የአዲስ አበባ ወንዞችና የወንዞች ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ሐሙስ የካቲት 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ሸራተን ሆቴል ፊት ለፊት ከሚገኘው ከቀድሞ የፌዴራል ፖሊስ ጋራዥ ግቢ ውስጥ በተደረገ የማስጀመርያ መርሐ ግብር ተጀመረ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ይገኙበታል ተብሎ ቢጠበቅም ሌላ ጉዳይ አጋጥሟቸው እንዳልተገኙ በተገለጸበት መድረክ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የፕሮጀክቱን መጀመር አብሥረዋል፡፡
አዲስ አበባን እንደ ስሟ ለማድረግ አልሞ የተነሳ ነው በማለት ስለፕሮጀክቱ ያስተዋወቁት ምክትል ከንቲባው፣ የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ በልማት ምክንያት ከሥፍራው የተነሱ ነዋሪዎች በዚህ ፕሮጀክት ዕውን መሆን እንደሚካሱ ገልጸዋል፡፡
ይኼ በ2.5 ቢሊዮን ብር በጀት በቫርኔሮ ኩባንያ ተግባራዊ የሚሆነው ፕሮጀክት የሙከራ ፕሮጀክት ሲሆን፣ ከእንጦጦ ጀምሮ እስከ ቀበናና አቃቂ ወንዞች ድረስ ለሚዘረጋው ሰፊ ፕሮጀክት በማሳያነት እንደሚያገለግል የምክትል ከንቲባ ታከለ የቴክኒክ አማካሪ ወ/ሮ መስከረም ታምሩ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ምንም ዓይነት ዲዛይን እንዳልተሠራለት የገለጹት ወ/ሮ መስከረም፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩንና የምክትል ከንቲባውን ሐሳብ በመውሰድ በተሠራ ንድፍ ከኮንትራክተሩ ጋር ውል መፈጸሙን አስረድተዋል፡፡
በዚህም መሠረት ኮንትራክተሩ ቫርኔሮ የፕሮጀክት ዲዛይን ሠርቶ በየጊዜው እያስገመገመ ፕሮጀክቱን እንደሚያከናውን ገልጸው፣ ካሁን ቀደም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተሠርቶ የነበረውን የአዋጭነት ጥናት መነሻ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡ በዚህ ሒደት ተቋራጩ የሚያስፈልጉ ሥራዎችን በሚያስፈልጉበት ሥፍራ እንደሚያከናውን በመግለጽ፣ እየፈረሱ የሚሠሩ ቦታዎች ቢኖሩ እንኳን በራሱ ኪሳራ ይወጣዋል ሲሉ ወ/ሮ መስከረም ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ሙሉ ለሙሉ ወደ ትግበራ ሲገባ ከ29 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ የተገመተ ሲሆን፣ ከዚህ የሙከራ ፕሮጀክት ትግበራ በኋላ የሌሎች ወንዝ ዳሮች ሥራ ጨረታ እየወጣ ለተቋራጮች ይሰጣል ተብሏል፡፡
እንደ ወ/ሮ መስከረም ገለጻ የዚህ ፕሮጀክት ዲዛይን የሚሠራው በቫርኔሮ ሲሆን፣ የሚገነባውም ራሱ ቫርኔሮ ነው፡፡ ይሁንና የፕሮጀክት አማካሪ ተቀጥሮ ሥራውን እንደሚከታተልም ተነግሯል፡፡ በአንድ ዓመት የሚያልቅ ፕሮጀክት እንደሆነም አማካሪዋ አክለዋል፡፡
ነገር ግን የሰፊው ፕሮጀክት መጀመር የዚህኛውን መጠናቀቅ እንደማይጠብቅ በመግለጽ፣ ሙሉ በሙሉ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ሦስት ዓመታት ይፈጃል ሲሉ ወ/ሮ መስከረም አስረድተዋል፡፡
ካሁን ቀደም በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ውስጥ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ተቀርፀውና የመተግበርያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
ሆኖም ወ/ሮ መስከረም ካሁን ቀደም የነበሩት እየተቆራረጡ ተግባራዊ ሲደረጉ እንደነበር በመግለጽ፣ ይኼኛው ሁሉንም ያካተተና ያቀናጀ ፕሮጀክት እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
ይኼን ያክል ግዙፍ ፕሮጀክት ተግባራዊ የማድረግ ልምድ በአገር ውስጥ ስለሌለ በሙከራ መጀመር ማስፈለጉን ያከሉት አማካሪዋ፣ ቀጣዩ ፕሮጀክት ያስኬዳል ወይ የሚል ተሞክሮ የሚገኝበት ነው ብለዋል፡፡
‹‹እኛ ወንዞቻችንንና ፍሳሾቻችን ከየት እንደሚመጡ የምናውቀው ነገር የለንም፡፡ ገና እየተጠና ስንቆፍር በምናገኘው ነገር ሁሉ እየታየ ነው የሚሄደው፤›› በማለትም ተግባራዊነቱ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል አክለዋል፡፡
በየቦታው የሚኖሩት የወንዝ ዳርቻ ሥራዎች በየባህርያቸው የተለያዩ ሊሆኑ ቢችሉም ሁሉም የእግረኛ መረማመጃ፣ የብስክሌት ማሽከርከሪያ መስመርና የፍሳሽ መስመር ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡
በዚህ ፕሮጀክት ልምድ ለመቅሰም እንዲያስችልም 40 በመቶ የሚሆኑ የአገር ውስጥ ባለሙያዎችን ማሳተፍ ለሥራ ተቋራጮች በቅድመ ሁኔታ ተቀምጧል፡፡
Average Rating