ኦነግ ሠራዊቱ ትጥቁን ለአባ ገዳዎችና ለአገር ሽማግሌዎች ያስረክባል አለ
ስምምነቱን ለማስፈጸም 71 አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሟል
በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለወራት ሲወዛገቡ የቆዩት የክልሉ ገዥ ፓርቲ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦዴፓ) እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦሮሞ አባ ገዳዎች ኅብረት ባዘጋጀው የዕርቀ ሰላም ውይይት ላይ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ከስምምነት ደረሱ፡፡
ማክሰኞ ጥር 14 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የኦሮሚያ ባህል አዳራሽ በተካሄደውና በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተሳተፉበት ውይይት፣ የኦሮሞ አባ ገዳዎችና ሀደ ሲቄዎች በሁለቱ ድርጅቶች መካከል ዕርቅ ካልወረዱ እንደማይቀመጡና ወደ ቤታቸውም እንደማይመለሱ አስታውቀው ነበር፡፡ የሁለቱ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ውዝግብ በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ ወለጋ ውስጥ ግጭት መቀስቀሱና የሰዎችን ሕይወት ለአደጋ ማጋለጡ፣ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ችግር ውስጥ መክተቱ ይታወሳል፡፡
በውይይቱ ወቅት የአባ ገዳዎች ኅብረት ሰብሳቢ አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ፣ ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ መግባት እንደሚፈልግ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎቹም እርስ በርስ መጋጨታቸውን አቁመው ችግሮቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ጠይቀው ነበር፡፡
ኦዴፓንና ኦነግን ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ የከተተው ዋነኛ ጉዳይ በኤርትራ በመንግሥትና በኦነግ መካከል የተደረሰው ስምምነት አለመከበሩ ነው ተብሏል፡፡ በስምምነቱ መሠረት የኦነግ ጦር ትጥቁን ፈትቶ ወደ ካምፕ መግባት ሲኖርበት፣ ኦነግ ግን ሠራዊቱን ትጥቅ የሚያስፈታው የፀጥታ ኃይሎች ከፓርቲ ወገንተኝነት ተላቀው የመንግሥት መሆናቸው ሲረጋገጥ ነው የሚል ክርክር ሲያነሳ ነበር፡፡
ነገር ግን ሁለቱ ወገኖች መስማማት ባለመቻላቸው ምዕራብ ኦሮሚያ የጦር ቀጣና ሆኖ በርካታ ጉዳዮች መድረሳቸው ሲዘገብ ሰንብቷል፡፡ በዚህም ሳቢያ ነው የኦሮሞ አባ ገዳዎች ኅብረት የሁኔታውን አሳሳቢነት በመገንዘብ የዕርቀ ሰላም መድረኩን የጠራው ተብሏል፡፡
በዕርቀ ሰላም ውይይቱ ላይ የተገኙት የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፣ የአንድ አገር አባት ልጆች መገዳደል እንደማይገባቸው፣ አንዱ ሌላውን ማባረር መቅረት እንደሚኖርበት፣ ኦነግም በኤርትራ የተደረገውን ስምምነት ማክበርና መንቀሳቀስ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በኋላም አንዱ ሌላውን ማዳከምና በጦርነት መፈላለግ ማብቃት አለበት ብለዋል፡፡
በኦዴፓ በኩል ለሰላም ከመሥራት ወደኋላ አለመባሉን ጠቁመው፣ ከአባ ገዳዎችና ከሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር እየተሠራ ነው ካሉ በኋላ፣ የሰዎች ሕይወት እያለፈ በመሆኑና ባንኮችም ስለሚዘረፉ መንግሥት ሕግ ለማስከበር መገደዱን አስታውቀዋል፡፡ ፓርቲያቸው ሰላም ለማስፈንና የአባ ገዳዎችን ውሳኔ ለመቀበል ዝግጁ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ ዋናው የሚፈለገው ጉዳይ በምዕራብ ኦሮሚያ ሕዝቡ ችግር ውስጥ ስለሆነ፣ የሕዝብን ሰላም ማስከበርና ሕግ እንዲከበር ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ፣ ኦነግ ከመንግሥት ጋር ተስማምቶ ወደ አገር ቤት በሰላማዊ መንገድ ለመታገል መመለሱን አስታውሰዋል፡፡ በመሀል የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ከክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ ጋር መወያየታቸውንም ጠቁመዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት በኤርትራ የተደረገው ስምምነት በመንግሥት በኩል ተፈጻሚ አልሆነም፡፡ ከስምምነቱ ውስጥ ጦርነት በይፋ ማቆም፣ የፀጥታ ኃይሎች ከፓርቲ ተፅዕኖ መላቀቅና የኦነግ ሠራዊት የክልሉን የፖሊስ ኃይል መቀላቀል የሚሉት ይገኝበታል ብለዋል፡፡ የኦነግ ጦር ካምፕ ከገባ በኋላ ግን የኦነግ አመራሮች መጎብኘት ባለመቻላቸው ችግር ተፈጠረ ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ኦነግ ሰላም እንዲሰፍን ፍላጎትና ዝግጁነት አለው ብለዋል፡፡ ይህንንም ለአባ ገዳዎችና ለኦሮሞ ሕዝብ ኃላፊነቱን በመስጠት ተጠያቂነታቸውን ማውረዳቸውን አስታውቀዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኘው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ኃላፊና አክቲቪስት አቶ ጃዋር መሐመድ፣ ዕርቅ ለማውረድ መዋሸት ስለማያስፈልግ ሁለቱም ወገኖች ሀቁን ፊት ለፊት መነጋገር እንዳለባቸው ተናግሯል፡፡ በኦነግ በኩል ጦሩ ውጊያ አቁሞ ወደ ካምፕ እንዲገባ አቶ ዳውድን አባ ገዳዎች ቃል እንዲያስገቧቸው ጠይቋል፡፡
አቶ ዳውድም መንግሥትና ኦነግን የሚያጋጫቸው ከእነ ትጥቁ ያለው ሠራዊት መሆኑን በመግለጽ፣ የሠራዊታቸውን ጉዳይ ለአባ ገዳዎችና ለኦሮሞ ሕዝብ አስረክበናል በማለት ቃል ገብተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ሠራዊቱ ትጥቁን ለአባ ገዳዎችና ለአገር ሽማግሌዎች እያስረከበ ይገባል ብለዋል፡፡ ተቋማዊ የሆነ ዋስትና እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡
አጠቃላይ በዕርቀ ሰላሙ ወቅት የተደረሰበትን ስምምነት ለማስፈጸም በተወሰነው መሠረት 71 አባላት ያሉት የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ የኮሚቴ አባላቱም ከአባ ገዳዎች 54፣ ከምሁራን 11፣ ከኦዴፓ ሦስት፣ ከኦነግ ሦስት እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
Average Rating