ለጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ማምረቻ ፋብሪካ የሚያገለግል የኃይል ማመንጫ (ፓወር ፕላንት) ግንባታ ግዥ ጋር በተያያዘ፣ ከ422 ሚሊዮን ብር ጉዳት በመንግሥት ላይ አድርሰዋል የተባሉ ሦስት የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የተለያዩ የቀድሞ ኃላፊዎችና አንድ ቻይናዊ በሌለበት ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
ኃላፊዎቹ ክሱ የተመሠረተባቸው የኃይል ማመንጫውን ለማስገንባት ግዥ ሲፈጽሙ የኮርፖሬሽኑን የግዥ መመርያን መከተልና በግልጽ ጨረታ አወዳድረው መሆን ሲገባው፣ መመርያውን በመጣስና በጥቅም በመመሳጠር በተጋነነ ዋጋ ውል ከመግባታቸውም በተጨማሪ ለዋስትና መያዝ የሚገባቸውን ገንዘብ ሳይዙ ሙሉ ክፍያ በመፈጸማቸው ጉዳቱ ሊደርስ መቻሉን፣ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡
በመንግሥትና ሕዝብ ላይ 422,791,908 ብር ጉዳት አድርሰዋል ተብለው ክስ የተመሠረተባቸው ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁርንዲ፣ ሌተና ኮሎኔል አሰፋ ዮሐንስና ሻለቃ ክንደያ ግርማይ ሲሆኑ፣ በሌሉበት ክስ የተመሠረተባቸው በጥቅም በመመሳጠር ውል እንዲፈጽምና ክፍያ እንዲፈጸምላቸው አስደርገዋል የተባሉት ቻይናዊ ዩዋን ሃን ናቸው፡፡ የሜቴክ ኃላፊዎች የኮርፖሬሽኑን የግዥ መመርያን በመተላለፍ ቲሞስ ኢንተርናሽናል ሊሚትድ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው ከተባሉትዩዋን ጋር ውል የተፈጸመው ሁለት ጊዜ መሆኑን፣ መጀመርያ በ49,920,000 ዶላር ከዚያም በማሻሸል የ5,720,000 ዶላር ጭማሪ በማድረግ በ55,640,000 ዶላር መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
ኃላፊዎቹ ውሉን ከመፈራረምና ከማፅደቅ ባለፈ፣ የሥራ አፈጻጸም የባንክ ዋስትና ሳይያዙ፣ ለድርጅቱ 55,640,000 ዶላር ወይም 1,096,672,908 ብር ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ነገር ግን የፕሮጀክት ጠቅላላ ክፍያ አሥር በመቶ ወይም 422,791,908 ብር በሪቴንሽን (ዋስትና) መያዝ ይገባቸው እንደነበር ጠቁሞ፣ ባለመሆኑ ግን የተጠቀሰው የገንዘብ ጉዳት መድረሱን በክሱ አብራርቷል፡፡
በተጨማሪም መንግሥት ሥራውን ለማጠናቀቅ ዩናይትድ ኢንተርናሽናል ከተባለ ኩባንያ ጋር በገባው ተጨማሪ ውል 6,400,000 ዶላር በመክፈሉ፣ ይኼም ተጨማሪ ጉዳት መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ በመሆኑም ተጠርጣሪዎቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀ)፣ 33 እና 407(1ሀ)፣ (2) እና (3)ን፣ እንዲሁም አንቀጽ 411 (1ሀ እና ሐ) እና (3)ን በመተላለፋቸው፣ የመንግሥትን ሥራን በማያመች አኳኋን መምራትና በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆን የሙስና ወንጀል መፈጸማቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቶ አቅርቦባቸዋል፡፡
በሌላ የክስ መዝገብ ክስ ያቀረበባቸው የሜቴክ የተለያዩ ክፍሎች ኃላፊዎች የነበሩት ኮሎኔል ተከስተ ኃይለ ማርያም፣ ሌተና ኮሎኔል ያሬድ ኃይሉ፣ ኮሎኔል ሙሉ ወልደ ገብርኤል፣ ሌተና ኮሎኔል ሰለሞን በርሔና በሌሉበት የተከሰሱ አቶ ስምዖን ገብራይ፣ አቶ ሕንፃ አመሐ ገብረ ማርያም፣ ሃምሳ አለቃ መሳይ ባዩ፣ አቶ ግርማ ብዙነህና አቶ ደጌና አሰፋ ይባላሉ፡፡ ተከሳሾቹ የኢምፔሪያል ሆቴልን በግልጽ ጨረታና በኮርፖሬሽኑ የግዥ መመርያ መሠረት ተጫራቾችን አወዳድረው ማሳደስ ሲገባቸው፣ ከደጌና አሰፋ ሕንፃና ውኃ ሥራዎች ተቋራጭ ጋር በጥቅም በመመሳጠር፣ በተጋነነ ዋጋ እንዲታደስ በማድረጋቸው በመንግሥት ላይ 21,140,615 ብር ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ በሥልጣን ያላግባብ መገልገልና በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆን የሙስና ወንጀል ክስ ዓቃቤ ሕግ መሥርቶባቸዋል፡
Average Rating