በሙስና ወንጀል ተከሰው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ የቀረበባቸው ኢሣያስ ዳኘው በ50 ሺሕ ብር ዋስ እንዲፈቱ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የካቲት 7 ቀን በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ወንጀል ችሎት የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ተከሳሽ ላይ ባቀረበው ክስ በኢትዮ ቴሌኮም የኤን.ጂ.ፒ.ኦ ዳይሬክተር ሆነው በሚሠሩበት ወቅት ከሌሎች ግብረ አበሮች ጋር በመሆን ኢዲም ከተባለ አማካሪ ድርጅት ጋር ያለምንም ጨረታና የውል ስምምነት 12 ለሚሆኑ የድርጅቱ ሠራተኞች ምንም ዓይነት ሥራ ሳይሠሩ በሰዓት ከ125-150 ዶላር በሳምንት ደግሞ ለስድስት ቀን ወይም ለ44 ሰዓት ከ2001 ጀመሮ እስከ 2005 ያለአግባብ ክፍያ በመክፈል እንዲሁም እንዲሁም ለሥራ አስኪያጇ ከ500 ሺሕ ብር በላይ የቤት ኪራይ እንዲከፈል አድረገዋል፤ ከአማካሪ ድርጅቱ ጋር የተደረገው ውል ከሕግና መመሪያ ውጭ እንዲሻሻልና የሥራ ማጠናቀቂያ ግምገማ ሰነድ ሳይቀርብና በሚመለከተው አካል ሳይረጋገጥ ከአጠቃላይ የውል ዋጋ ለመጠባበቂያ የተያዘ (Retention payment) ለአማካሪው ድርጅት ሥልጣኑን አለአግባብ በመገልገል 104 ሺሕ 495 ዶላር ክፍያ እንዲፈፅም አድርገዋል ሲል ክሱን አሰምቱዋል።
ተጠርጣሪው ላይ በተከፈተው አዲስ የምርመራ መዝገብ ተጨማሪ የሰውና የሰነድ መረጃዎችን ለማሰባሰብ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። ተጠርጣሪው በዋስ ቢወጡ ማስረጃዎችንና ምስክሮችን ሊያጠፋ እንደሚችሉ በመግለፅ የዋስተና መብታቸው እንዲከለከል አመልክተዋል።
ተከሳሽም በተከላካይ ጠበቃቸው በኩል ተፈፀመ የተባለው የወንጀል ድርጊት 2001 እስከ 2005 ባለው ጊዜ መሆኑን በመግለጽ ደንበኛቸው ከሦስት ወር በላይ በእስር ላይ ቆይተው የዋስትና መብታቸውን ባስከበሩበት ሁኔታ ጉዳዩ ባለቀ ሰዓት አዲስ ምርመራ መዝገብ መቅረቡ ተገቢ አለመሆኑን ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት ሆን ተብሎ ተጠርጣሪውን በእስር ለማቆየት የቀረበ ክስ በመሆኑ ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር በመመልከት መዝገቡን ከመረመረ በኋላ ኢሳያስ ዳኘው በ50 ሺሕ ብር ዋስ እንዲወጡ ትእዛዝ ሰጥቷል፤ ከአገር እንዳይወጡም ለኢሚግሬሽን እግድ በመስጠት ውሳኔውን አስተላልፏል።
Average Rating