- በፖለቲካ አለመረጋጋቱን ሳቢያ ግብር የማይከፍሉ በርካታ ግብር ከፋዮች መኖራቸው ተገልጿል
- ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች እንዳይገቡ የሕግ ማሻሻያ ሊደረግ ነው
ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ ከሚደረገው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በተቃራኒው ሰፊ የሆነ ‹‹የጨለማ ኢኮኖሚ›› እንቅስቃሴ መኖሩንና ሁሉም የመንግሥት መዋቅር ተናቦና ተቀናጅቶ መዋቅሩን ካላፈራረሰው፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ከማድረስ አልፎ ፖለቲካዊ አንድምታ ሊኖረው እንደሚችል የገቢዎች ሚኒስትሯ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሯ የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ነው በህቡዕ የሚደረግ የጨለማ ኢኮኖሚ (Underground Economy) እንቅስቃሴ፣ በአገሪቱ መንሰራፋቱን የተናገሩት፡፡ ‹‹ይህ የጨለማ ኢኮኖሚ መሠረቱ ሰፊ ነው፡፡ የግብር ሥርዓቱ አያውቀውም፡፡ በመሆኑም የንግድ ፍትሐዊነትን አዛብቷል፡፡ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን የግብር ገቢ በመሰወር ኢኮኖሚው እንዳይጎለብት በማድረግ በአገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፤›› ሲሉ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡
ይህ ሥውር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ (በእሳቸው አጠራር የጨለማው ኢኮኖሚ) አሁንም ሙሉ በሙሉ እየተንቀሳቀስ እንደሚገኝ፣ ነገር ግን ሰንሰለቱን ለመበጠስ መንግሥት በተቀናጀ ሁኔታ ስትራቴጂ ነድፎ ተግባራዊ ዘመቻ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡
ከዚህ አደገኛ እንቅስቃሴ በተጨማሪ ላለፉት በርካታ ዓመታት ሕግን ተገን አድርጎ ተግባራዊ ሲሆን የቆየው የቀረጥ ነፃ መብት ዓላማው፣ ኢንቨስትመንትን በማበረታታት የጎላ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ውጤት ለመፍጠር ቢሆንም ሲከናወን የቆየው ግን በተቃራኒው የአገሪቱን ኢኮኖሚ ማድማት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የቀረጥ ነፃ መብት የማበረታቻ ዕድል አፈጻጸምን በተመለከተ ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ ያሉትን መረጃዎች በመመርመር የተገኘው ውጤት አስደንጋጭ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ ወ/ሮ አዳነች፣ በተጠቀሱት ዓመታት የተሰበሰበው አጠቃላይ የግብር ገቢና የቀረጥ ነፃ መብት ከሞላ ጎደል እኩል መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በተጠቀሱት ዓመታት የተሰበሰበው አጠቃላይ የግብር ገቢ 519 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ በእነዚህ ዓመታት የተፈቀደው የቀረጥ ነፃ መብት 517 ቢሊዮን ብር እንደነበር አስረድተዋል፡፡
ከፍተኛ ግብር መክፈል የነበረባቸውን ወደ ጎን ትቶ ሊበረታታና ሊደገፍ የሚገባውን ነጋዴ የማዋከብና የማስጨነቅ እንቅስቃሴ እንደነበር የገለጹት ሚኒስትሯ፣ እነዚህ በግብር መዋቅሩ አድልኦ ሲደረግላቸው የቆዩ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች አሁንም ሥርዓተ አልበኝነት እንደሚታይባቸው አስታውቀዋል፡፡
እነዚህ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ፖለቲካዊ ሁኔታ እንደ ዕድል ሊጠቀሙበት እንደሚፈልጉ የተናገሩት ሚኒስትሯ ግብር መክፈል ያቆሙ መኖራቸውን፣ ግብር እንዳይከፍሉ ከለላ የተሰጣቸው በሚመስል ሁኔታ ከፍተኛ የግብር ውዝፍ ያለባቸው በምርመራ መገኘታቸውን፣ ግብር የመሰብሰብ ሒደቱን ከፖለቲካዊ ሁኔታዎች ጋር ለማስተሳሰር የማመፅ ምልክቶች ባለፉት ስድስት ወራት እንደገጠሟቸው አብራርተዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ እነዚህ ግብር ከፋዮች ለዓመታት ሳይከፍሉ የታለፉትን ውዝፍ ግብር እንዲከፍሉ ቁርጠኛ እንቅስቃሴ በማድረግ፣ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ማስከፈል መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
የቀረጥ ነፃ መብት ተግባራዊ የተደረገበት አግባብና ውጤቱን በተመለከተ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ የቀረጥ ነፃ መብት በመጠቀም ዕድሉ የተሰጣቸው ግብር ከፋዮች መብቱ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ማድረጋቸውን በተመለከተ፣ በመካሄድ ላይ ያለው ጥናት ባይጠናቀቅም በአብዛኛው ግን ለታለመለት ጥቅም አለመዋሉን ገልጸዋል፡፡
ሁለት ሺሕ የማይሞላ ሕዝብ በሚኖርባት የአፋር ከተማ 55 ዓለም አቀፍ ሆቴሎችን ለመገንባት ለ43 ሰዎች የቀረጥ ነፃ መብት የተፈቀደ ቢሆንም፣ ‹‹ለማስመሰል ሲባል እንኳን›› የተደረገ አንድም ግንባታ አለመገኘቱን ገልጸዋል፡፡ ሆቴሎችን ለመገንባት የቀረጥ ነፃ መብቱ ከተሰጣቸው መካከል አንዱ ግለሰብ ብቻ 28 ጊዜ የሆቴል ዕቃዎችንና የግንባታ ብረት ማስገባቱን አስረድተዋል፡፡
በሕጉ 34 መሥፈርቶች የቀረጥ ነፃ መብት እንደሚያስገኙ መዘርዘሩን የተናገሩት ሚኒስትሯ፣ ከሌሎች አቻ አገሮች ጋር በማነፃፀር በተደረገው ጥናት በየትኛውም አገር እንዲህ ዓይነት ልቅ የቀረጥ ነፃ መብት አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡
‹‹የአገር ሀብት በዚህ መልኩ እንዲበዘበዝ ያደረግነው እንዴት ነው የሚለውን ሁላችንም መመለስ ይገባናል፤›› ሲሉ ሕግ አውጪውን ፓርላማም በምፀት ወረፍ አድርገዋል፡፡
በአገሪቱ የሚስተዋለውን የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹እንደምታስቡት አይደለም ውስብስብ ነው፡፡ ኮንትሮባንድ በሕጋዊ መንገድ ነው ሲከናወን የቆየው፡፡ የመንግሥት አመራሮችና መዋቅሮች ጭምር የሚሳተፉበት ነው፡፡ እነዚህን ድርጅቶች እንዳትፈትሿቸው የሚል ሰርኩላር ደብዳቤ በመሥሪያ ቤታችን ውስጥ አግኝተናል፤›› ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ደሃው ማኅበረሰብ ሕግ እየጣሰ መሆኑን ሳይረዳ እንዲሳተፍ በማድረግ እንደሚፈጸምም ተናግረዋል፡፡ መፍትሔው ሰንሰለቱን ለመበጠስ ማጥናትና ሌብነትን የመጠየፍ እሴት ባለቤት የሆነውን ሰፊውን ማኅበረሰብ ማንቀሳቀስ እንደሆነ አሳስበዋል፡፡ ሰሞኑን የተያዘው ሰባት ኪሎ ግራም ወርቅ ከአገር ሊወጣ መሆኑን የዚህ እሴት ባለቤት ከሆኑ ዜጎች በደረሰ ጥቆማ፣ ከጅማሮ አንስቶ ተጠርጣሪዎቹ እጅ ከፍንጅ እስከተያዙበት ሰዓት ድረስ ክትትል መደረጉን የተናገሩት ሚኒስትሯ፣ ሕግ የማስከበር ተልዕኮውን በስኬት ለመወጣት የመከላከያ ሠራዊቱ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 442 ግለሰቦች በኮንትሮባንድ ድርጊት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡
ወደ አገር እየገቡ ያሉ ተሽካርካሪዎች ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ የመሆናቸው ሚስጥር የቀረጥ ሥርዓቱ ይኼንን የሚያበረታታ እንደሆነ፣ ድምር ውጤቱ ግን የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪውን የሚጎዳና ለሚገቡት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችም ከሚሰጡት አገልግሎቶት አንፃር ሲታይ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ የሚያመዝን መሆኑን በመጥቀስ፣ ከምክር ቤቱ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራርያ ኢትዮጵያ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ማራገፊያ መሆኗን አስረድተዋል፡፡
ይኼንን በመረዳትም የሕግ ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ አዲስ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር እንዲገቡ ለማበረታታት የቀረጥ ታሪፍ ማሻሻያ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት የተሰበሰበው አጠቃላይ የግብር ገቢ 98.6 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ ለመሰብሰብ ታቅዶ ከነበረው 122.1 ቢሊዮን ብር በ20 በመቶ ዝቅተኛ እንደሆነና ካለፈው ዓመት በ8.6 በመቶ እንደሚበልጥ ተገልጿል፡፡
Average Rating