመንገድ ተቋራጮችና አማካሪዎች በተጠሩበት ስብሰባ ወቅት ከንቲባው እንደገለጹት፣ ካሁን በኋላ ባለው አሠራር በተለይ የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን በከንቲባ ጽሕፈት ቤት ሥር ይመራሉ፡፡
በእነዚህ ተቋማት ክትትል የሚገነቡ መሠረተ ልማቶችም በተዋረድ እስከ ክፍለ ከተማ ባለው መዋቅር ድረስ ተጠያቂ የሚደረጉበት፣ ከታች ያሉት የአስተዳደር አካላት ወደ ላይ ጥያቄ በማቅረብ ክትትል የሚያደርጉበት አሠራር እንደሚዘረጋ ምክትል ከንቲባው አስረድተዋል፡፡ የፕሮጀክት ኮንትራት አስተዳደርና የጨረታ ግዥ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ እንደሚቀየርም አስታውቀዋል፡፡
ከከተማው በጀት እስከ 60 በመቶ የሚያገኙት እነዚህ ተቋማት፣ ሲከተሉት የቆየው የጨረታ ሒደትም ለውጥ ይደረግበታል ተብሏል፡፡ ‹‹ግልጽ ጨረታ እየተባለ›› ግልጽነት የጎደለው አሠራር በመስፈኑ የሕዝብ ገንዘብ ሲባክን ቆይቷል ያሉት አቶ ታከለ፣ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ሳይጠናቀቅ የሚጓተት ፕሮጀክት ከመነሻው የተቀመጠለትን በጀት በከፍተኛ መጠን እያናረ የግብር ከፋዮች ገንዘብ ለተቋራጭ ድርጅቶች ያላግባብ የሚውልበት መንገድ ይቀየራል ብለዋል፡፡
በዚህ መሠረት ከዚህ ቀደም በጨረታ የሚሳተፉ ኩባንያዎችና የሚሳተፉበት አግባብ እንደሚፈተሽ፣ የተሰጣቸውን ፕሮጀክት በአግባቡ የማይፈጽሙ ተቋራጮችና አማካሪዎችም ተለይተው እንደሚወጡና በሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ እንዳይሳተፉ የሚታገዱባቸው አሠራሮችን ጨምሮ፣ መንግሥት ብቃቱና ጥራቱ፣ እንዲሁም በተመደበው በጀት መሠረት በወቅቱ ገንብተው የሚያስረክቡ ድርጅቶችን እየመረጠ ግንባታዎችን እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል፡፡
‹‹ችግር ያለባቸው ተቋራጮች ይመዘገባሉ፡፡ በአግባቡ ከተመዘኑት ውስጥ የትኛው አቅም አለው እያልን እንለያለን፡፡ የጨረታው አሠራር ይቀየራል፡፡ የግንባታ ሒደቱም በየፕሮጀክቱ ክንውን ይገመገማል፤›› ብለዋል፡፡ በግንባታው መስክ 30 አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ከንቲባው በጨረፍታ ቢጠቅሱም፣ ለፕሮጀክቶቹ የተመደበውን ወጪ ለማወቅ ሪፖርተር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡
Average Rating