የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፍርድ ቤት ውሳኔ አፈጻጸምን ተግባራዊ ሊያደርግ ባለመቻሉ፣ ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን ታስረው እንዲቀርቡ በፍርድ ቤት የተሰጠ ትዕዛዝ በሌላ ኃላፊ መቀየሩ ታወቀ፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀጽ 26(1)ን በመተላለፍ የተቋሙን አንድ ኃላፊ ያለፈቃዳቸውና በሌለ የሥራ ቦታ መመደባቸው ተገቢ አለመሆኑ ተገልጾ፣ በፍርድ ቤት የተሰጠን ውሳኔ ተግባራዊ ባለማድረጋቸው፣ የፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 13ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት፣ ጥር 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ታስረው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡
ሚኒስትሩ ታስረው እንዲቀርቡ የተሰጠውን ትዕዛዝ የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ለ15 ቀናት ማገድ እንደሚችሉ የተረዳው ተቋሙ፣ ለ15 ቀናት ተፈጻሚ እንዳይሆን ማሳገዱንም ሪፖርተር አረጋግጧል፡፡
የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 334 ድንጋጌ መሠረት ለ15 ቀናት የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዳይፈጸም ከማገድ ውጪ፣ ሚኒስትሩ ለበላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ስለማለታቸውና የቀረበለት ነገር ስለመኖሩ ያለው ነገር እንደሌለ ተገልጿል፡፡
የሚኒስትሩን መቅረብ ለመጠባበቅ ለጥር 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው የፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለተከራካሪ ወገኖች በሰጠው ምላሽ፣ መዝገቡን ለጥር 27 ቀን 2011 ዓ.ም. መቅጠሩንና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለምን እንዳልተፈጸመ መጠየቅ ያለባቸው ሚኒስትሩ ሳይሆኑ፣ የሰው ሀብት ዳይሬክተሩ መሆናቸውን እንደገለጸላቸው ታውቋል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ቀጠሮ ፍርድ ቤት ቀርበው የሚያስረዱት ሚኒስትሩ ሳይሆኑ፣ የሰው ሀብት ዳይሬክተሩ ናቸው፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ታስረው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ የተሰጠበት ክርክር የተጀመረው በ2010 ዓ.ም. ሲሆን፣ ምክንያቱ ደግሞ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የጤና አገልግሎት ጥራት ዳይሬክተር የነበሩት ዶ/ር ሐሰን መሐመድ ናቸው፡፡
ሚኒስትሩ ሚያዝያ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ለጥራት ዳይሬክተሩ በጻፉት የዝውውር ደብዳቤ፣ ከሚያዝያ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በያዙት ደመወዝና የሥራ ኃላፊነት ወደ አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተዛውረው እንዲሠሩ መመደባቸውን እንዳሳወቋቸው ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡ ዳይሬክተሩ ለዝውውር በተጻፈላቸው ደብዳቤ መሠረት እንዲፈጽም በግልባጭ ትዕዛዝ የደረሰው የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሰጠው ምላሽ፣ ተዘዋውረው እንዲሠሩበት የተገለጸው የሥራ መደብ አለመኖሩንና ደመወዝም አለመገለጹን በመጠቆም፣ ቦታ እንደሌለው ማሳወቁንም ሰነዶቹ ይገልጻሉ፡፡
በዚህ ጊዜ ሕጋዊ አሠራርን ባልተከተለና ከፈቃዳቸው ውጪ ከመደበኛ ሥራቸው ወደ ሌላ የሥራ ቦታ እንዲዛወሩ ከመደረጋቸውም በላይ፣ በተመደቡበት መሥሪያ ቤት የእሳቸውን ሥራ መደብ የሚመጥን ቦታና ደመወዝ እንደሌለ በመግለጽ ለፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር ፍርድ ቤት ክስ ይመሠርታሉ፡፡
ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ በሰጠው ፍርድ ሚኒስቴሩ የሕግ ስህተት መፈጸሙን፣ ዶ/ር ሐሰን ወደ አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላዝድ ሆስፒታል እንዲዘዋወሩ የተደረገበት ሁኔታ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆኑን በመግለጽ፣ ሲሠሩበት በነበረው የጤና አገልግሎት ጥራት ዳይሬክቶሬት በዳይሬክተርነት እንዲቀጥሉ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር፡፡
የፍርድ ቤቱን ውሳኔ የተመለከተው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ውሳኔውን በማክበር በሰው ሀብት ዳይሬክተሩ አቶ ሀብታሙ ደምሴ ፊርማ ወጪ በተደረገ ደብዳቤ፣ በነበሩበት የሥራ ኃላፊነትና ቦታ እንዲቀጥሉ ተደርገው ነበር፡፡
ነገር ግን የሰው ሀብት ዳይሬክተሩ የጻፉት ደብዳቤ በደረሳቸው በማግሥቱ ዶ/ር ሐሰን በሚኒስትሩ ወጪ የተደረገ ደብዳቤ ይደርሳቸዋል፡፡ ይኼውም ቀደም ብለው ተመድበውበት የነበረው አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ የሥራ መደብ ተፈጥሮለት ማለትም ‹‹ኮንሰልታንት ኤክስፐርት ፐብሊክ ሔልዝ ስፔሻሊስት›› ተብሎ በያዙት ደመወዝ እንዲዛወሩ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ሰነዶቹ ያስረዳሉ፡፡ የሚኒስትሩን ሁለተኛ ደብዳቤ የተቃወሙት ዳይሬክተሩ፣ ‹‹የፍርድ ቤት ውሳኔ አልተከበረም፤›› በማለት ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፍርድ አፈጻጸም በማመልከት መብታቸው እንዲፈጸምላቸው በማመልከታቸው፣ ፍርድ ቤቱ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዲጸም ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ተደጋጋሚ የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሊፈጸም ባለመቻሉ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ታስረው ለጥር 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ትዕዛዝ ቢሰጥም፣ ሊቀርቡ አለመቻላቸው ታውቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ምክንያቱን ባይገልጽም ትዕዛዙን ወደ ተቋሙ የሰው ኃይል በመቀየር ጥር 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀርበው እንዲያስረዱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
Average Rating