የሽንት ቧንቧ ችግር (Hypospedia) ሕክምና ለማግኘት ገብቶ ቀዶ ሕክምና ከተደረገለት በኋላ፣ ሕክምና በተደረገበት ጠረጴዛ ላይ እያለ ወደ ሳንባው የተላከ መተንፈሻን ቱቦ በመንቀል ሕፃኑ ሙሉ ለሙሉ ፓራላይዝድ (መንቀሳቀስ እንዳይችል) አድርጓል የተባለው የኮሪያ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ የ23.6 ሚሊዮን ብር የፍትሐ ብሔር ክስ ተመሠረተበት፡፡
ጉዳት የደረሰበት ሕፃን እዩኤል ፍሬው የሁለት ዓመት ከአራት ወር ሕፃን መሆኑንና ወደ ሆስፒታሉ ሄዶ የነበረው ለግርዛትና የሽንት መውጫ ቀዳዳ ከብልቱ አናት (ጫፍ) ትንሽ ወረድ ብሎ በመገኘቱ በቀላል ቀዶ ጥገና ለማስተካከል ቀጠሮ ተይዞለት እንደነበር፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ቀጥታ ክስ ፍትሐ ብሔር ችሎት የቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡
የሕፃኑ ወላጆች አቶ ፍሬው በቀለና እናቱ ወ/ሮ ምሕረት ጌታቸው ነዋሪነታቸው በደቡብ ክልል ሐዋሳ ከተማ ታቦር ክፍለ ከተማ ውስጥ ሲሆን፣ ልጃቸውን በቀጠሯቸው መሠረት ወደ ኮሪያ አጠቃላይ ሆስፒታል ይዘው የመጡት የካቲት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደነበር፣ ቀዶ ጥገና እንዲደረግለት ቀጠሮ የያዘው በካርድ ቁጥር 394082 መሆኑን በጠበቃቸው አቶ ሰለሞን እምሩ የቀረበው ቀጥታ ክስ ያብራራል፡፡
ሕፃኑ ዶ/ር ፍሬው አየለ በተባሉ የሆስፒታሉ የሕፃናት ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት፣ ቀዶ ጥገናው በጥሩ ሁኔታ ተሠርቶለት እንደነበር ክሱ ይገልጻል፡፡ ቀዶ ጥገናውን ያደረጉት ሐኪም ስለቀዶ ጥገናው ሥራ ለመጻፍ ወደ ቢሯቸው ሲገቡ፣ በሁለተኛ ተከሳሽነት የቀረቡት እሌኒ ታምሩ የተባሉ የሰመመን ሰጪ ባለሙያ፣ ሕፃኑ በሕክምና ጠረጴዛ ላይ እያለ በራሱ መተንፈስ ስለመጀመሩ ሳያረጋግጡ ለሕፃኑ ሳንባው የተላከውን የመተንፈሻ ቱቦ መንቀላቸው በክሱ ተጠቁሟል፡፡
በመሆኑም ሕፃኑ የኦክስጅን እጥረት እንዲከሰትበት በመደረጉ፣ ዘለቄታ ያለው የአዕምሮ ጉዳት (Hypoxic Brain Injury) እንደደረሰበት በክሱ አክሏል፡፡ ፍፁም ጤነኛ የነበረው ሕፃን መላ አካሉ መንቀሳቀስ ተስኖት ፓራላይዝድ መሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡ ክሱ ከመመሥረቱ በፊት የደረሰው ጉዳት እውነት ስለመሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣንና የጤና ባለሙያዎች ሥነ ምግባር ኮሚቴ ምርመራ ማካሄዳቸውም ተጠቁሟል፡፡
የሥነ ምግባር ኮሚቴው ቀዶ ሕክምና የሠሩትን ሐኪም፣ የሰመመን ሰጪ ባለሙያ እሌኒ ታምሩ፣ አንስቲሎጂስት ክንፈ በዕደማርያም (ዶ/ር) እና አዜብ ሌንጮ የተባሉትን ባለሙያዎች የሙያ ምስክርነት ቃል ተቀብሎ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ በዚህ መሠረት እሌኒ ታምሩ ከባድ የሕክምና ሙያ ግድፈት መፈጸማቸው በመረጋገጡ፣ የሙያ ፈቃዳቸው ለሁለት ዓመት እንዲታገድና በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስለሙያው ለሁለት ወራት ሥልጠና እንዲወስዱ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ሆስፒታሉ ቀዶ ሕክምናው በእሑድ ቀን እንዲደረግ ሲወስን ሕፃን ልጅ መሆኑን እያወቀ፣ በአንድ ሰመመን ሰጪ ሠራተኛ ብቻ እንዲሠራ ማድረጉ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁሞ፣ አስተዳደራዊ ዕርምጃ እንዲወስድበት ኮሚቴው ውሳኔ ማስተላለፉን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም በቀረበው ቀጥታ የፍትሐ ብሔር ክስ የሞራል ካሳ 1,000 ብር ጨምሮ፣ ሌሎች ከሕፃኑ ጋር የተገናኙ የተለያዩ ሕክምናዎችና ክብካቤ ጋር በአጠቃላይ 23,647,000 ብር ካሳ እንዲከፈል ለፍርድ ቤቱ የዳኝነት ጥያቄ ቀርቧል፡፡
Average Rating