የትግራይ ሕዝብ ግዴታ
የትግራይ ሕዝብ ሆይ፤
ከፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ
ታሪክ ጸሐፊዎቻችሁና የፖለቲካ መሪዎቻችሁ ከኦነግ ጋር በመሆን በዘመኑ ፖለቲካ ላይ በሚያወጧቸው መግለጫዎች ላይ ታሪክ ሲያዛቡ፥ ምንጮቹ በሚሉት መሠረት ያንን ለማስተካከል (ለማስተማር) የምጽፈውን ስለሚያነቡ አይወዱኝም ብዬ እገምታለሁ። መገመት ብቻ ሳይሆን፥ እንደማይወዱኝ ነግረውኛል። ዳኛው ነፃ አወጣኝ እንጂ፥ አቶ መለስ ዜናዊ፥ “ዘር አጥፊዎች” ብሎ ከከሰሳቸው ንጽሓን ውስጥ አንዱ አድርጎኝ ነበር። የኦነግ ደጋፊዎች የታሪክ መጽሐፌ (የአባ ባሕርይ ድርሰቶች) ከሰው እጅ እንዳይደርሱ ለማድረግ ሞክረዋል። በቀጥታም ደጋግመው ሰድበውኛል፥ አስፈራርተውኛልም። እኔን በመጥላት ረገድ ሕወሐቶች ብቻቸውን አይደሉም፤ ደርጎችም አይወዱኝም ነበር።
ስለዚህ፥ ይኸንን መልእክት የምልክላችሁ በጨለማ እንደሚያነጣጥር ሰው ሆኜ ነው። ሆኖም፥ የጥላቻው ምንጭ ታሪክ እየጠቀስኩ በመናዴፌ ስለሆነ፥ መልክቴን ከሰፊው የትግራይ ሕዝብ እንዳይደርስ አያደናቅፍብኝም የሚል ምኞት አለኝ። የምትናደፍ ንብ ማር ትሰጣለች።
መልእክቴ ባጭሩ እንዲህ የሚል ነው፥ “የኢትዮጵያን አንድነት ለመጠበቅ፥ ዲሞክራሲንና ፍትሕን በኢትዮጵያ ለማስፈን፥ ሕዝቧን ለማበልጸግ፥ ጤናውን ለማስጠበቅ በሚደረገው ዘመቻ ታሪክ የሰጣችሁን የፊታውራሪነት ቦታችሁን በምንም ምክንያት እንዳትለቁ” ነው። ታሪክ የሰጣችሁን ቦታ የምለው የኢትዮጵያ መንግሥት የተጀመረው አክሱም ላይ ስለሆነ ነው። መንግሥት አክሱም ላይ የተጀመረው እንደ ዝናም ከአክሱም ሰማይ ወርዶ፥ ወይም እንደ ማዕድን ከአክሱም ምድር ወጥቶ ሳይሆን፥ አባቶቻችን አክሱማውያን ስለወለዱት ነው። ጠቅላይ ሚንስተሩ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወርቆች ናችሁ ያሏችሁ፥ የቅዱስ ያሬድን አስተዋፅኦ ያደነቁት፥ የንጉሥ ካሌብን ቅዱስነትና ጀግንነት የነገሩን የሆነውን ታሪክ እየጠቀሱ ነው።
“የፊታውራሪነት ቦታችሁን እንድትይዙ” ሳሳስብ የአስተዳደሩን መሪ ቦታ መያዝንና አለመያዝን ይጨምራል። በምርጫ ብታሸንፉ መሪውን ትይዛላችሁ፤ ባታሸንፉ የዲሞክራሲ መንገድ ጠራጊነትን ትይዛላችሁ። አባቶቻችሁ የፈጠሯትን ሥልጣን በጦር ከመያዝ ታላቅቁናላችሁ።
ባለፉት ጥቂት ወራት ከትግራይ ፖለቲከኞች የሚሰማው፥ “ሕገ መንግሥቱ ይከበር” የሚል ነው። ሕግ ተከብሮ በማይታወቅበት ዘመን ይህ ጥሪ ሲሰማ ቃናው ከምርጥ ሙዚቃ የበለጠ ይጣፍጣል። ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻልና እንዲከበር፥ ኑ እንተባበር። ይህን ጥሪ የማቀርብላችሁ ያስተዳደር መሪው ከእጃችሁ ስለወጣ አለመደሰታችሁ በግልጽ ስለሚታይ ነው። አገር ወዳድ ሕዝብ ብልህ መሪ ይፈልጋል እንጂ፥ እኔ ካልመራሁ ሰርዶ አይብቀል አይልም።
የታሪክን ሂደት ስናየው፥ የተጀመረው ለውጥ ግፋ ቢል ይዘገይ ይሆናል እንጂ፥ መፈጸሙ የማይቀር ነው። ኢትዮጵያ አንድ ቀን ሙሉ ዲሞክራሲ የሰፈነባት አገር ትሆናለች። በምን ዓይነት ትግል አልፋ ዲሞክራሲ እንደሰፈነባት ሂደቱን ታሪክ ይመዘግበዋል። እዚያ ታሪክ ውስጥ የትኛውን አቋም ይዛችሁ፥ የትኛውን ሚና ተጫውታችሁ ትገኙ ይመስላችኋል? “ደርግን የጣሉ ትግሬዎች የዲሞክራሲን መስፈን ተቃውመው ነበር” የሚል ጥቁር አሻራ ካስመዘገባችሁ፥ ልጆቻችሁን መኵሪያ አባቶች ታሳጧቸዋላችሁ።
በግላጭ ለመቀበል ይከብዳችሁ ይሆናል እንጂ፥ ደርግ ከወደቀ በኋላ መቅሠፍት የደረሰብን፥ የሕወሐት አመራር ባህላችንን ባህሉ ከማያደርግ መሪ እጅ ስለገባ ነው። እውነት ብትመርም ለአንዳፍታ ልብ በሉ፤ አመራሩ የትግራይ አካል የሆነችውን ኤርትራን “የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነበረች” ብሎ ከጻፈ ሰው እጅ ስለገባ ነው። “የኢትዮጵያ ጠላት አማራውና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ናቸው” ብሎ በሚያምን ሰው እጅ ስለገባ ነው። “ትግሌ የትግራይን ሕዝብ በኢትዮጵያውያን ሁሉ ላይ የበላይ (Tegray über Alles) ለማድረግ ከሚፈልግ መሪ እጅ ስለገባ ነው። “ትግሌ ትግራውያንን በሀብት ረገድ የኢትዮጵያ አይሁድ ለማድረግ ነው” ከሚል መሪ እጅ ስለገባ ነው። ባለ ብዙ ወደብ ኢትዮጵያ ወደብ-አልባ የሆነችው፥ አመራሩ መለስ ዜናዊ እጅ ስለወደቀ ነው። ክልል የሚባል ሥርዓት ፈጥሮ በድምበር የሚያጋድለን፥ “ከገዛ ሀገራችሁ ውጡ” የምንባለው፥ አመራሩ መለስ ዜናዊ እጅ ስለወደቀ ነው።
ከነዚህ ወንጆሎች ውስጥ የማትቀበሉት የትኛውን ነው? ሁሉም ወይም አብዛኛው እውነት ከሆነ፥ በምን ምክንያት ነው የወንጀለኛውን ወንጀል ወንጀላችሁ የምታደርጉት? ይህ ሰው ፍላጎቱን ለመፈጸም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ምን መቅሠፍት እንዳመጣ ተዘርዝሮ አይተናል፤ አይታችኋል። ርግጥ፥ ብቻውን አልፈጸመውም፤ ግን ግብር-አበር መፍጠር ከቻለ፥ የሚቈጠረው ብቻውን እንዳደረገው ነው። “ከምገደል፥ ግደል ያሉኝን ብገድል ይሻለኛል” የሚሉ ብዙ ግብር-አበሮች ከየትናውም ጎሳ/ነገድ አትርፏል።
ዛሬ በይፋ የወጡትን የኢሕአዴግ ወንጀሎች የሠሩት ሁሉም ትግሬዎች አይደሉም። የጌታቸው አሰፋ ምክትል የነበረው ያሬድ ትግሬ አይደለም። ኢሕአዴግ የፈጸመውን ወንጀል ሽንጣቸውን ገትረው ከጋዜጠኞች ጋራ ይከራከሩ ከነበሩት ውስጥ የሌላ ጎሳ ግብር-አበሮች ነበሩባቸው፤ ሁሉም ትግሬዎች ብቻ አልነበሩም። “ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጡ” አይሁን እንጂ፥ ፈርተው ወንጀል የፈጸሙና ጥቅም ፈልገው ግብር-አበር የሆኑ አንድ አይደሉም።
በኢትዮጵያ ታሪክ በደጉም በክፉውም አማሮችና ትግሬዎች በምንም ጊዜ ተለያይተው አያውቁም። በመሠረቱ የአግዓዝያን “ባህል ተሸካሚዎች” ትግሬዎችና አማሮች ናቸው። በታሪክ አንድነታቸው በአጭር ድርሰት ተዘርዝሮ አያልቅም። ሆኖም፥ ለምሳሌ ያህል፥ አፄ ልብነ ድንግል ከግራኝ ሰይፍ ያመለጠው ደብረ ዳሞ (ትግራይ ውስጥ) ተሸሽጎ ነው። ልጁን አፄ ገላውዴዎስን ቅብዐ ንግሥ ቀብተው ያነገሡት የገዳሙ አበምኔት አቡነ ተርቢኖስ ናቸው።
ድል ሲቀዳጂ ብሥራቱን መጀመሪያ የላከው ለደብረ ዳሞ መነኮሳት ነው፤
አባቴ ተርቢኖስና የደብረ ዳሞ መነኮሳት ሆይ፥ የምሥራች፥ የምሥራች፥ በጸሎታችሁ እግዚአብሔር ለኔና ለመኳንንቴ ጠላትን ማንበርከክንና ሰላምን ሰጥቶኛል። የአባቴን ሰይፍና አምስት ጠባቂዎች ከነቀለባቸው ልኬላችኋለሁ። ከአሁን ጀምሮ ይህ ሰይፍ በአባቴ አስከሬን ትራስ አጠገብ ይቀመጥ።
ፖለቲከኞችና ወገንተኛ ታሪክ ነጋሪዎች ንጉሦቻችንንና የመንፈሳዊ መሪዎቻችንን የጎሳ ወይም የጎጥ ሲያደርጉብን፥ እኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ እምቢ ማለት አለብን። አፄ ቴዎድሮስ የቋራ ሰው ቢሆኑም፥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ንጉሥ ነበሩ። አፄ ዮሐንስ የተምቤን ሰው ቢሆኑም፥ ከነገሡ በኋላ የኔም የተምቤኔው ሰውም ንጉሥ ነበሩ። አቡነ ኤዎስጣቴዎስ፥ አቡነ እስጢፋኖስ፥ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሁላችንም አባቶች ናቸው። “አፄ ዮሐንስ የኛ ናቸው፤ አፄ ምኒልክ የናንተ ናቸው” የሚል አስተሳሰብ አንድነታችንን መካድ ስለሆነ፥ ከትግራይ ተወላጆች አፍ መውጣት የለበትም። አትስሟቸው፤ገሥጿቸው። የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሥልጣን የሚመኛት ብዙ ስለሆነ፥ ለማሸነፍ ሁሉም እርዳታ ከተገኘበት ይጠይቁ ነበር። ሥልጣን ለመያዝ በውጪ እርዳታ በመጠቀም ረገድ አንዱ ንጉሥ ከሌላው ንጉሥ የበለጠ ወይም ያነሰ አላደረገም። ይኸንን በታሪክ የተመዘገበ ታሪክ ማወቅ ትልቅ ዐዋቂ አያደርግም። ትልቅ ዐዋቂ መስሎ እውነታውን እያጓደሉ ለሌሎች ማስተማር በሕዝብ መካከል የቂምና የመለያየት መርዝ መርጨት ነው።
“የክልል ሥርዓት ስለአፋጀን፥ ከዛሬ ጀምሮ የትግራይ ሕዝብ ሰርዞታል” የሚል ዓዋጅ አስሰሙን። ያመጣችሁትን አሩጡት። ብዙ ተከታይ ታገኛላችሁ። ክልላችሁ/ክልላችን ሰፊዋ ኢትዮጵያ ነች። ወልቃይት፥ ጸገዴ፥ ጸለምት፥ ጠለምት የአማራ ወይም የትግራይ ብቻ አይደሉም፤ የራሳቸውና የሁላችንም ናቸው። ማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሀገር መሆኑን ሰው ሳይቀድማችሁ ዐውጁልን፤ በመንፈስ ምሩን። ኢትዮጵያ በኢሕአዴግ ዘመን (በትግራይ አመራር) በእድገት ጉልሕ እመርታ ማሳየቷ እንዳይዘነጋ ማድረግ ግዴታችሁ ነው። “ብቅል የገደለውን ብቅል ያነሣዋል።”
Average Rating