www.maledatimes.com አገርንና ሕዝብን ማስቀደም - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

አገርንና ሕዝብን ማስቀደም

By   /   November 1, 2012  /   Comments Off on አገርንና ሕዝብን ማስቀደም

    Print       Email
0 0
Read Time:31 Minute, 4 Second

1
ቅጽ 38 ቁ.1 ጥቅምት 2005
አገርንና ሕዝብን ማስቀደም
የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝን አስፍኖ የነበረው የህወሓት/ኢህአዴግ ቁንጮ መለስ ዜናዊ አፋኝና አምባገነናዊ አገዘዙን ጥሎ ተሰናብቷል። የመለስ ዜናዊን አፋኝ የአገዛዝ ሂደትና ከህልፈቱ በኋላ ያለውን ሀገራዊ እውነታ በትክክል መረዳት ልንከተለው የሚገባንን የትግል አቅጣጫ አመላካች ነውና በጥንቃቄ መጤን አለበት እንላለን።
መለስ ዜናዊ ከጅምሩ ፀረ-ኢትዮጵያዊ አቋሙን እውን ለማድረግ፤ በኢትዮጵያዊነታቸው ፀንተው የቆሙ ድርጅቶችን ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳ ግለሰብ ነበር። ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች በምንም መልኩ እንዳይጠናከሩ የተቻለውን ሁሉ አደርጓል። ገና ከጠዋቱ በከተማ ውስጥ የድርጅቱን አባሎች በሕዝብ ድርጅት ጽ/ቤት ውስጥ ሰርገው እንዲገቡ በማድረግና ከደርግ ካድሬዎች ጋር በመተባበር ቀይ ሽብር እንዲካሄድ አስተዋጽዖ ያደረገ ግለሰብ ነበር። ከዚህም በላይ ኢትዮጵያዊ ድርጅቶችን የማምከን ጦርነቶች ከፍቶ ከትግራይ የውጡልኝ ዘመቻ በማካሄድ በርካታ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆችን ያጠፋ ድርጅት መሪ ሲሆን በትረ መንግሥቱን ከጨበጠ በኋላም ይህንኑ አቋሙን አጠናክሮ
ቀጥሎበት ነበር። በኢትዮጵያዊነት ላይ የሚደረገውን ዘመቻ በመቃወማቸው በአምባገነኑ መሪ ዕይታ ሥር በግፍ የተገደሉት እነ ጋይም፤ አሰፋ ማሩ፤ ተስፋዬ ታደሰና ደዛቸው የጠፋውን እነ አበራሽ በርታ፤ ፀጋዬ ገብረ መድኅን፤ ስጦታው ሁሴንና ሌሎች የኢሕአፓ አባላት፤ እንዲሁም እነ ፕሮፌሰር አሥራትና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ምን ጊዜም መዘንጋት የለባቸውም። ከምርጫ 97 በኋላም የቅንጅት የአመራር አባላትን በሙሉ
ዘብጥያ ማውረዱም የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።2አምባገነኑ መሪ “ሕገ-መንግሥት” ተብዬው ለዜጎች “የሰጠውን” መብት እየጣሰ፤ በዙሪያው የተኮለኩሉ አሻንጉሊቶቹ እንኳን ይታዘቡኝ ይሆን? ሳይል በሕዝባችንና በአገራችን ብሄራዊ
ጥቅም ላይ ለ21 ዓመታት እንደፈለገው ሲፈልጥና ሲቆርጥ የኖረ ግለሰብ ነበር።
በኢትዮጵያዊነት ላይ ያደረሰውን ግፍና ደባ እንዲሁም አምባገነናዊነትን ለማስፈን ያደረገውን የጥፋት ሂደት ቀላል አልነበረም። ገና በሥልጣን ላይ እንደወጣ ከሥልጣኑ በላይ በመሄድና የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጹ እንዳይሰማ ተደርጎ በጊዜው የትግል አጋሩ ከነበረው ከሻእቢያ ጋር በመመሳጠር ኤርትራን “አስገነጠለ”። ብዙም ሳይቆይ የኢትዮ-ኤርትራ እየተባለ የሚጠራው ጦርነት ሲቀሰቀስ አምባገነኑ መሪ ለፓርላማ ተብዬው ያሳወቀው ጦርነቱ ከተጀመረ ሳምንት ካለፈ በኋላ ነበር። ጥቂት የተቃዋሚ ድርጅቶች የፓርላማ አባላት ከማንገራገራቸው በስተቀር አብዛኛዎቹ ምንም ሳይተነፍሱ ነበር የተቀበሉት። ጦርነቱ የሁለቱ አምባገነን መሪ ተብዮዎች የዕብሪት ውጤት ሲሆን በርካታ
ሕይወትን የቀጠፈና ከፍተኛ ንብረትን ያወደመ የትዕቢተኞች ጦርነት እንደነበር የምናስታውሰው ነው። ይህ ብቻ አይደለም አምባገነኑ በማንአለብኝነት የፈጸመው ድርጊት። በመለስ ትዕዛዝ የኢትዮጵያ ወታደር የሶማሊያን ድንበር ተሻግሮ ሞቃዲሾ እስከሚደርስ ድረስ ፓርላማ ተብዬው በይፋ የሚያውቀው ነገር አልነበርም። ለፓርላማው ከቀረበ በኋላም ተቃውሞ ያሰሙት ጥቂቶች ሲሆኑ እነሱንም ለሀገር ደህንነት ደንታ የሌላቸው ተብለው ለጠቅላይ ሚኒስቴሩ ታማኝ በሆኑ የፓርላማ አባላት ተፈረጁ፤ ተወገዙም። አምባገነናዊ አገዛዙን የተቃወሙና የተቹ ሁሉ በሽብርተኝነትና “ሕገ-መንግሥት ሊንዱ” ነው በማለት ተወነጀሉ፤ ለእስራትና ስደት ተዳረጉ፤ ተገደሉም።
ሕዝባችን በዕቅድ ላይ የተመሠረተ የምግብ ዋስትና ይኑረው ብለው የጠያቁም ፀረ-ሕገ-መንግሥት ተባሉ።
በምርጫ 97 ወቅት አምባገነኑ እንደሚያሸንፍ ፍጹም እርግጠኛ ስለነበረ ለአጭር ጊዜም ቢሆን የመገናኛ ብዙሃንን ለተቃዋሚ ኃይሎች ፈቀደ። ተቃዋሚዎችም አጋጣሚውን በመጠቀምና ሕዝቡን በመቀስቀስ ህወሓት/ኢህአዴግ ምን ዓይነት ባዶ ድርጅት እንደሆነ ለማሳየት ቻሉ። ዕርቃኑን የቀረውና የተደናገጠው መለስ ዜናዊ የተረፈችውን የመጨረሻዋን ካርድ ተጫወተ። ይኸውም የኢትዮጵያ ሕዝብ የትግራይን ሕዝብ ለማጥፋት የተነሳ እንደሆነ አድርጎ ተቃዎሚዎችን ኢንተርሀምዌይ ናቸው በማለት በሚቆጣጠራቸው የመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ቀሰቀሰ። በዚህም በትግራይ ሕዝብና በተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ከፍተኛ ውጥረት እንዲሰፍን አደረገ። ምርጫ 97ን 3
ተከትሎም ከ50ሺህ በላይ ዜጎችን አሠረ፤ በጠራራ ፀሐይ ከ700 በላይ ንፁሃን ወገኖቻቸንን ጨፈጨፈ።
ከዚህ በተጨማሪ አባቶቻችንና እናቶቻችን ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው  ያቆዩልንን ሀገር መለስ ከ30 አስከ 60 ኪሎሜትር ስፋት ያለውና በርዝመቱ ደግሞ እስከ 1000 ኪሎሜትር የሚደርሰውን የሀገራችን ለም መሬት ለሱዳን ሲሰጥ የሕዝብ ተወካይ ነኝ የሚለው ፓርላማ ትንፍሽም አላለም። ይህ ብቻ አይደለም በመለስ ዜናዊ ይመራ የነበረው መንግሥት ተብዬው በሀገራችንና በወገናችን ላይ የፈጸመው በደል። ሕዝቡን እያፈናቀለ
ከሀያ እስከ ዘጠና ዘጠኝ ዓመት በሚደርስ ውል የሀገሪቷን ለም የእርሻ መሬት ባዕዳኑን ባለሀብቶች ባስገረመና ነፃ በሚባል ደረጃ ለሕንድ፤ ለቻይና፤ ለሳውዲ አረቢያና ለሌሎችም ሲቸበቸብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሁንም ተቃውሞ አላሰማም። የዚህ አስከፊ ድርጊት አሳዛኝ ውጤት ደግሞ ሕዝቡ አስተማማኝ የምግብ ዋስትና ሳይኖረውና የሕግ ከለላና ገደብ ሳይደረግበት በልማት ስም የአገሪቱን ሀብት የውጭ ከበርቴዎች እየተቀራመቱት ምርቱንም በኢትዮጵያ ገበያ ሳይሆን ወደ አውሮጳና መካከለኛው ምሥራቅ መጫን ሆነ።
በተጨማሪም አምባገነኑ መሪ በሀገሪቷ ውስጥ ያሉትን የዕምነት ተቋማት ለመቆጣጠር ባደረገው ጥረት ኦርቶዶክስን ለሁለት ሲከፍለው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በእምነታችን ጣልቃ ገብነት ይቁም! በማለታቸው መለስ ዜናዊ በአክራሪነትና በሽብርተኝነት ወነጀላቸው፤ በዓለም ሕዝብ ለማስወንጀል ጥረት አደረገ። ከዚህም በላይ ረግጦ ለመግዛት እንዲያመቸውና ሕዝቡ እንዳይተነፍስ አፋኝ የፕሬስ ሕግ በማውጣት ተግባራዊ አደረገ። ሌሎችንም ሌሎችንም መዘርዘር ይቻላል ይሁን እንጂ የጊዜው ጥያቄ አሁን ምን መደረግ አለበት? የሚለው ነው።
ዛሬ በሀገራችን ውስጥ የፖለቲካ ዳመና አንጃቧል። በመለስ ዜናዊ ቦታ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተተክተዋል። አቶ ኃይለማርያም መለስን ይተኩት እንጂ የሁለቱ ሰዎች ተክለ-ሰውነትና በኢህአዴግ ላይ ያላቸው ተጽዕኖ ለየቅል ነው። መለስ ዜናዊ ብቸኛ አድራጊና ፈጣሪ ሆኖ በድርጅታቸው ውስጥ የሚፎካከረው መሪ ሳይኖር የሱን ትዕዛዝ የሚቀበሉትን ሰብስቦ የተጓዘ አምባገነን መሪ ነበር። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ተፎካካሪና ተሟጋች በመሆን የሚታሙ አይደሉም። ነገር ግን መለስ ጥሎላቸው የሄደውን አምባገነናዊ አገዛዝ ተረክበው እየሄዱ ነው። አንዳንዶች ለአዲሱ ጠ/ሚኒስቴር ጊዜ እንስጣቸው የሚል 4አስተያየት ሲሰነዝሩ ተደምጠዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ የተቃዎሚ ኃይሎችና የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዥታ ሊኖራቸው አይገባም እንላለን፤ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ቃለ-መሃላ በፈጸሙበት ወቅት ሲናገሩ እንደተደመጠው የመለስ ዜናዊን ራዕይ እናስፈጽማለን ብለዋልና።
የመለስ ዜናዊ ራዕይ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ክብር ዝቅ ያደረገ፤ የኢትጵያን ታሪክ የአዝማሪዎች ታሪክ ያለ፤ መላ አፍሪቃውያን የሚኮሩባትን ሰንደቅ ዓላማችንን ጨርቅ ነው ያለ፤ አገራችንን በጎሳ ፖለቲካ ሸንሽኖ ሕዝባችን አብሮ እንዳይኖር እሳት ያቀጣጠለ፤አገራችን በኢኮኖሚ ከዓለም ድሃ አገሮች ውስጥ ወደ መጨረሻው እርከን እንድትወርድ ያደረገ፤ በልማት ስም በሙስና የተጨማለቁ ባለሥልጣኖችን ኮትኩቶ ያሳደገ…ወ.ዘ.ተ ራዕይ ነው። ስለዚህ አቶ ኃይለማርያም በእርግጥም ከመለስ ዜናዊ የተለዩና የተሻሉ ከሆኑና ጊዜ ሊሰጣቸው የሚገባ መሪ ከሆኑ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ ሰጭ የሆነ የራሳቸው ራዕይ ሊኖራቸው ይገባል። የህወሓት/ኢህአዴግን ራዕይ ነው ይዘን የምራመደው የሚሉ ከሆነ ግን “ጉልቻ ቢቀየር ወጥ አያጣፍጥም” ከማለት የዘለለ ሊሆን ስለማይችል ትግሉ  ተጠናክሮ መቀጠሉ የግድ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሀገሩና ለመብቱ ተሟጋችና ታጋይ በመሆኑ የሀገሩ ድንበርና መብቱ እስኪከበርለት ድረስ ትግሉን አጠናክሮ ሕዝባዊ ማዕበል ፈጥሮ መታገሉ የማይቀር ነው። ሕዝባዊ ማዕበል ምንኛ ጠንካራ እንደሆነ በቅርቡ የዐረብ ፀደይ (ስፕሪንግ) እየተባለ የሚጠራው እንቅስቃሴ በተጨባጭ አሳይቶናል። እንደ ሙባረክ ዓይነቱ አምባገነን በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ተንኮታኩቶ ሲወድቅ ለመታዘብ በቅተናል። ስለዚህ በተለያዩ ምክንያቶች የአፋኙ አገዛዝ መሣሪያ የሆኑ ዜጎች ሥርዓቱን በማራመድ ተጠያቂ ከመሆናቸው በፊት ጊዜው ሳያልፍ ስህተታቸውን አምነው ከሕዝብ ጋር መወገኛ ጊዜያቸው አሁን መሆኑን ለማስታወስ እንወዳልን። በተለይም የኢትዮጵያን ጥቅም ማስጠበቅ
ተቀዳሚ ግዳጁ የሆነው የመከላከያ ሠራዊት በዐረብ ፀደይ ወቅት በግብፅ እንደታየው፤የታጠቀውን መሣሪያ አፈሙዙን መደገን ያለበት በሕዝብ ላይ ሳይሆን በፀረ-ሕዝቦች ላይ እንደሆነ ሊገነዘብ ይገባዋል፤ ሕዝብ ምን ጊዜም አቸናፊ ነውና። ሕዝብ የሚፈልገው ሀገራችን የዜጎች መብታቸው ተከብሮ፤ ከዚህ ክልል አልፋችሁ መኖር አትችሉም፤ እኛ የሰጠናችሁን ሕገ-መንግሥት አትተቹም፤ አትቃሙም የሚለውን አምባገነናዊ መርህ የማይሰማባት ሀገር እንድትሆን ነው። በገዛ አገራቸው በሚፈልጉበትና በመረጡት ክልል ተዘዋውረው የመኖር፤ የመናገር፤ የመጻፍና የመሰብሰብ መብታቸው እንዲከበር ነው።5 የተቃዋሚ ኃይሎች ደግሞ የሕዝብ መብትና የአገር ደህንነት እስኪረጋገጥ ድረስ ተጨባጭ ሁኔታውን በትክክል በማጤን፤ አካሄዳቸውንም በጥንቃቄ በመመርመር ለሁኔታው የሚመጥኑ ውሳኔዎችንና እርምጃዎችን በመውሰድ ትግላቸውን በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠል ይጠበቅባቸዋል። አሁን የምንገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ የሚያረጋግጥል ነገር ቢኖር በጋራ ከመታገል የተሻለ አማራጭ እንደሌለ ነው። ህወሓት/ኢህአዴግ እስካሁን በሥልጣን ላይ ሊቆይ የቻለው በኃይል አፍኖና ረግጦ በመግዛቱ እንደሆነ ቢታወቅም የተቃዋሚ ኃይሎች
በጋራ መታገል አለመቻላቸው ደግሞ አስተዋጽዖ እንዳደረገ አሌ የሚባል አይደለም።
ስለዚህ በጋራ መታገል የግድ በመሆኑ ለጊዜው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ስድስት የፖለቲካና ሰባት የሲቪክ ድርጅቶችን እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦችን አቅፎ የተመሠረተው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) እጅግ ተስፋ ሰጪና አበረታች ኅብረት ነው። ስለዚህ ፀረ-ህወሓት/ኢህአዴግ ኃይሎች ሁሉ ተረባርበው ሊረዱትና ሊያጠናክሩት ይገባል እንላለን። አንድነት ኃይል በመሆኑ ተቃዋሚዎች ሁሉ በአንድ ድምጽ መናገር መቻል አለባቸው፤ ከዚህ የተሻለ አማራጭ የለምና። ይህ ብቻ አይደለም ሌላም አብሮ መሄድ ያለበት ጉዳይም አለ፤ የብሄራዊ እርቅ ጉዳይ።
ኢሕአፓ (ዴሞክራሲያዊ) አገራችን ያለችበትን ሁኔታ በሚገባ አጢኖና ሊከተል የሚችለውን አደጋ ተገንዝቦ ከመተላላቅ ፖለቲካ፤ ከባለጊዜ ጉልበተኛ፤ ቂም ከቋጠረ በቀለኛ፤ ከሙስና፤ ከቅጥፈት፤ ያለአግባብ ከመበልጸግ፤ ከኋላቀርነትና ከረሃብ ነፃ ልንወጣ የምንችለው ይህንን ለአንዴና ለሁሌም ከሥሩ ሊነቅል የሚችል የብሄራዊ እርቅ ሂደትን አማራጭ በማድረግ ስንሠራ ብቻ ነው ብሎ ያምናል። የብሄራዊ እርቅ አማራጭ ፍርሃትን፤ መሰደድን፤ መበቀልን፤ መታሰርንና መታረዝን ከኅብረተሰቡ ውስጥ የሚቀርፍ ወሳኝ አማራጭ ነው። ስለዚህ አዲሱ አስተዳደር የብሄራዊ እርቅ አማራጭን ዋነኛው አጀንዳው ሊያደርገው ይገባል እንላለን። አስተዳደሩ ከበስተጀርባው የሚበሳጭ፤ የሚከፋ፤
ቂም የሚቋጥርና ለመበቀል ጊዜን የሚጠብቅ ሕዝብ ፈጥሮ መጓዝ አይችልም፤ የለበትምም፤ ለሀገር እድገትና ብልጽግና ልብ ለልብ ተገናኝቶ ተባብሮ ለመሥራት የሚያስችል ልባዊ ፍቅር አይኖርምና። አምባገነን ያልፋል፤ አራማጆቹም እንዲሁ።
አዲስ ራዕይ ያለው አስተዳደር ግን ለሕዝብ ተስፋ የሚሰጥ እንጂ የሕዝቡን ተስፋ የሚያጨልም መሆን የለበትም። ስለዚህ ባለፉት 21 ዓመታት የተጓዘበትን መንገድ የሚከተሉ የአገዛዙ አራማጆች ለልጆቻቸው ትተው የሚያልፉትን ጠባሳ ጠንቅቀው ሊገነዘቡት ይገባል። የመንግሥቱ ሃይለማርያም ልጆች በሱ ግፍና በደል ኢትዮጵያዊ 6 ቁርኝታቸውን አጥተው በስደት እንኳን ሳይቀር ከራሳቸው ወገን ጋር ለመገናኘት የሚያስችላቸው የትስስር ገመድ በአባታቸው ጭካኔ ተበጥሶ የሱ ግፍ ከፋዮች ሆነዋል። ጠ/ሚኒስቴሩ ከተለመደው የጭካኔ መንገድ ወጥተው የባለሥላጣናቱ ልጆችና የተራው ሕዝብ ልጆች እጅ ለእጅ ተያይዘው በሀገር ግንባታ ሂደት ላይ እንዲሳተፉ የማድረግ ሕልም አለኝ ሊሉ ይገባቸዋል። ይህ ሕልም የብሄራዊ እርቅ ሕልም ሊሆን ይገባል። ይህንን ሕልም ተግባራዊ ከማድረግ ያነሰ ሕልም ከንቱ የፖለቲካ ቧልት፤ “የታላቁ መሪ” መዝሙር፤ ምን ጠብ ተፈጥሮ ነው ብሄራዊ እርቅ የሚለው ተረት ተረት ከመገዳደልና ከመጠፋፋት የማያድን የተለመደው የአምባገነኖች አዙሪት ሆኖ ሊቀጥል እንደሚችል ከወዲሁ መገንዘብ ይገባል እንላለን።እውነተኛ ብሄራዊ እርቅን ለማምጣት ምን ያስፈልጋል? ከሁሉ አስቀድሞ በማንኛውም
መልኩ ሀገራችን ያለችበትን አስከፊ ሁኔታ በመረዳት ከዚህ የድህነት አረንቋ፤ ከኋላቀርነት፤ ከመሃይምነት፤ ከረሀብ፤ ከበሽታ…ወ.ዘ.ተ በመላቀቅ በልማት ጎዳና ላይ ልትጓዝ የምትችለው በዜጎቿ ንቁ ተሳትፎ ብቻ መሆኑን ማመን ያስፈልጋል። ሀገራችን የዜጎቿን ሁሉ አስተዋጽዖ የምትሻበት ጊዜ እንጂ ማንንም ግለሰብ ወይም ቡድን ማግለል የምትችልበት ደረጃ ላይ እንዳልሆነች መረዳትን ይጠይቃል። ስለሆነም ዜጎች የችሎታቸውን ለማበርከት እንዲችሉ አስተዳደሩ ሁኔታዎችን ሊያመቻችላቸው ይገባል። አዲሱ አስተዳደር ከወያኔ/ኢህአዴግ ጎጠኝነትና አምባገነንነት ነፃ ሆኖ የአገሪቱ የወደፊት ዕድል ቀና እንዲሆን ምኞት ካለው፤ አዲስ ምዕራፍ የመክፈት ዕድሉና ቁልፉ በአጁ
ይገኛል። አስተዳደሩ ይህን አስቦና አልሞ በመጓዝ ከሕዝብ ጋር የሚታረቅበትንና በእርግጥም አዲስ አስተዳደር መሆኑን በተግባር ማስመስከር ያለበት ጊዜው አሁን ነው። ለዚህ ደግሞ በዝቅተኛ ደረጃ የሚከተሉትን እርምጃዎች በአፋጣኝ በመውሰድ ከሕዝብ ጋር ለመወገን ዝግጁ መሆኑን ምልክት መስጠት መቻል አለበት እንላለን። እነዚህም፦ 1. የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፤2. የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች፤ የመጻፍ፤ የመናገር፤ የመሰብሰብና
የመደራጀት መብቶችን ተግባራዊ ማድረግ፤3. የፖለቲካ እስረኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት፤4. ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች (በሕገ-ወጥነት የተፈረጁትንም ጨምሮ) በነፃነት
የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ መፍጠር፤75. ፀረ-መገናኛ ብዙሃን፤ ፀረ-ሲቪክ ማኅበራትና ፀረ-አሸባሪነት ተብለው የሚታወቁትን የሰው ልጅ መሠረታዊ መብቶችን የረገጡ ሕጎችን መሻር፤6. አፋኙን የፕሬስ ሕግ መሻር፤
7. ለሱዳን የተሰጠውን መሬትና፤ ሌሎች የሀገሪቱን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት የማያስከብሩ ውሎችን መሰረዝ፤ እንዲሁም 8. ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች የሚያሳትፍ የሰላምና የዕርቅ ጉባዔ መጥራት።
አዲሱ አስተዳደር የሰላም ምልክት የሆነው የወይራ ዘለላ መስጠቱንና በእርግጥም ለሰላም የቆመ አዲስ አስተዳደር መሆኑን የምናየው ከላይ የተጠቀሱትን መሠረታዊ ጥያቄዎች ተግባራዊ ሲያደርግ ነው እንላለን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች!!
እናቸንፋለን!!

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on November 1, 2012
  • By:
  • Last Modified: November 1, 2012 @ 10:55 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar