በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት በዓለም ባንክ ውስጥ ለከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ እንዳይወዳደሩ የተደረጉት ኢትዮጵያዊው ምሁር ዶ/ር ዮናስ ብሩ በተቋሙ ውስጥ የሚፈፀመውን ዘረኝነት በመቃወም ከ2 ሳምንት በላይ በረሃብ አድማ ላይ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ጣልቃ እንዲገባ እና ድምፁን እንዲያሰማ በደብዳቤ ተጠይቋል፡፡
ላለፉት 7 ዓመታት በዓለም ባንክ ውስጥ የአለማቀፍ ንፅፅሮሽ መርሃ ግብርን በምክትል ስራ አስኪያጅነት የመሩት ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ዮናስ፤ ተቋሙ ላወጣው የመወዳደሪያ መስፈርት ብቁ መሆናቸውን ጠቅሰው ራሳቸውን ለቦታው በእጩነት ቢያቀርቡም አፍሪካዊ በመሆናቸው ብቻ ተቀባይነት ማጣታቸው ተጠቁሟል፡፡
ከዓለም ባንክ አመራሮች “አውሮፓውያን አንተን የመሳሰሉ ጥቁር አፍሪካውያንን በከፍተኛ የስልጣን ቦታ ተቀምጠው ማየት አይፈልጉም” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ዶ/ር ዮናስ ይናገራሉ፡፡
ጉዳዩን ወደ አሜሪካ ፍ/ቤት ለመውሰድ አስበው እንደነበር የሚገልፁት ዶ/ር ዮናስ፤ የዓለም ባንክ ያለመከሰስ መብት እንዳለው በመረዳታቸው ተቋውሟቸውን በተለያየ መንገድ ለመግለፅ መወሰናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የመጀመሪያ አማራጭ ያደረጉት ደግሞ የረሃብ አድማ ማድረግ ነው፡፡ ላለፉት ሁለት ሳምንታትም በረሃብ አድማ ላይ የሚገኙት ዶ/ር ዮናስ፤ ይህን ተቋውሟቸውንም ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እያሳወቁ ነው፡፡
የዶ/ር ዮናስን ተቃውሞ የደገፉት የቀድሞ የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ኮኔት ቹሲሊኒ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በፃፉት ደብዳቤ “ዜጋዎን በባዕድ ሃገር በረሃብ አድማ ከመሞት ይታደጉ” ብለዋል፡፡
ዶክተሩ ባለፉት 40 ዓመታት በአሜሪካ ሲኖሩ ኢትዮጵያዊነታቸውን ክደው አሜሪካዊ ዜግነት ማግኘት እየቻሉ አላደረጉም ሃገራቸውን በተግባር የሚወዱ ሰው ናቸው ያሉት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ፤ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጉዳይ ይመለከትዎታልና መንግስትዎ ነገሩን በአንክሮ ተመልክቶ፣ ድምፁን እንዲያሰማ እጠይቃለሁ” ብለዋል፡፡
ለዚህ ሃገር ወዳድና ለሰብአዊ ክብሩና ለማንነቱ የሚታገል ምሁር፣ የኢትዮጵያ መንግስት ድምፅ ሊሆነው ይገባል ያሉት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ፤ ይህን ግልፅ የሆነ ዘረኝነት የዓለም ማህበረሰብ በይፋ እንዲቃወመውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዶ/ር ዮናስ ብሩ በዓለም ባንክ የንፅፅሮሽ ፕሮግራም ውስጥ ም/ስራ አስኪያጅ ሆነው በቆዩባቸው ያለፉት 7 ዓመታት ከ80 በላይ በሆኑ የዓለም ሃገራት ተዘዋውረው ማገልገላቸውን መረጃው ይጠቁማል፡፡ የአለም ባንክ የዓለምን ሁኔታ እየገመገመ በየ4 ወሩ የሚያወጣውን በጥናት ላይ የተመሰረተ መረጃ፤ አሃዞችን በመተንተን የሚያጠናክሩትና ሂደቱን የሚመሩት ዶ/ር ዮናስ እንደነበሩ ተመልክቷል፡፡
ይህ ስራቸውም ተገቢውን እውቅናና ክብር እንዳያገኝ በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት አድልዎ መደረጉን በመቃወም ላለፉት 2 ሳምንታት በረሃብ አድማ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ የመሰረቱት የኢኮኖሚ አማካሪ ጉባኤ ማቋቋሚያ ሰነድን ካዘጋጁ ኢትዮጵያውያን መካከልም ዶ/ር ዮናስ ብሩ ይገኙበታል ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያዊው የአለም ባንክ ኃላፊ ዘረኝነትን በመቃወም የረሃብ አድማ ላይ ይገኛሉ ተባለ
Read Time:1 Minute, 44 Second
- Published: 6 years ago on February 5, 2019
- By: maleda times
- Last Modified: February 5, 2019 @ 3:16 pm
- Filed Under: Ethiopia
Average Rating