. 1500 ሰዎች ተሳታፊ በሆኑበት ጥናት ከኢቢኤስ በመቀጠል ፋና ቴሌቭዥን፣ ኢቲቪ ዜና እና ቃና ቀዳሚውን ስፍራ ይዘዋል
. ሸገር ኤፍ ኤም ከሬዲዮ ጣቢያዎች ቀዳሚ ተደማጭ ሆኗል
ዋስ ኢንተርናሽናል የተባለ አገር በቀል ድርጅት ባለፉት ሦስት ወራት 12 ከተሞች ላይ ባደረገው ጥናት 33 በመቶ የገበያ ድርሻ በመያዝ ኢቢኤስ ከፍተኛ ተመልካች ያለው የቴሌቭዥን ጣቢያ መሆኑ ታወቀ።
የዛሬ ዐሥር ዓመት በውጭ ዜጎች የተመሰረተው ኢቢኤስ፤ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ፈቃድ ያገኘው ገና ባለፈው ዓመት ቢሆንም፤ በሚያስተላልፋቸው ፕሮግራሞቹ ከሁሉም ጣቢያዎች ቀዳሚ መሆኑን የዋስ ጥናት አሳይቷል።
በ14 ቴሌቭዥን ጣቢያዎች ላይ በተደረገው ጥናት 1500 ሰዎች ተሳታፊ ሲሆኑ፤ ከኢቢኤስ በመቀጠል ፋና ቴሌቭዥን፣ ኢቲቪ ዜና እና ቃና ቀዳሚውን ስፍራ ይዘዋል። የውጭ ፊልም በማሳየት የሚታወቀው ቃና የገበያ ድርሻው ሲቀንስ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ለብቻው የቴሌቭዥን ገበያው ተቆጣጥሮት የነበረው ኢቲቪ ዜና ተመልካቾቹ ቀንሰዋል።
ጥናቱ ከተካሄደባቸው ከተሞች መካከል አዳማ፣ አዲስ አበባ፣ ድሬ ዳዋ፣ ጎንደርና ባሕር ዳር ዋናዎቹ ሲሆኑ 738 ወንዶች እና 765 ሴቶችን አሳትፏል። በጥናቱ መሰረት ባለፉት ሦስት ወራት የኢቢኤስ ተመልካቾች ከ59 በመቶ ወደ 72 በመቶ ሲያድጉ፤ የኢቲቪ ዜና እና የአፍሪ ሄልዝ ተመልካቾች ቀንሰዋል። በሌላ በኩል አማራ ቲቪ፣ ናሁ ቲቪ እና አሻም ቲቪ አነስተኛ ተመልካች ያላቸው ሆነዋል።
በአዲስ አበባ ኢቢኤስ በ74 በመቶ ቀዳሚ ሲሆን ፋና (46 በመቶ)፣ ኢቲቪ ዜና (30 በመቶ) እና ቃና (28 በመቶ) ይከተላሉ። በአዲስ አበባ ከሁሉም አነስተኛ ተመልካች ያለው ጣቢያ ደግሞ ናሁ ቲቪ (4 በመቶ) ሆኗል።
በዕድሜ አኳያ ሲታይ፤ ከ50 ዓመት በላይ የሆናቸው መላሾች ኢቲቪ ዜናን ተመራጭ ሲያደርጉ፤ ከ49 በታች ያሉት ኢቢኤስ ቀዳሚ ምርጫቸው አድርገዋል። ብዙ ጊዜ በመከፈት ደረጃ ሲታይ ደግሞ፤ አዲስ ቲቪ የመጨረሻውን ደረጃ ሲይዝ ኢቢኤስ፣ ፋና ቲቪ እና ኢቲቪ ዜና ቀዳሚ ሆነዋል።
በገበያ ድርሻ ሲታይ ደግሞ ኢቢኤስ አንድ ሦስተኛው የቴሌቭዥን ተመልካቾች ምርጫ በመሆን ቀዳሚ ሲሆን ፋና በ17 በመቶ፣ ቃና በ12 በመቶ እና ኢቲቪ ዜና በ10 በመቶ ይከተላሉ። ጄቲቪ በ6 በመቶ እና ዋልታ በ5 በመቶ ቀጣዩን ደረጃ ይዘዋል።
በአንፃሩ ገበያ ድርሻቸው በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ ኢቲቪ ዜና ቀዳሚ ሲሆን የቃና እና አፍሪ ሄለዝ ድርሻም ሲወርድ ተስተውሏል። በሌላ በኩል በፕሮግራም ደረጃ ሲታይ 57 በመቶ መላሾች የመረጡት የቤተሰብ ጨዋታ ቀዳሚ ሲሆን ዜና በ34 በመቶ፣ እሁድን በኢቢኤስ በ36በመቶ፣ ሰንሰለት በ37 በመቶ እንዲሁም ሞጋቾች ድራማ በ33 በመቶ ይከተላሉ።
ከሬዲዮ ጣቢያዎች ደግሞ ሸገር ኤፍኤም 28 በመቶ የመላሾችን ቀልብ በመሳብ ቀዳሚ ሲሆን ፋና ኤፍኤም በ26 በመቶ ሁለተኛ ሆኗል። ብስራት ኤፍኤም በ25 በመቶ ኤፍኤም አዲስ 97 ነጥብ 1 በ11 በመቶ ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።
ከሬዲዮ ፕሮግራሞች ስፖርት (39 በመቶ) ቀዳሚ ሲሆን ዜና (36 በመቶ) ሙዚቃ እና ታዲያስ አዲስ በ8 በመቶ ይከተላሉ። ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ደግሞ ፌስቡክ (84 በመቶ) የመጀመሪያውን ደረጃ ሲይዝ ቴሌግራም እና ቫይበር ቀጣዩን ደረጃ ይዘዋል።
ጥናቱን ያደረገው ዋስ ከተመሠረተ 26 ዓመት ሲሆነው ከ6 ወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን በተመለከተ ነዋሪዎች ያላቸውን አስተያየት በጥናት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
Average Rating