ታኅሣሥ 2011
- በመጀመሪያ ራሴን ላስተዋውቅ፡ የተወለድሁት አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አካባቢ ነው፤ ዘመኑም 1922 ዓ. ም. ነው፤ የአገዛዝ የመንግሥት ለውጥ የተደረገበት ዘመን ነበር፤ አባቴ አቶ ወልደ ማርያም እንዳለ (ከአንኮበር፣ ሸዋ፤) ፣ እናቴ ወይዘሮ ይመኙሻል ዘውዴ (ከየጁ፣ ወሎ፤) ናቸው፤ ሚስቴ የነበረችው በአባትዋ ሸዋ (መርሐቤቴ) በእናትዋ ትግራይ (አድዋ፣ እንትጮ፤) ነች፡፡
በሥራዬ አብዛኛው ዕድሜዬ ያለፈው በአስተማሪነት ነው፤ መጀመሪያ በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት፣ በኋላ በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ ከዚያ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሳስተምር ነበር፤ በአጼ ኃይለ ሥላሴ አገዛዝ በፓርላማ ተመርጬ ለአንድ ዓመት ያህል በመርማሪ ኮሚስዮን ሠርቻለሁ፤ ጡረታ ከወጣሁ በኋላ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤን አቋቁሜ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ስለሰብአዊ መብቶች ለማስተማር ሞክሬአለሁ፤ የመጨረሻ ሥራ የምለው በቅንጅት የፖሊቲካ ፓርቲ አባልነት ነው፤ ከዚያ በኋላ በመጻፍና በማሳተም ቆይቻለሁ፤
2 ከትግራይ ጋር የተዋወቅሁት በ1951 ነው፤ ክፉ ዘመን ነበረ፤ ገና ዕድሜዬ ሠላሳ ሳይሞላ በትግራይ የተመለከትሁት ስቃይና መከራ ልቤን ሰንጥቆ የገባ ነበር፤ በአገሬ በኢትዮጵያ፣ በወገኖቼ በኢተትዮጵያውያን ላይ የተጫነውን አገዛዝና ግፈኛነነቱን የተረዳሁበትና ከማናቸውም አገዛዛ ጋር በተቃውሞ ለመቆም የወሰንሁበት ዓመት ነበር፤ ያን ሁኔታ አይቼ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለቀስሁበት ዓመት ነበር፤ በችጋር ለተጠቃው ሰብአ ትግራይ መፍትሔ ልዑል ራስ ሥዩም ለትግራይ አውራጃዎች በሙሉ በየቀኑ ጸሎት እንዲደረግ አዝዘው ነበር፤ አገዛዙ ከጊዜው የዓለም ሁኔታ ጋር መራራቁን የተገነዘብሁበት ዓመት ነበር፤ ሁለት የትምህርት ቤት ጓደኞቼን (ነፍሱን ይማረውና) መንገሻ ገብረ ሕይወትንና ኃይለ ሥላሴ በላይን አግኝቻቸው ያየሁትን አ.ይተዋል፤ በዚያን ጊዜ ትግራይ አገሬ ነበር፤ የሰብአ ትግራይ ስቃይ የኔም ስቃይ ነበር፤ በሰብአ ትግራይ ላይ የደረሰው ችጋር የኢትዮጵያ ነበር፤ ስለዚህ የኔም ችጋር ሆኖ ተሰማኝ፤ በሕይወቴ ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ በመሳፍንትና መኳንንት ቤት እየዞርሁ ደጅ ጠናሁ፤ በዚያን ጊዜ የአዲስ አበባ ከንቲባ የነበሩት ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ ‹‹እኔን ትግሬ ስለሆነ ነው ይሉኛልና ተወኝ፤›› ብለውኛል፡፡
- ከሀያ አምስትና ከሠላሳ ዓመታት በኋላ በጉዳዩ ላይ ሁለት መጽሐፎችን (Rural Vulnerability to Famine in Ethiopia: 1958—1977. Suffering Under God s Environment: A Vertical Study of the Predicament of Peasants in North-Central Ethiopia) እስክጽፍ ድረስ ችግሩ ከአእምሮዬም ከልቤም አልወጣም ነበር፤ ትግራይን ከአክሱም ጽዮንና ከያሬድ ለይቼ አላይም፤ ኤርትራን ከደብረ ቢዘንና ከዘርአይ ደረስ ለይቼ አላይም፤ የኔ ኢትዮጵያዊነት የሚፈልቀው ከነዚህ ምንጮች ነው፤አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ወያኔና ሻቢያ እነዚህን ምንጮች ለማደፍረስ ሞክረዋል፤ በተለይ በአለፉት አርባ ዓመታት ኢትዮጵያ በገዛ ልጆችዋ በጣም ደምታለች፤ ጥቂት ልጆችዋ በባዐድ ፍልስፍና ተመርዘው ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ለመመረዝ ተደራጅተው ፍቅርን በጦር መሣሪያ፣ ኢትዮጵያዊነትን በዘር ለውጠው የታሪክ ቅርሳችንን ሊያሳጡን ሞክረው ነበር፡፡
- የምንጮቹን ጥራት ለመጠበቅ አዲስ ትግል ተጀምሯል፤ በፍቅርና ይቅር ለእግዚአብሄር በመባባል በሰላማዊ መንገድ ኢትዮጵያን ለማደስ አዲስ ትውልድ ተነሥቷል፤ ይህ ትውልድ ድምጽና የፖሊቲካ ኃይል ያገኘው ወያኔ ከሥልጣን ከመገለሉ በኋላ ነው፤ ከሥልጣን (ከአድራጊ-ፈጣሪነት) የወረዱት የወያኔ ባለሥልጣኖች የትግራይ ተወላጆች መሆናቸው በአለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያውያን (ሰብአ ትግራይን ጨምሮ) ላይ የደረሰውን ግፍ ሰብአ ትግራይ ሰርዘውታል ማለት ነው ወይስ የተፈጸመው ግፍ በጎሣ ሚዛን ታይቶ ተናቀ የሚሰረዝም የሚናቅም አይደለም፤ በዚያው በትግራይ ውስጥ ብዙ ግፍ እንደተፈጸመ የሚመሰክሩ የትግራይ ተወላጆች ሞልተዋል፡፡
- ግፍንና ግፈኛን ለማውገዝ የግፍ ተቀባዩ ወገን መሆን አስፈላጊ አይደለም፤ አእምሮና ኅሊና ያለው ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው፤ ዛሬ የሰው ልጅ እንኳን ለሰውና ለእንስሳም በጣም የሚቀረቆርበትና ዘብ የሚያቆምበት ጊዜ ደርሰናል፤ ሰብአ ትግራይ እንዴት ከዚህ ውጭ ይሆናሉ በአለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት ውስጥ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ግፍ እንደሚካሄድ ሰብአ ትግራይ አላዩም አልሰሙም ለማለት ይቸግራል፤ በሌላ በኩል በወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ሰብአ ትግራይ በሙሉ ተጠቃሚዎች ነበሩ የሚል ሐሜት አለ፤ ስለዚህም የግፍ አሳላፊዎች እንጂ የግፍ ተቀባዮች አልነበሩም የሚባለው ልክ ነው ልንል ነው፤ በበኩሌ ይህንን የመጨረሻውን አስተያየት ለመቀበል በጣም ያዳግተኛል፤ ለማንኛውም ሰብአ ትግራይ በቅርቡ እውነተኛ መልሱን እንደሚሰጡን እተማመናለሁ፡፤
- የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባለሥልጣኖች ፍርድ ቤት የመቅረብ መብታቸው ሳይጠበቅላቸው በአስከፊ ሁኔታ እየተጨፈጨፉ አልቀዋል፤ የደርግ አባሎች በፈጸሙት ግፍ ተከስሰውና ተከራክረው ተፈረደባቸው፤ በምሕረት ወጡ፤ አሁን ደግሞ የወያኔ ባለሥልጣኖች ተራ ሆነ፤ የወያኔ ተራ ሲደረስ ትግሬነታቸው ተነሣ፤ ሁሉም የትግራይ ተወላጆች መሆናቸው ከተከሰሱበት ወንጀል አንዱ ይመስለኛል፤ ወያኔ የሥልጣን መሰላሉን ለመውጣት ትግሬነትን መሣሪያ አድርጎ እንደተጠቀመበት እውነት ነው፤ አሁን መውረድ ግዴታ ሲሆን የወጡበትን መሰላል መካድ አይቻልም፤ የወያኔ ባለሥልጣኖች ከአለፉት ሁለት አገዛዞች የሚለዩት በወያኔ ዘረኛነት ብቻ ይመስለኛል፤ ስለዚህም ዛሬ ለፍርድ የሚፈለጉት ትግሬዎች በመሆናቸው አይደለም፤ የሚፈለጉት ትግሬነትን የዘረኛነት ሥልጣን መሠረት አድርገው ፈጽመዋል በተባሉት ወንጀሎች ነው፤ ትግሬነት ከወያኔ ወንጀል ውጭ ነው፤ ፍርዱ በሥርዓት ከተካሄደ ከወያኔ ባለሥልጣኖች ጋር በወንጀል ተያይዘው የሚቆሙ የሌሎች ጎሣዎች አባሎች ይኖራሉ፤ የነሱ ድርሻ በፍርድ ካልታየ የዘር አድልዎ ተፈጸመ ለማለት እንችላለን፤ ይህ አድልዎ ሐቅ ቢሆንም የወያኔን ባለሥልኖች ወንጀል ወደትግሬነት አይለውጠውም፤ ስለማይለውጠውም አይሰርዘውም፤ ወንጀለኛነነት ከትግሬነት ተለይቶ ብቻውን ይቆማል፤
- ሰብአ ትግራይ አክሱም ጽዮንን አቅፎ የወንጀል ምሽግ መሆን አይችልም፤ ሰብአ ትግራይ አክሱም ጽዮን የዕርቅና ይቅር የመባባል መንፈሳዊ ኃይል እንጂ የወንጀለኞች ምሽግ እንደማትሆን ያውቃሉ፤ በኢትዮጵያውያን መሀከል አለመግባባት ሲከሰት በሰላማዊ መንገድ በንግግርና በክርክር፣ በውይይትና በምክክር መፍትሔ ማግኘት ከከፍተኛ ጥፋትና ደም መፋሰስ እንደሚያድን ይታመናል፤ ስለዚህም የሰብአ ትግራይ ምርጫ ከወንጀል ተነጥሎ ከአክሱም ጽዮን ጋር መቆም ነው፡፡
Average Rating