በአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚቆመው የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሐውልት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የሌሎች አገሮች መሪዎች በሚገኙበት ተመርቆ ይፋ እንደሚሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አስታወቁ፡፡
ሐውልቱ ተመርቆ ይፋ የሚሆነው ከጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ በሚካሄደው የኅብረቱ የመሪዎች ስብሰባ ወቅት እንደሆነ፣ ቃል አቀባዩ አቶ ነቢያት ጌታቸው አክለው ገልጸዋል፡፡
የሐውልቱ ወጪ በኢትዮጵያ መንግሥት የተሸፈነ መሆኑን፣ ሐውልቱ የተሠራው ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለፈለገ ሰላም የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ባለሙያዎች እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ቃል አቀባዩ ሐሙስ ጥር 23 ቀን 2011 ዓ.ም. ስለተጠናቀቀው የኢትዮ ጂቡቲ የጋራ ሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባና ውጤቱ፣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጥረት ከተለያዩ አገሮች ስለተመለሱ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ፣ እንዲሁም ከመጪው ሳምንት ጀምሮ ስለሚከናወነው የአፍሪካ ኅብረት 32ኛው የመሪዎች ጉባዔ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮ ጂቡቲ የጋራ ሚኒስትሮች ስብሰባን በተመለከተም የሁለቱ አገሮች ሚኒስትሮች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን አውስተው፣ በተለይ ጂቡቲ በቅርቡ ያፀደቀችው የውጭ አገር ዜጎች የመኖርያና የሥራ ፈቃድ ለማግኘት ክፍያ መክፈል አለባቸው የሚለው አዋጅ፣ ለኢትዮጵያውያን በልዩ ሁኔታ ሊታይ እንደሚችል የጂቡቲ ፕሬዚዳንት ቃል መግባታቸው እንደ አንድ መልካም ውጤት የሚታይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የተለያዩ አገሮች ባለሥልጣናትና የሥራ ኃላፊዎች ከኅብረቱ ስብሰባ በፊትና ከኅብረቱ ስብሰባ ጎን ለጎን ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙም ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያን ከሚጎበኙ የሥራ ኃላፊዎች መካከልም የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንትና የኅብረቱ የውጭ ጉዳይና ደኅንነት ኃላፊ ፌዴሪካ ሞገሪኒና የኢስቶኒያ ፕሬዚዳንት ከሪስቲ ካጁሌግድ እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡FacebookTwitterLinkedInShare
Average Rating