በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የፋብሪካ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ 50 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መገኘቱ ታወቀ። የፌደራል ኦዲተር መስሪያ ቤት ከ2007 እስከ 2010 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የኢንዱሰትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን የክዋኔ ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት እንደገለፀው በ2009 በጀት ዓመት በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የውጭ ንግድ ገቢ አፈፃፀም 2 ነጥብ 91 በመቶ መሆኑን አሳውቋል። ከዚህም ጋር በተያያዘ ኮርፖሬሽኑ ከፋብሪካ ሼዶች ኪራይ ሊሰበስብ አስቦ 36 በመቶ የሚሆነውን ለመሰብሰብ ችያለሁ ቢልም መረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት መረጃውን መቀበል እንደሚቸገር በሪፖርቱ ላይ ገልጿል።
የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ሥራ ከገቡት የኢንዱስትሪ መንደሮች የሚገኘው ገቢ ዝቅተኛ መሆኑን የገለፀ ሲሆን። በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት አምስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በወር 11 ሚሊዮን ዶላር እንደሚገኝና ይህም ዝቅተኛ እንደሆነ የፌደራል ኦዲተር ኃላፊ ገመቹ ዱቢሶ ተናግረዋል። ገመቹ ዱቢሶ አያይዘው እንደገለፁት ለፓርኮች ከወጣው ወጪ አንፃር አሁን የሚገኘው ገቢ እጅግ አነስተኛ ነው ሲሉ አክለው እንደ ምክንያት ያስቀመጡት ደግሞ ከሼዶች ኪራይ መሰብሰብ የነበረበት ገቢ በአግባቡ አለመሰብሰብ፣ ለሠራተኞች የሚሰጥ ሙያዊ ሥልጠና አለመኖር እና በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ያለውን የሠራተኞች ፍልሰትን ለአብነት አንስተዋል።
የኮርፖሬሽን መስሪያ ቤቱ ሥራ አስፈፃሚ ሌሊሴ ለሚ የታዩትን የኦዲት ክፍተቶች በእርግጥ እንዳሉ እናምናለን ብለዋል። ሌሊሴ ̋ኮርፖሬሽኑን ይህን ያህል ሚሊዮን ዶላር አላመጣህም ተብሎ መገምገም የለበትም˝ ሲሉም በመከራከር ˝መጠየቅ ካለብን ለውጭ ንግድ ምቹ ሁኔታን ፈጥራችኋል ወይ?˝ ተብለን ነው መጠየቅ ያለብን ሲሉ ተደምጠዋል። ሌሊሴ እንደ ምክንያት የሚጠቅሱት ደግሞ ኮርፖሬሽኑ ከውጭ ንግድ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሌለው ገልፀው የባለ ሀብቶች ድርሻ መሆኑን ተናግረው ኮርፖሬሽኑ በባለ ሀብቶች ላይ ጣልቃ እንደማይገባ አክለዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ሌሊሴ ከሼዶች ኪራይ አሰባሰብ ጋር በተያያዘ ሲናገሩ ሼዶችን ለሚከራዩ ባለ ሀብቶች የእፎይታ ጊዜ እስከ ስድስት ወር መኖሩን ገልፀው በዚህ ጊዜም ኪራይ ማሰከፈል እንደማይችሉ ተናግረው በእነዚህ ምክንያቶች ገቢው ሊቀንስ እንደቻለ ገልጸዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከፌደራል ዋና ኦዲተር ጋር በመሆን ለኢንዱስትሪ መንደሮች ኮርፖሬሽን በኦዲት ግኝቱ ላይ በመመርኮዝ ጥያቄ አቅርቧል። በዚህም መሠረት የኦዲት ሪፖርቱ ያተኮረባቸውን ቦሌ ለሚ ቁጥር 1 እና ሐዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን መዕከል ያደረገ ሲሆን በ2008 በጀት ዓመት በቦሌ ለሚ ቁጥር አንድ ላይ 130 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታስቦ 16 ነጥብ 9 ሚሊዮን መገኘቱን ጠቅሰው በ2009 ለምን ዕቅዱ ወደ 40 ሚሊዮን ዝቅ ሊል ቻለ ሲሉ ይጠይቃል። በዚሁ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ2010 በጀት ዓመት ላይ የተከሰተው 98 ነጥብ 97 በመቶ የሠራተኞች ፍልሰት በምን ምክንያት እንደሆነ የሚሉ ጥያቄዎች ተሰንዝረዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ከቋሚ ኮሚቴው በአሁኑ ሰዓት የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሲጀምር ከነበረዉ የሰው ኃይል አሁን ለምን እንደቀነሰ የሚለው ከተነሱ ጥያቄዎቸ መካከል ዋነኛው ነው።
ለቀረቡት ጥያቄዎች የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ምላሽ ሲሰጡ እንደተናገሩት የቦሌ ለሚን የ2009 በጀት ዓመት ዕቅድ ክለሳ የተደረገው ከባለሀብቶች በተሰበሰበ መረጃ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቦሌ ለሚ የሠራተኞችን ፍልሰት በተመለከተ እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው የመኖሪያ ቤት ችግር፣ ተመጣጣኝ ክፍያ አለመኖር፣ የትራንስፖርት ችግር በዋናነት የሚጠቀሱ ችግሮች ሲሆኑ በሐዋሳ ኢንዱስትሪም ፓርክ እንደዚህ ዓይነት ችግር እንደሚስተዋል አክለው ገልፀዋል። በተያዘው በጀት ዓመት የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለ22 ሺሕ ሠራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን የሠራተኞቹ መቀነስ ዋነኛው የመኖሪያ ቤት ችግር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ኮርፖሬሽኑ የታዩትን ችግሮች ለመፍታት እየሠራ መሆኑን የጠቀሱት ሌሊሴ ባለ ሀብቶች ለሠራተኞች መኖሪያ ቤት እንዲገነቡላቸው እስከ ማስገደድ ድረስ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ከሲዳማ ብድርና ቁጠባ ጋር በመተባበር ለሠራተኞች ብድር ተመቻችቶ ቤት እንዲገነቡ እየተደረገ መሆኑ ታውቋል።
Average Rating