በአስከፊ ደረጃ ለረሃብ የተዳረጉ ተጎጂዎች ምሥል በርካቶችን አስቆጥቷል
ከፌዴራል እስከ ዞን ባሉ ኃላፊዎች ላይ ጥያቄ አስነስቷል
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞንና በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን መካከል በተከሰተ ግጭት ሳቢያ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ከሚገኙ ተረጂዎች በተጨማሪ ለ103‚221 አዲስ ተፈናቃዎች ዕርዳታ እንዲቀርብላቸው ከደቡብ ክልል ጥያቄ መቅረቡን፣ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ ኮሚሽኑ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ማቅረቡን ገልጿል፡፡ የሰላም ሚኒስትሯና ኮሚሽነሩ ዓርብ መጋቢት 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ወደ ጌዴኦ ዞን አቅንተዋል፡፡
ላለፉት ሦስት ዓመታት በሰላም ዕጦት ሲሰቃይ የከረመው የጌዴኦ ዞን፣ በተለይም ከአጎራባቹ የጉጂ ዞን ጋር በተፈጠረ ግጭት ሳቢያ ባለፈው ዓመት ከሁለቱም ወገን የተመዘገው የተፈናቃዮች ብዛት ከ900 ሺሕ በላይ ነበር፡፡ በተለይ በጌዴኦ ዞን የታየው ጉዳት እየተባባሰና በመጠለያ ጣቢያዎች የነበሩ ተጎጂዎችም ምግብና ሌሎችም የዕርዳታ ድጋፎች እንዳይደርሷቸው መንገዶችን የመዝጋት ድርጊቶች በመታየታቸው፣ በርካቶች ለአስከፊ የረሃብ አደጋ ተጋልጠው ቆይተዋል፡፡
በተለይ ከሰሞኑ በማኅበራዊ ትስስር ድረ ገጾች በምግብ እጥረት በአስከፊ ደረጃ የተጎዱ እናቶችና ሕፃናት ምሥሎች በመሠራጨታቸው በርካቶች ቁጣቸውን በመንግሥት ላይ እንዲሰነዝሩ፣ አንዳንዶችም ‹‹ለጌዴኦ ሕዝብ እንድረስለት›› የሚል ዘመቻ በመክፈት የዕርዳታ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ይታወቃል፡፡
ይህም ሆኖ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ለ54‚864 አዲስ ተጎጂዎች፣ እንዲሁም መጋቢት 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ለ48‚357 ተጨማሪ አዲስ ተጎጂዎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንዲያቀርብ ከደቡብ ክልል በተጻፈለት ጥያቄ መሠረት፣ በ48 ሰዓታት ውስጥ ድጋፍ መስጠቱን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡ በዚህም መሠረት 200 ኩንታል ብስኩት፣ 200 ኩንታል ዱቄት፣ 200 ኩንታል አተር ክክና 2,000 ሊትር ዘይት የክልሉ ደብዳቤ እንደደረሰ እንደተላኩ የገለጹት አቶ ደበበ፣ ከዚህ በተጨማሪም ከተረጂዎቹ ውስጥ 35 በመቶው ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡሮችና አጥቢ እናቶች እንደሚሆኑ በማሰብ፣ 200 ኩንታል አልሚ ምግብ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ መጓጓዙን አስታውቀዋል፡፡
ሆኖም ወርኃዊ የምግብ ዕርዳታ የሚያቀርበው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኅብረት በመሆኑ ደብዳቤ እንደተጻፈለትም ተጠቁሟል፡፡ ከዚህ ቀደም ከ208 ሺሕ በላይ በቋሚነት ዕርዳታ ያገኙ የነበሩ የጌዴኦ ዞን ተጎጂዎችን በመደበኛነት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሲደግፍ እንደቆየም ተገልጿል፡፡
ዕርዳታ በማቅረቡ ተግባር ላይ ከመንግሥት በተጨማሪ የዓለም ምግብ ፕሮግራምና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኅብረት ቢሳተፉበትም፣ በጌዴኦ ዞን የታየው አስከፊ የረሃብ አደጋ ግን መንግሥትን ከአገር ውስጥ ባሻገር ዓለም አቀፍ ወቀሳና ትችት ዳርጎታል፡፡ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃንም ይህንኑ አስተጋብተዋል፡፡ የጠቅላይ ሚነስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ለሰብዓዊ ጉዳዮች ትኩረት አለመስጠቱን፣ እንደ ጌዴኦ ባሉ አካባቢዎች ለአስከፊ ረሃብ የተጋለጡ እናቶችና ሕፃናትን ለመታደግ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለቱ እየተነገረና እየተዘገበ ቢሆንም፣ ኮሚሽኑ ጥያቄ ካልቀረበት በቀር በክልሎች አቅም የሚሸፈን ነው በማለት ምንም ማድረግ እንደማይችል አቶ ደበበ አስታውቀዋል፡፡ ጥያቄ ሲቀርብለት ግን ከ72 ሰዓታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የሚያስፈልገውን ዕርዳታ እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ለተጎጂዎች የመድረስና ድጋፍ የመስጠት አቅም እንዳለውም ተከራክረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ከአሥር ሚሊዮን በላይ የድርቅ ተጎጂዎች ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ በመንግሥት ወጪ ተደርጎ ድጋፍ ማግኘታቸውን ያወሱት አቶ ደበበ፣ አሁንም ቢሆን በአገሪቱ ከ8.3 ሚሊዮን በላይ የድርቅና የግጭት ተፈናቃዮችን ለመደገፍ ከተጠየቀው ከ1.34 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ መንግሥት ከወዲሁ 346 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን አስረድተዋል፡፡ መንግሥት ከ8.3 ሚሊዮን ተረጂዎች ውስጥ ከአምስት ሚሊዮን በላይ የድርቅ ተጎጂዎችን ለመደገፍ መዘጋጀቱን፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራምና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኅብረትም ከሦስት ሚሊዮን በላይ የግጭትና የረሃብ ተጎጂዎችን ለመደገፍ መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ2.7 ሚሊዮን በላይ በእርስ በርስ ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
የደቡብ ክልል አስተዳደር ስለጌዴኦ ዞን አስከፊ የረሃብ አደጋ ምን እንዳከናወነ ለመጠየቅም ሆነ በረሃብ ምክንያት ለጉዳት ተዳርገው ምሥላቸው በየድረ ገጹ ስለተሠራጨው ዜጎች ጉዳይ ጥያቄ ለማቅረብ ተሞክሮ፣ ለኅትመት እስከ ገባንበት ዓርብ መጋቢት 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ምሽት ድረስ ምላሽ አልተገኘም፡፡ የደቡብ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማንን በስልክ ለማናገር የተደረገው ጥረትም ውጤት አላስገኘም፡፡ ይህም ሆኖ የሰላም ሚኒስትሯና የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ሊቀመንበር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ ከኮሚሽነር ምትኩ ካሣ ጋር በሔሊኮፕተር ወደ ጌዴኦ ዞን ማቅናታቸው ቢሰማም፣ የጉብኝታቸውን ዝርዝር መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡
ምንም እንኳ የፌዴራል መንግሥት ከክልሎች አቅም በላይ መሆኑ ተገልጾለት ድጋፍ እንዲያቀርብ ካልተጠየቀ በቀር አልገባም ቢልም፣ ይኼ ግን ሁሌም ትክክለኛ ምክንያት እንዳልሆነ የሕግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ የክልሎች ሥልጣንና ራሳቸውን የማስተዳደር መብት፣ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ችግሮች ሲከሰቱ፣ በሁለት ክልሎች መካከል በሚከሰት ግጭትና አለመግባባት ውስጥ የፌዴራል መንግሥት ተገቢውን ድጋፍና ዕርዳታ የማቅረብ ብሎም ጣልቃ የመግባት ግዴታ እንዳለበት ያብራራሉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለጌዴኦ ዞን ተጎጂዎች በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚደረገው የድጋፍ ቅስቀሳና የዕርዳታ ማሰባሰቢያ የሒሳብ አካውንት በመክፈት የሚደረገው እንቅስቃሴ፣ ተገቢነት እንደሚጎድለው አቶ ደበበ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹እንቅስቃሴው አግባብነት የለውም፤›› ያሉት አቶ ደበበ፣ ‹‹የአካባቢውን ሕዝብ የመተሳሰብና የመደጋገፍ ልማድ ሊጎዳ ይችላል፣ እንዲሁም የሚሰበሰበው ገንዘብ የሚተዳደርበት ገለልተኛ አሠራርም በተገቢው ሁኔታ ስላልተዋቀረ እንቅስቃሴው ተገቢ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
Average Rating