ዜጎች በሕክምና ወቅት የሚጠየቁትን ከፍተኛ ገንዘብ ያስቀራል የተባለው እና መደበኛ ያልሆነ ዘርፍ ውስጥ የሚካተቱ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚያቅፈው አዋጅ ሊፀድቅ እንደሆነ ታወቀ። አዋጁ በእርሻና በሌሎች የግብርና ሥራዎች፣ በአርብቶ አደርነት፣ በከፊል አርብቶ አደርነት፣ በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት የተሠማሩና የጎዳና ተዳዳሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የሚጠበቀው ይህ አዋጅ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን አንደማይመለከት ለማወቅ ተችሏል።
መደበኛ ባልሆነ ዘርፍ የተሰማራ ማንኛውም ሰው የማኅበረሰብ ዐቀፍ የጤና መድህን አባል እንዲሆን አዋጁ የሚያስገድድ ሲሆን፤ የአባልነት ምዝገባውም ለአንድ ዓመት የሚፀና እና በየዓመቱ የሚታደስ ይሆናል። በዚህ የጤና መድኅን አባልነት ለመመዝገብ አባላት መዋጮ የሚከፍሉ ሲሆን የአባልነት መዋጮ የመክፈል አቅም ለሌላቸው ደግሞ በተናጠል ድጎማ እንደሚደረግ አዋጁ ይደነግጋል። ለዚህም ደግሞ የጤና መድኅኑ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኘው ከከፋይ አባላት፣ ከተናጠልና ከአጠቃላይ ድጎማ እንዲሁም ከልማት አጋሮች ከሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ መሆኑን አዋጁ ይጠቅሳል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በሚያጋጥሙ የገንዘብ ጉድለቶች ላይ የጤና መድኅኑን የሚያስተዳድረው መዋቅር ወጪውን እንደሚሸፍን በአዋጁ ላይ ተጠቁሟል።
በማኅበረሰብ ዐቀፍ የጤና መድኅን ውስጥ ለተካተቱ አባላት የሚሸፈነው የጤና አገልግሎት የጥቅም ማዕቀፍ በአገሪቱ ከሚሰጡ የጤና አገልግሎቶች ውስጥ ሲሆን በዝርዝር የሚገለፅ እንደሚሆንና፤ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትም ከክልል እና ከፌደራል አስፈፃሚ አካላት ጋር ውል የገቡ የግልና የመንግሥት የጤና ተቋማት እንደሚሆኑ ተገልጿል። አስፈፃሚ አካላትም በፌደራል ደረጃ የኢትዮጵያ የጤና መድኅን ኤጀንሲ ሲሆን በክልል ደረጃ ደግሞ የጤና መድኅን ሥርዓቱን የሚመራ ፣ የሚያስተባብር እና የሚያከናውን አካል ይሰየማል። አስፈፃሚው አካልም በተገባው የውል ስምምነት መሰረት ተጠቃሚዎች የሕክምና አገልግሎት በአግባቡ ማግኘታቸውን ማረጋገጥና በውሉ መሰረት በወቅቱ ክፍያ የመፈፀም ግዴታ አለባቸው። ከፌደራልና ከክልል አስፈፃሚ አካላት ጋር የተገባውን ውል በመጣስ ወንጀል በሚፈፅሙ ተቋማትና የጤና ባለሙያዎች ላይ አስፈፃሚ አካሉ ፍቃድ ከማገድ ጀምሮ በወንጀልና በፍትሕ ብሔር እንዲጠየቁ እንደሚያደርግ ተገልጿል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ጤና መድኅኑን ተገን በማድረግ ያልተገባ ጥቅም ለማዋል በሚንቀሳቀሱ የጤና ባለሙያዎች ላይ ከ50 እስከ 100 ሺሕ ብር የሚደረርስ የገንዘብ መቀጮ እና ከስድስት ወር እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ እስር እንደሚቀጣ ታውቋል።
በአዋጁ ላይ እንደተጠቆመው የማኅበረሰብ ዐቀፍ ጤና መድኅን ምክር ቤት በብሔራዊና በክልል ደረጃ እንደሚቋቋም የተገለፀ ሲሆን፤ ክልሎች ከክልልም በታች ባለ አስተዳደራዊ መዋቅር የማኅበረሰብ ዐቀፍ የጤና መድኅን ምክር ቤት ሊያቋቁሙ ይችላሉ። በብሔራዊ ደረጃ የሚቋቋመው ምክር ቤት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ሲሆን፤ የምክር ቤቱ አባላት ዝርዝርና አሠራር በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ይወሰናል።
Average Rating