ከምዕራብ አፍሪካ አገራት በመነሳት በረሃዎችን አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ የሚፈልሱ የፈላታ ጎሳዎች መጨመራቸው የጋምቤላ እና አልጣሽ ፓርኮችን ችግር ውስጥ ከቷቸዋል ሲል የፌዴራል ዱር እንስሳት ልማት ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ ስጋቱን ገለፀ።
ከናይጄሪያ እንዲሁም ጥቂቶቹ ከቻድ እና ማሊን በመነሳት ወደ ኢትዮጵያ የሚፈልሱት የፈላታ ጎሳዎች፤ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ከብቶቻቸውን በመያዝ መድረሻቸውን የጋምቤላ በተለይም ደግሞ አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ማድረጋቸው የአገሪቷ ተፈጥሮ እና የዱር እንስሳት ሀብት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደሩ መሆናቸውን ባለሥልጣኑ ገልጿል።
የናይጄሪያ ፉላኒ ብሔረሰብ አባል የሆኑት ፈላታዎቹ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የቀንድ ከብት ይዘው ወደ ፓርኮቹ ይዞታ በመግባታቸው የዱር እንስሳት እንዲሰደዱ ምክንያት መሆናቸውንና በፓርኩ ብዝኃ ሕይወት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ባለሥልጣኑ ገልጿል። ውሃ እና ለከብቶቻቸው የሣር ግጦሽ ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት አርብቶ አደሮቹ፤ ሁለቱ ከጎረቤት ሱዳን ከሚያዋስኑት የኢትዮጵያ ፓርኮች ውስጥ በተለይም በበጋ ወቅት መኖሪያቸውን ማድረጋቸውን አዲስ ማለዳ ማግኘት የቻለችው መረጃ አመላክቷል።
ይህ ዓይነቱ ድርጊት ለብዙ ዐሥርት ዓመታት የነበረ ቢሆንም፤ አርብቶ አደሮቹ ይዘውት የሚገቡት ከብቶች ሳይመረመሩ መግባታቸው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች የቀንድ ከብቶችን ላይ እንዳይተላለፍ ባለሥልጣኑ መስጋቱን የተቋሙ የኮምኒኬሽን ኃላፊ ጌትነት ይግዛው ገልፀዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በ1960ዎቹ ወደ ኢትዮጵያ ብቅ ያሉት ፈላታዎች በብዛት በበጋ ወቅት የሚፈልሱ ሲሆን፤ በከፍተኛ ሁኔታ መታጠቃቸው ከደኅንነት አኳያ አስጊ እንደሆነ ጌትነት ተናግረዋል። በተጨማሪ፤ በዚህ የተነሳ ከአካባቢ ነዋሪዎች ጋር አንዳንዴ ግጭት ውስጥ አንደሚገቡ ማወቅ ተችሏል። ከሉዓላዊነት አንጻር፤ ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱንም አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአማራ ክልል አካባቢ፣ ደን፣ የፓርኮች ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ከፍተኛ ኃላፊ እንደገለፁት ብዙዎቹ ከሁለቱም ሱዳኖች ጋር የተዋለዱ ሲሆኑ፤ በአልጣሽ ፓርክ በደንብ መሥፈርት ከጀመሩ ሁለት ዐሥርት ዓመታት እንዳለፋቸው ገልጸዋል።
በደርግ ወቅት በአልጣሽ ፓርክ በነበረው ከፍተኛ ጥበቃ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት ፈላታዎች ቁጥራቸው አነስተኛ የነበረ ሲሆን ከሽግግር ጊዜ አንስቶ ግን ቁጥራቸው እየጨመረ እንደመጣ መረጃዎች ያሳያሉ። በ2009 በክልሉ በተደረገ ጥናት መሠረት፤ የፈላታ ጎሳዎች ዛፎች እየቆረጡ እሳት የሚያቀጣጥሉ ሲሆን ይህም በአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ለሚከሰቱ ሰደድ እሳት ምክንያት እንደሆነ ገልፆ ነበር። ፓርኩ ላይ ለሚከሰቱ 99 በመቶ ለሚሆኑ ችግሮች ምክንያት መሆኑ ጥናቱ አሳይቷል። በወቅቱም ወደ 300ሺሕ የሚሆኑ ከብቶች ፈላታዎች በፓርኩ ውስጥ እንደነበራቸው ጥናቱ አሳይቶ ነበር።
የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ከአዲስ አበባ 1025 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በመቀጠል ለአማራ ክልል ኹለተኛው ትልቁ ፓርክ ነው። የቆዳ ሥፋቱ 266 ሺሕ 570 ሄክታር የሆነው ፓርኩ፤ የአዲስ አበባን የቆዳ ሥፋት አምስት እጥፍ ያክላል። በሌላ በኩል፤ የፈላታዎች መኖሪያ የሆነው የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ 4ሺህ 575 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው።
Average Rating