አምነስቲ ኢንተርናሽል አዲሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ረቂቅ አዋጅ በምዝገባ ሒደትና እንዲሁም ጣልቃ ገብነትን በማስፋት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችንና ማኅበራትን እንቅስቃሴን ያውካሉ ባላቸው አንቀፆች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ጠየቀ።
አምነስቲ ለምክር ቤቱ አባላት ጥር 16 በበይነ መረብ ላይ በጻፈው ግልጽ ደብዳቤና ባወጣው መግለጫ ረቂቅ አዋጁ በሥራ ላይ ካለው አዋጅ ጋር ሲነፃፀር መሠረታዊ መሻሻሎችን ያካተተ ነው ሲል ጀምሯል።
ኢትዮጵያ በነፃነት የመደራጀትና የመንቀሳቀስ መብቶችን የሚመለከቱትን የአፍሪካ የሰብኣዊና የሕዝቦች መብቶች ቻርተርን እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ዓለም ዐቀፍ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳንን ማጽደቋን ያስታወሰው አምነስቲ የማሻሻያ ሐሳቦቹንም ከእነዚህ ስምምነቶች ጋር እንዳነፃፀረው አመልክቷል።
አምነስቲ ከምዝገባ ጋር ተያይዞ “ሁሉም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ መመዝገብ አለባቸው” የሚለው አንቀፅ አላስፈላጊ የሆነ የፍቃድ ስርዓትን የሚዘረጋ ነው ሲል ይተቻል። ወደ ሥራ ለመግባት አግባብ ላለው የመንግሥት አካል ከማሳወቅ ባለፈ የመመዝገብ ግዴታ መጣሉ ተገቢ አለመሆኑን በመጥቀስም መቋቋማቸውን ማሳወቅ ብቻ በጎ አድራጎት ድርጅቶችንና ማኅበራትን ለማቋቋም፣ ሕጋዊ ሰውነት ለመስጠትና ሥራ እንዲጀምሩ በቂ መስፈርት እንዲሆን መደረግ አለበት ሲል ጠይቋል። የማሳወቅ ሥርዓትን የሚከተሉ አገራትን ለአብነት በማንሳትም አዋጭው መንገድ መሆኑን መክሯል።
ለምዝገባ የተቀመጡ የጊዜ ገደቦችም የተለጠጡ ናቸው የሚለው መግለጫው ለይግባኝ የተቀመጡትን የጊዜ ገደቦች ጨምሮ ለአገር ውስጥ ማኅበራት 4 ወር፣ ለውጪዎቹ ደግሞ ከ4 ወር በላይ የሚፈጅ ነው ብሏል። በመሆኑም አመልክተው ምስረታቸውን የሚጀምሩበት ስርዓት እንዲዘረጋ ጠይቋል።
ከውጭ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ጋር ተያይዞም “የውጪ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውሳኔ ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር የአድቮኬሲ ወይም የማሳመን ሥራ ላይ መሰማራት አይችሉም። በተጨማሪ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አግባብ ካለው የመንግሥት አካል ልዩ ፍቃድ ካልተሰጣቸው በቀር መራጮችን ማስተማርና ምርጫ መታዘብ አይችሉም” የሚለው አንቀጽ ሰፊና ለትርጉም የተጋለጠ ሐሳብ ስለያዘ ቢሻሻል ብሏል።
የመንግሥት ስጋት በአድቮኬሲ ሰበብ የዴሞክሪያሳዊ ስርዓቱ ላይ ያልተገባ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ የሚል ከሆነ ሙሉ በሙሉ ከማገድ የተሻሉ እርምጃዎችን በመውሰድ ሥጋቱን መቅረፍ እንደሚችል አመልክቷል። ለምሳሌ የምርጫ ስርዓቱን በተመለከተ የወጡ ሕጎችን ያለአድሎ በሁሉም ላይ ተፈፃሚነት በማድረግ ዴሞክሪያሳያዊ ስርዓቱን ውጫዊ ከሆነ ሕገ ወጥ ጣልቃ ገብነት ለመከላከል ሁነኛ መሣሪያ ነው ሲል መክሯል።
ረቂቅ አዋጁ ሁሉም በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት እንቅስቃሴያቸውን በነፃነትና ያለማንም ጣልቃ ገብነት ለመወስን እንዲችሉ እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ግንኙነት መፍጠር እንዲችሉ በሚያደርግ መልኩ እንዲሻሻልም ጠይቋል።
ክትትል፣ ምርመራ እና ንብረት ማገድ እንዲሁም በአስተዳደር ወጪዎች ላይ የተጣሉ ገደቦችም ቢስተካከሉ ሲል ምክረ ሐሳቡን አስፍሯል። ረቂቅ አዋጁ ተወካዮች ምክር ቤት ደርሶ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መመራቱ ይታወሳል።
Average Rating