የእውቁ የህወሓት ታጋይና የትግርኛ ዘፋኝ ብርሃኑ ጋኖ እናት በችግር ጐዳና ላይ መውጣታቸው ተጠቆመ፡፡ ወይዘሮዋ 6 ልጆቻቸውን ለህወሓት ትግል ገብረው ጧሪ ቀባሪ በማጣት፣ በአሳዛኝ ሁኔታ በመቀሌ ጐዳና ላይ መውደቃቸውንና በቅርቡ ወደ ተንቤን መሄዳቸውን ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁት አቶ አርአያ ተስፋማርያም ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
የህወሓት ታጋዮች በወኔ ወደ ትግል እንዲገቡ ሲቀሰቅሱና ሲያነሳሱ ከነበሩት ድምፃዊያን ታጋዮች መካከል አንዱ የሆነው ብርሃኑ ጋኖ፣ ለትግሉ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለ ቢሆንም ህወሓት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ እንደ ሸንኮራ ተመጥጠው ከተተፉትና ከተገፉት ታጋዮች አንዱ መሆኑን አቶ አርአያ አስታውሰዋል፡፡
ከስድስት አመት በፊት ከትግራይ ወደ ሱዳን የባህልና የኪነት ቡድን አሳፍሮ ይጓዝ በነበረ መኪና ላይ በደረሰ አደጋ ህይወታቸውን ካጡት ድምፃዊያን መካከል አንዱ ብርሃኑ ጋኖ ሲሆን፤ በተለይም እሱ ከሞተ በኋላ ወላጅ እናቱን የት ወደቅሽ ብሎ የሚጠይቃቸው ወዳጅ ዘመድ በማጣታቸው፣ በመቀሌ ጐዳና ላይ ለልመና ተዳርገው እንደነበር የቅርብ ምንጮቹን ጠቅሰው አቶ አርአያ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
የታጋዩና ድምፃዊው እናት በአሁን ሰዓት ከመቀሌ ጐዳና ወደ ተንቤን መሄዳቸውን የጠቆሙት አቶ አርአያ፤ ኩዌት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን አዋጥተው በላኩላቸው ጥቂት ገንዘብ ህይወታቸውን ለማቆየት እየተፍጨረጨሩ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ብርሃኑ (ጋኖ) በተለይ በቅብብሎሽ ባቀነቀነው ዘፈኑ ብዙ በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች ትግሉን እንዲቀላቀሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ቢያደርግም፣ ከሥርዓቱ እንኳን ሊጠቀም ጭራሽ ተገፍቶ፣ በግሉ ህይወቱን ለመምራት በትግል ላይ እያለ ነው በመኪና አደጋ ህይወቱ ያለፈው፡፡
የወላድ መካን የሆኑት የእነ ብርሃኑ እናት፣ ስድስት ልጆቻቸውን ለሕወሓት ትግል ገብረው ፣የማምሻ እድሜያቸው በመከራ የታጀበ መሆኑ እንደሚያም የገለፁት አቶ አርአያ፤ እኚህ እናት የበርካታ የትግል ሰለባ ልጆች እናቶች ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡
ጥቂት ባለስልጣናት እስከ 10 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቪላ ቤት ለልጆቻቸው ሳይቀር ሰርተው እየኖሩ፣ ለትግሉ መሳካት አጥንትና ደም የገበሩ ወጣቶች እናቶች ሜዳ ላይ ወድቀው መከራ ሲገፉ እንደማየት የሚያስቆጭ ነገር የለም ያሉት አቶ አርአያ፤ የብርሃኑ ጋኖን እናት የመጨረሻ የህይወት ዘመን ለማሻሻል ሰብአዊነት የሚሰማው ወገን ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ተማፅነዋል፡፡
“6 ልጆቻቸውን ለህወሓት ትግል የገበሩ እናት ጐዳና ላይ ወድቀዋል”
Read Time:1 Minute, 21 Second
- Published: 6 years ago on February 23, 2019
- By: maleda times
- Last Modified: February 23, 2019 @ 1:25 pm
- Filed Under: Ethiopia
Average Rating