ለረዥም ዓመታት አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ 44 የሰላም ባስ የመጓጓዣ አውቶቡሶች አገልግሎት መስጠት እንዳቆሙ ታወቀ። አውቶቡሶቹ ሥራቸውን ያቆሙት በጸጥታ ችግር፣ እርጅናና የመለዋወጫ እጥረት እንደሆነም ተገልጿል።
የሰላም ባስ አክስዮን ማኅበር ሲመሠረት 64 አውቶቢሶች የነበሩት ቢሆንም፣ አሁን ላይ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት አውቶቡሶች 14 ብቻ መሆናቸውም ታውቋል።
አንድ መጓጓዣ በየአምስት ዓመቱ የአገልግሎት ጊዜው እንደሚያበቃ የሚናገሩት የአክስዮን ማኅበሩ የቦርድ አባል ኪሮስ ጂራኔ፣ በየአምስት ዓመት አዳዲስ አውቶቡሶች ይገዛሉ ተብሎ የታቀደ ቢሆንም በወጋገን ባንክ፣ አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክና ዘመን ባንክ በኩል የውጭ ምንዛሪ ባለመፈቀዱ ምክንያት ተገዝተው መግባት የነበረባቸውን 20 አውቶቡሶች ግዢ መፈፀም እንዳልተቻለ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ሰላም ባስ ሥራውን ሲጀምር 17 የኢትዮጵያ ከተሞችን መዳረሻ አድርጎ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን አስር የጉዞ መስመሮች መቋረጣቸው ተገልጿል። አገልግሎት የተቋረጠባቸው መስመሮች አላማጣ፣ ደሴ፣ ወልዲያ፣ ማይጨው፣ አሶሳ፣ ነቀምት፣ ጅግጅጋ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ባሕር ዳር እና ጎንደር ሲሆኑ ምክንያቱም ከፀጥታ ችግርና በዚህም በሰላም ባስ ተጓዞች ላይ ሊደርስ ይችላል ከሚባለው የደኅንነት ስጋት ምክንያት መሆኑን አዲሰ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ካስተናገደቻቸው ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ጋር በተያያዘ ከመንግሥት ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል የፀጥታ ችግሩ ሰለባ ከሆኑት ንብረቶች መካከል አንዱ የሰላም ባስ አክሲዮን አውቶቡሶች ናቸው። በዚህም በብዙ መስመሮች አገልግሎቱን ለማቋረጥ የተገደደው ሰላም ባስ አሁን ላይ የደንበኞቹ ቁጥር እንደቀነሰ ታውቋል።
ከአዲስ አበባ- ድሬዳዋ፣ ሀረር፣ አርባ ምንጭ፣ ሚዛን ቴፒ፣ ሽሬ፣ አዲግራት እና ሀዋሳ የሰላም ባስ አውቶቡሶች በአሁኑ ወቅት አገልግሎት የሚሰጡባቸው መስመሮች ናቸው። ከአዲስ አበባ በደሴ ወልዲያ አድርጎ መቀሌ የሚወስደው የ783 ኪሎ ሜትር ጉዞም ባጋጠመው የፀጥታ ችግር ምክንያት መስመሩን ለመቀየር ተገዷል። በዚህም ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ኪሎ ሜትሮችን መጓዝ ግዴታ እንደሆነበትና በአፋር ክልል ዞሮ መሄድ በመጀመሩ የታሪፍ ማስተካከያ ማድረጉም ታውቋል።
ከዚህ ቀደም በነበሩ ተቃውሞዎች ጎንደር እና ጅማ ላይ ኹለት፣ ኹለት የሰላም ባስ አውቶቡሶች መቃጠላቸውን ከአክሲዮን ማኅበሩ የተገኘ መረጃ ያሳያል።
‹‹በአውቶቡሶቻችን፣ ሰራተኞቻችንና ደንበኞቻችን ላይ ጥቃት በተፈጸመባቸው ከተሞች ላይ አገልግሎት መስጠት አቁመናል›› ያሉት ኪሮስ ‹‹ጥቃት እንደማይደርስብን እርግጠኛ ስንሆን አገልግሎት መስጠት እንጀምራለን›› ብለዋል።
በጎንደርና ጅማ የደረሰውን የንብረት ውድመት ተከትሎ መንግሥት አስመዝግቡ ባለው መሰረት አስመዝግቦ ካሳ እየጠበቀ መሆኑንም ማኅበሩ አሳውቋል።
Average Rating