የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በግማሽ ዓመት ውስጥ ከ114 ሚሊዮን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ። አስተዳደሩ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ 88 ሚሊዮን ብር በግማሽ ዓመት ለማትረፍ ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም አሁን ከታቀደው በላይ 114 ሚሊዮን ማግኘቱንና ይህም የዕቅዱን 127 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ ተናግሯል።
አስተዳደሩ ጨምሮ እንደገለፀው ትርፉ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ እንደሆነና በታሪክም ትልቁ የግማሽ ዓመት ትርፍ የተመዘገበበት ወቅትም እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በባለፈው ዓመት 86 ሚሊዮን ብር አስተዳደሩ ማትረፉን ለማወቅ ተችሏል። በዚህ የበጀት ዓመት አጋማሽ ላይ ለተመዘገበው ከፍተኛ ትርፍ የወረቀት ሎተሪ ሽያጭ መጨመርን እንደምክንያት የሚያነሳው አስተዳደሩ ከበርካታ ተዛማጅ ጉዳዮች የሚሰበሰቡ ገቢዎችንም በአግባቡ መሰብሰብ ስለታቸለ እንደሆነ አስታውቋል።
ከወረቀት ሎተሪ ሽያጭ በተጨማሪ ማንኛዉንም ዓይነት በኢትዮጵያ ውስጥ በአገር ዐቀፍ ደረጃ የሚከናወኑ ዕጣ ነክ እንቅስቃሴዎችን በመቆጣጠርና ከዘርፉም እስከ 15 በመቶ ገቢ እንደሚያገኝ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያው ገዛኸኝ ይልማ “ከቢራ ፋብሪካዎች እና ከባንኮች በኩል ለተጠቃሚዎች ከሚደረሱ ሽልማቶች የዕቃዎቹን ጠቅላላ ዋጋ 15 በመቶ ድርጅቶቹ ለብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ይከፍላሉ” ብለዋል። ከዚህም ጋር በተያያዘ አስተዳደሩ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው እና የቢራ አምራች ድርጅቶች ሽልማት ማዘጋጀት እንዳይችሉ የሚደነግገው አዋጅ በተወሰነ ደረጃ የአስተዳደሩን ገቢ ሊቀንሰው ይችላል የሚል ፍራቻ እንዳለ የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያው ገልጿል።
አስተዳደሩ በራሱ ከሚያከናውናቸው የሎተሪ ሽያጭ ውጭ በግሉ ዘርፍ ላሉ እና ሎተሪ በማጫወት ሥራ ላይ ለተሰማሩ፣ የልማት ማኅበራት ሆነው ቶምቦላ ሎተሪ ለሚያዘጋጁ እና ገቢ ለማሰባሰብም ፈቃድ እንደሚሰጥ የሚታወቅ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ከኳስ ስፖርት ጋር በተያያዘ ለሚሠሩ አቋማሪ ድርጅቶች ፈቃድ ምስጠቱንም ከአስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። ከዚህም ጋር በተያያዘ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ በአጭር መልዕክት አማካኝነት ከሚደረጉ ዕጣዎች ገቢ በአግባቡ እየሰበሰበ እንደሚገኝና ከዚህ ጋር ተያይዞ ለሚቄዶንያ የአረጋዊያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ለሚደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ የአጭር መልዕክት ምንም ዓይነት ገቢ እንደማይሰበስብ አስታውቋል። ከማዕከሉ ጋር በተያያዘ ብሔራዊ ሎተሪ እያደረገ ያለውን ገዛኸኝ ሲገልጹ “ድርጅታችን የሕዝብ እንደሆነ ማሳያ ከመሆኑም በላይ በተለያዩ አገራዊ ጥሪዎች ግንባር ቀደም መሆኑንም ያመላክታል” ብለዋል።
ብሔራዊ ሎተሪ ከጠቅላላ ገቢው 43 በመቶ የሚሆነውን መልሶ ለሎተሪ ባለ ዕድለኞች ለሽልማት እንደሚያውለው የታወቀ ሲሆን እንዲሁም ከጠቅላላ ገቢው በየዓመቱም 21 በመቶ የሚሆነውን ወደ መንግሥት ካዝና ፈሰስ እንደሚያደርግ ለማወቅ ተችሏል። በአዋጅ ቁጥር 256/86 መሰረት አስተዳደሩ ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ ገቢዎች ሚኒስቴር እንደሆነም ታውቋል።
Average Rating