• መንግሥትን ወደ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ሊያስወጣ ይችላል
የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን 200 ሺሕ ቶን ስኳር ለፋብሪካዎች እና ለተጠቃሚዎች ሊገዛ መሆኑን አስታወቀ። ኮርፖሬሽኑ ጥር 18 ባወጣው ጨረታ ዓለም ዐቀፍ የስኳር አማካኝ ዋጋ በፓውንድ 0.13 የአሜሪካ ዶላር መሠረት በማድረግ ገዢው ወደ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር አካባቢ ሊያስወጣው ይችላል።
ግዢው ሙሉ ለሙሉ በመንግሥት የሚሸፈን ሲሆን ከዚህ ቀደም ሲያጋጥም የነበረውን የስኳር ዕጥረት ዳግም እንዳይከሰት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል።
ይህ ከባለፈው መስከረም አንስቶ እየገባ ካለው ጋር የስኳር ዕጥረት እንዳያጋጥም ለመጠባበቂያ የተገዛውና በአምስት ዙሮች ተከፋፍሎ ከወጭ አገር እየገባ ካለው 2 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ጋር ተዳምሮ አቅርቦት ላይ ያለውን ችግር ሊፈታ እንደሚችል ታምኗል።
የሚገዛው ስኳርም ለአራት ዙሮች ተከፋፍሎ ከሚያዚያ ወር አንስቶ የሚገባ ሲሆን በጅቡቲ ወደብ በኩል እንዲመጣ ታቅዷል። ጨረታውም የካቲት 19 የሚከፈት ሲሆን የተለያዩ አገራት አስመጪዎች ይሳተፋሉ ተበሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ከውጪ ስኳር ማስገባት ከጀመረች ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን በ1985 አስራ አምስት ሺሕ ቶን በሚደርስ የተጀመረው በአሁኑ ሰዓት ከ350 ሺሕ ቶን የሚጠጋ ስኳር ወደ አገር ውስጥ ታስገባለች። ስኳሩ በዋናነት ከሕንድ የሚገባ ሲሆን በተጨማሪም ከሳውድ አረቢያ፣ ታይላንድ፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬት፣ አልጄሪያና ቱኒዚያ ይገኙበታል።
አገሪቷ ስኳር ፋብሪካዎችን ገንብታ ማምረት ከጀመረች ከ60 ዓመታት በላይ ያስቆጠረች ቢሆንም በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ቁጥር እና የፍጆታ መጠን ተከትሎ ከፍተኛ የሚባል የስኳር እጥረት በተደጋጋሚ ሲከሰት ይታያል። በዚህም ምክንያት በመቶ ሺዎች ቶን የሚቆጠር ስኳር በተደጋጋሚ ከውጪ ግዢ ትፈፅማለች።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ስኳር ፋብረካ ወንጂ ሲሆን በ1950 አካባቢ የተመሰረተ ሲሆን ከ30 ሺሕ ሄክታር በላይ እርሻ ቦታን ይይዛል 4 የሚሆኑ አነስተኛ እና መካከለኛ የሚባሉ ፋብሪካዎች ሲኖሩት አጠቃላይ 12 ሺሕ 500 ቶን የመፍጨት አቅም አላቸው። የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰኳር ማምረት አቅም 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ሲሆን ይህም ከ 50 በመቶ ዓመታዊ ፍጆታ በታች በመሆኑ ክፍተቱን ለመሙላት ብዙ ሺሕ ቶን ስኳር ከውጪ ታስገባለች።
በአሁኑ ወቅት አገሪቱ አጠቃላይ ሰባት የስኳር ፋብሪካዎች ሲኖሯት እነሱም ቆየት ብለው የተመሠረቱ የትንዳሆ፣ አርጆ ዴዴሳ፣ ቀሰም እና በከፊል ሥራ የጀመረው እና በጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቅ የተመረቀው አሞ ኩራዝ ይገኙበታል።
እነዚህም በአጠቃላይ እስከ 500ሺሕ የሚጠጋ ዓመታዊ ምርት ሲኖራቸው አዳዲስ በመገንባት ላይ ያሉት የወልቃይት እና የጣና በለስ የስኳር ፋብሪካዎች ተጠናቀው ወደ ሥራ ሲገቡና ከላይ የተጠቀሱት በቅርቡ ሥራ የጀመሩት ፋብሪካዎች በሙሉ አቅም ማምረት ሲጀምሩ አጠቃላይ የአገሪቱ ምርት ወደ ሰባት ሚሊየን ኩንታል እንደሚሆን ይጠበቃል።
Average Rating