በኦነግና በኦሮሚያ ክልል መንግሥት መካከል የነበረው ቅራኔ በእርቅ ተፈቷል መባሉን ተከትሎ ኦነግ ሠራዊቱን በ20 ቀናት ወደ ካምፕ እንዲያስገባ ስምምነት ላይ መደረሱ ተገለጸ።
ወታደሮቹ ወደካፕ ሲገቡ የጀግና አቀባል እንዲደረግላቸው የሚል ውሳኔ የተላላፈም ሲሆን፣ በመንግሥት በኩል ወታደሮቹ ቶሎ ወደ ካምፕ እንዲገቡ ጉጉት መኖሩ ተነግሯል። በአዲሱ እርቅ የተላላፉ ውሳኔዎችን ሙሉ በሙሉ እንደሚቀበልም መንግሥት አሳውቋል።
ወታደሮቹ ወደ ካምፕ ሲገቡ ችግር እንዳይፈጠር በሚልም የአገር መከላከያ ሠራዊት ለሦስት ተከታታይ ቀናት ጥበቃ እንዲያደርግ ተስማምተዋል። በተጨማሪም ወታደሮቹ በካምፕ ውስጥ ከኹለት ወር ለዘለለ ጊዜ እንዳይቆዩ ውሳኔ መተላለፉ ተሰምቷል።
ቅራኔውን እንዲያስታርቅ የተቋቋመው ኮሚቴ ሐሙስ ጥር 17 ኹለተኛ የውይይት መድረኩን በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ማካሄዱን ተከትሎ ነው በኹለቱ ወገኖች መካከል እርቅና ሰላም የወረደው ተብሏል።
ኹለቱ ወገኖች ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲወቃቀሱባቸው ከነበሩ ጉዳዮች መካከል አንዱ የማጥላላት ዘመቻና ፕሮፖጋንዳ አለ የሚል ነው። በእርቅና የሰላም ጉባኤው ላይ ከዚህ በኋላ ማንኛውም ዓይነት ፕሮፓጋንዳ እንዲቆም እንዲሁም ቅሬታ ቢፈጠር እንኳን ለኮሚቴው እንዲያቀርቡ ተብሏል። ቅሬታን ለኮሚቴው ማቅረብ እንጂ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት እንደማይችሉም ስምምነት ላይ ተደርሷል ነው የተባለው።
የኦነግ ሊቀመንበር ዳውድ ኢብሳን ጨምሮ የኦዴፓ አመራሮች፣ አባገዳዎችና ምሁራን በተገኙበት በኦሮሞ ባሕል መሰረት ኮርማ በሬ ታርዶ የሰላምና እርቅ ሒደቱ በተፈጸመበት እለትም ‹‹ከዚህ በኋላ ለነጻነት በሚል አንድም ጥይት እንዳተኮስ፣ የመጨረሻው እርቅ ተካሂዷል፤ ሰላምም ወርዷል፣ የመጨረሻው ውሳኔ በመሆኑ ውሳኔውን የማይቀበል አካል ኦሮሚያ ውስጥ መኖር የለበትም›› የሚሉና ሌሎችም ሐሳቦች ከተሳታፊዎች ተሰንዝረዋል።
ኦነግ በመስከረም በሰላም ለመታገል ወስኖ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ በይፋ መግባቱ ይታወሳል። ይሁንና ላለፉት ወራት በመንግሥትና በኦነግ መካከል ‹‹ስምምነቱ ተጥሷል›› በሚል ወቀሳ ከመሰናዘር ተሻግሮ በተለይም በምዕራብ ወለጋ የሰው ሕይወትን የቀጠፉ ግጭቶች እንዲከሰቱ ሆነዋል። ኦነግ ገለልተኛና ሦስተኛ ወገን መሐል ገብቶ እንዲያደራድራቸውና ቀድሞ የነበረው ስምምነት እንዲታደስ፣ ሰላምም እንዲወርድ ሲል መጠየቁም ይታወሳል።
Average Rating