የክልሎች አስተያየት አልተጠየቀበትም የሚል ተቃውሞ የተሰነዘረበት የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ በአብላጫ ድምፅ ፀደቀ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሙስ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ላይ የቀረበው የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ ከምክር ቤቱ አባላት ትችቶች የተሰነዘረበት ሲሆን፣ አዋጁን በዝርዝር ተመልክቶ የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርብ ኃላፊነት የተሰጠው የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የክልል መንግሥታትን ማወያየት ሲገባው ይኼንን አላደረገም ተብሎ ተተችቷል።
አዋጁ በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች በኢኮኖሚ ዘርፎች ተሰማርተው ገቢ ማመንጨት እንዲችሉ፣ በሚኖሩበት አካባቢ መሬት እንዲያገኙና በመስኖ የግብርና ልማት እንዲሳተፉ ዕድል የሚሰጥ ነው። በተጨማሪም ቋሚ ንብረት የማፍራት፣ የመሸጥ፣ የመለወጥና ፍትሕ የማግኘት መብት የሚሰጥ ነው።
የተገለጹት መብቶች የክልል አስተዳደሮችን የሚመለከትና መሬት የማስተዳደር መብትም የክልሎች በመሆኑ፣ እንዲሁም ስደተኞቹ የሚጠለሉት በተለያዩ ክልሎች ስለሆነ የክልል መንግሥታት አስተያየት ሊጠየቅ ይገባ እንደነበር በማንሳት አንድ የምክር ቤቱ አባል ተከራክረዋል።
የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ፎዚያ አሚን የተቸገሩ ስደተኞችን ተቀብሎ ማስተናገድ የአገራችንን ስም ከፍ ከማድረግ አንፃር የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረው፣ በዚህ ምክንያት የሚገኝ ብድርና ድጋፍ ኢትዮጵያ ሃምሳ በመቶ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋትና ሕግ ሳይወጣለትም እስካሁን በተግባር እየተሠራበት ያለ ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።
ክልሎችን ከማወያየት አንፃር ምክር ቤቱ የሁሉም ክልሎች ተወካዮች ያሉበት እንደመሆኑ የክልሎችን ፍላጎት በዚሁ ተፈትሿል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸው፣ በተጨማሪም ሁለት ጊዜ ሕዝቡን በይፋ በሚዲያ ጠርተው ያወያዩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የመሬትና የመስኖ እርሻ አጠቃቀምን በሚመለከትም በየሰባት ዓመቱ የሚታይና የሚታደስ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አዋጁ በሥራ ላይ የሚገኘውን የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ አሻሽሎ እንደ አዲስ የሚደነግግ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች ከመጠለያ ካምፖች ውጪ ለመኖር እንዲችሉ፣ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር ነፃነትን የሚያጎናፅፍ ድንጋጌ ይዟል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የባንክ ሒሳብ የመክፈት፣ መንጃ ፈቃድና መታወቂያ ማውጣት እንዲችሉ መብት የሚሰጥ ድንጋጌ የያዘ ሲሆን፣ ከ20 ዓመት በላይ በኢትዮጵያ የኖሩ ስደተኞች አግባብ ባለው ሕግ የኢትዮጵያን ዜግነት እንዲያገኙም በሰነዱ ተካቷል፡፡
የሥራ ዕድልን በተመለከተም ለውጭ አገር ዜጎች ከተሰጡ መብቶች እጅግ የተሻለውን ያህል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መብት የሚሰጥ ድንጋጌ በአዋጁ ተካቷል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተለየ ሁኔታ ለስደተኞች የሚፈቀዱ የሥራ ዘርፎች ተለይተዋል፡፡ እርሻ፣ ኢንዱስትሪ፣ አነስተኛና ጥቃቅን የዕደ ጥበባትና የንግድ ዘርፎች ተዘርዝረዋል፡፡
ንብረት የማፍራትና የማስተላለፍ፣ የአዕምሮ ውጤቶች ጥበቃ እንዲያገኙ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያውያንና በስደተኞች መካከል መድልኦ እንደማይደረግ የሕግ ሰነዱ ይዘረዝራል፡፡ መንግሥት ይኼንን የሚፈቅድ ከሆነ ለኢትዮጵያውያን ሥራ አጦች የጋራ ተጠቃሚነትን የሚውል የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ዕርዳታ እንደሚገኝ የሰነዱ ማብራርያ ይገልጻል፡፡
ከእነዚህም መካከል ለ100 ሺሕ ሰዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በተመሳሳይ 100 ሺሕ ሰዎችን በመስኖ የታገዘ የእርሻ ልማት እንዲያለሙ እንደሚያስችል እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ለዚህም ሲባል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የዓለም ባንክ፣ የአውሮፓ ኅብረትና ሌሎች አገሮች የኢንቨስትመንት ካፒታል በዕርዳታ ለመስጠት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት ማድረጋቸውን ያስረዳል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ሲጠናቀቁ ከሚፈጠረው ለ100 ሺሕ ሰዎች የሚሆን የሥራ ዕድል ውስጥ 70 በመቶ (70 ሺሕ) ለኢትዮጵያውያን የሚደለደል ሲሆን፣ ቀሪው 30 በመቶ (30 ሺሕ) ለስደተኞች እንደሚሆን ማብራርያው ይገልጻል፡፡
በተመሳሳይ በእርሻ ልማት የሥራ ዕድል ለመፍጠር 10 ሺሕ ሔክታር መሬት የተዘጋጀ መሆኑን፣ በዚህም ከሚፈጠረው 100 ሺሕ የሥራ ዕድል 70 በመቶ ለኢትዮጵያውያን ቀሪውን 30 በመቶ ደግሞ ለስደተኞች እንደሚደለድል ይገልጻል፡፡
በመሆኑም በሁለቱ የሥራ ዘርፍች ከሚፈጠረው የሥራ ዕድል ውስጥ 60 ሺሕ ስደተኞች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
አዋጁ በሦስት ተቃውሞና በአንድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡
Average Rating