የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሠራተኞችን በሕግ የመዳኘት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ገፎ የነበረና ባለሥልጣኑ ከአሥር ዓመታት በላይ ሲጠቀምበትና ሲያስፈራራበት የነበረው ደንብ ቁጥር 155/2000፣ ሕገ መንግሥቱን ተቃርኖ እንዳገኘው የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ አስታወቀ፡፡
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 37(1)፣ ‹‹ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት አለው፤›› የሚለውን የማይገሰስና የማይጣስ የመብት ድንጋጌ፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ተብሎ ይጠራ የነበረው ተቋም በተቃራኒው በደንብ ቁጥር 155/2000 ተግባራዊ ሲያደርገው ከርሟል፡፡
ባለሥልጣኑ በደንቡ ውስጥ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት የሚሠራ ማንኛውም ሠራተኛ፣ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር በሙስና ከጠረጠረውና እምነት ካጣበት ወደ መደበኛውን የዲሲፕሊን ዕርምጃ አፈጻጸም ሳይከተል ዕርምጃ ይወስዳል፡፡ ዕርምጃው በየትኛውም የፍርድ አካል ውሳኔ ቢያገኝ ወደ ሥራ የመመለስ መብት የለውም፤›› በማለት የዜጎችን የማይጣስ ሕገ መንግሥታዊ መብት ሲጥስ ቆይቷል፡፡
የደንብ ቁጥር እየተጠቀሰ ዕርምጃ የተወሰደባቸው ሠራተኞች ከፍርድ ቤት ውጪ የሚሄዱበት የፍትሕ ቦታም ሆነ አካል ባለመኖሩ፣ የመጨረሻ ዕጣ ፈንታቸው አድርገው በመውሰድ ተጠቂ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ ደንቡ የአገሪቱ የበላይ ሕግ የሆነውን ሕገ መንግሥት የጣሰ መሆኑ በአደባባይ ጭምር ሲገለጽና እንደ ማስፈራሪያ መጠቀሚያ ሲሆን፣ የሕግ ባለሙያዎችም ሆኑ ለዜጎች መብት የሚከራከሩ ወገኖች እንዳላዩና እንዳልሰሙ ሲያልፉት የከረመ ቢሆንም፣ አንድ የባለሥልጣኑ ሠራተኛ ግን ደንቡ ሕገወጥ መሆኑንና ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን ሆኖ ስላገኘው ጉዳዩን ወደ ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር አስተዳደር ፍርድ ቤት ወስዶታል፡፡
የግለሰቡን አቤቱታ የመረመረው የሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር ፍርድ ቤት፣ ክርክሩን ከተመለከተ በኋላ ባለሥልጣኑ በግለሰቡ ላይ የወሰደው ከሥራ የማሰናበት ውሳኔ፣ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37 (1) ድንጋጌ ጋር የሚጋጭ መሆኑን ጠቅሶ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት ለጉባዔው ልኮታል፡፡
አጣሪ ጉባዔውም ባደረገው ምርመራ የባለሥልጣኑ ደንብ ቁጥር 155/2000 ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37 (1) ድንጋጌ ጋር እንደሚቃረን በማረጋገጡ፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም የመስጠት ሥልጣን ላለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳብ ማቅረቡን፣ የጉባዔው የኮሙዩኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ይርጋለም ጥላሁን ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡
ቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ተብሎ ይጠራ የነበረው አንድ ተቋም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አዲስ ባዋቀሩት ካቢኔ መሠረት በአዋጅ ቁጥር 1097/2011 የገቢዎች ሚኒስቴርና ተጠሪነቱ ለገቢዎች ሚኒስቴር የሆነ የጉምሩክ ኮሚሽን በመሆን ለሁለት ተከፍሎ መቋቋሙ ይታወሳል፡፡
Average Rating