እሑድ ጥር 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ከአንድ ዓመት ከሁለት ወራት በላይ ታስረው የተለቀቁት ሼክ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል አሙዲ፣ ከእስር ነፃ ለመውጣት ከፍተኛ ገንዘብ መክፈላቸው ተሰማ፡፡ ባለፈው ዓመት 10.9 ቢሊዮን ዶላር ሀብት የነበራቸው ሼክ አል አሙዲ፣ በአሁኑ ወቅት በፎርብስ የቢሊየነሮች ዝርዝር ላይ በ1.2 ቢሊዮን ዶላር ሀብት 159ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ፎርብስ እ.ኤ.አ. በ2018 ሼክ አል አሙዲ ከቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ ማስወጣቱ ይታወሳል፡፡ በሰጠው ምክንያትም የትኛው ሀብት የእሳቸው እንደሆነ ግልጽነት ባለመኖሩ ነው ብሏል፡፡
የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ባካሄደው የፀረ ሙስና ዘመቻ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ባለሀብቶች አንዱ የሆኑት ሼክ አል አሙዲ፣ ምን ያህል ገንዘብ ለሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ግን እንደከፈሉ ማወቅ አልተቻለም፡፡ ለሀብታቸው በከፍተኛ መጠን ማሽቆልቆል ምክንያት ግን ምናልባት ለነፃነታቸው ከፍተኛ ገንዘብ መክፈላቸው ሳይሆን እንዳልቀረ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት በፀረ ሙስና ዘመቻው ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሳያገኝ እንዳልቀረ ይገመታል፡፡
ሼክ አል አሙዲ በእስር በነበሩባቸው ጊዜያት ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ባደረጉባት ኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ የፖለቲካ አመራር ለውጥ ተካሂዷል፡፡ በፖለቲካ ለውጡ ሒደት በነበረው ሕዝባዊ አመፅ የሼክ አሊ አሙዲ የተወሰኑ ንብረቶች ሰለባ ሆነዋል፡፡ የፖለቲካ አመራር ለውጥ ከተደረገ በኋላም ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኘው የሚድሮክ ጎልድ የለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ በአካባቢና በሰዎች ላይ አድርሷል በተባለ ተፅዕኖ ምክንያት ሲታገድ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ለዓመታት ታጥረው የቆዩ 11 ቦታዎች ደግሞ ካርታቸው መክኗል፡፡
የሼክ አል አሙዲ የቅርብ ሰው የሆኑት አቶ አብነት ገብረ መስቀል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት ሼኩ ጂዳ በሚገኘው መኖርያ ቤታቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ጊዜያቸውን እያሳለፉ ነው፡፡
‹‹ጤናቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል፣ ሞራላቸውም እንደዚያው፡፡ ፕሮግራማቸውን አሁን መናገር ባይቻልም ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ወደ አገራቸው ይመጣሉ፤›› በማለት የገለጹት አቶ አብነት፣ ‹‹ሼክ አል አሙዲ አገራቸው ከመጡ በኋላ በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትለው ሥራቸውን ማካሄድ ይጀምራሉ፤›› ብለዋል፡፡ ምንም እንኳን አቶ አብነት ሼክ አል አሙዲ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ ይበሉ እንጂ፣ በሳዑዲ መንግሥት የፀረ ሙስና ዘመቻ ከታሰሩት መካከል አብዛኛዎቹ እስካሁን ከሳዑዲ ዓረቢያ መውጣት አይችሉም፡፡ በተመሳሳይም ሼክ አል አሙዲ ከሳዑዲ እንዳይወጡ ዕገዳ ሊደረግባቸው ይችላል የሚሉ ግምቶች አሉ፡፡
‹‹የቆሙ ሥራዎችና የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች በሙሉ በተካሄደው አገራዊ ለውጥ መሠረት ሥራቸው ይጀመራል፤›› በማለት የገለጹት አቶ አብነት፣ ‹‹ሼክ አል አሙዲ ባልነበሩባቸው ጊዜያት በኢትዮጵያ የሚገኙት ድርጅቶቻቸው ሥራቸውን በአግባቡ በመሥራት አትራፊ ሆነው ቀጥለዋል፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ሼክ አል አሙዲ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ደርግ ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ቢሆንም፣ ሙሉ ለሙሉ ወደ ኢንቨስትመንት ከገቡ 25 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ባለሀብቱ 105 የሚጠጉ ኩባንያዎችን በአራት ግሩፖች አዋቅረዋል፡፡ በእነዚህ ኩባንያዎች ከ50 ሺሕ በላይ ሠራተኞች የሚተዳደሩ ሲሆን፣ ከመንግሥት ቀጥሎ በኢትዮጵያ ትልቁ ቀጣሪ አድርጓቸዋል፡፡
Average Rating