እነ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ
የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የግዥ መመርያን በመተላለፍ ኮርፖሬሽኑ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ ሁለት መርከቦችን በመግዛት፣ ከ544 ሚሊዮን ብር በላይ በሕዝብና በመንግሥት ላይ ጉዳት አድርሰዋል በማለት ዓቃቤ ሕግ ክስ በመሠረተባቸው በእነ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው (14 ሰዎች) ላይ ብይን ተሰጠ፡፡
የሜቴክ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ ክስ የተመሠረተባቸው የኮርፖሬሽኑ የተለያዩ ክፍል ኃላፊዎች በክሱ ላይ ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ብይን ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ በሁለተኛ ክሱ ላይ ያቀረበው የክስ ሀተታ በአንደኛ ክሱ ላይ የዘረዘረውን በመነጣጠል መሆኑን ገልጿል፡፡ በአንደኛ ክስ ላይ ዋና ዳይሬክተሩ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 407 በመተላለፍ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ገልጾ ሳለ፣ በሁለተኛ ክሱ ደግሞ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 411 በመተላለፍ ‹‹የመንግሥት ሥራ በማያመች አኳኋን መምራት›› በማለት ያቀረበውን ክስ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል፡፡ በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ ሁለቱን ክሶች በማጣመር አሻሽሎ እንዲያቀርብም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ተከሳሾቹ በዋናነት የተመሠረተባቸው ክስ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ንብረት የነበሩና የአገልግሎት ጊዜያቸውን የጨረሱ ሁለት መርከቦችን ለመሸጥ ያወጣውን ጨረታ፣ ሜቴክ ለስክራፕ እንደሚፈልጋቸው በመግለጽ በ3.3 ሚሊዮን ዶላር መግዛቱን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስፍሯል፡፡ ሜቴክ መርከቦቹን ከገዛ በኋላ በ7.3 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማደስ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ በማድረጉ ከገዛበት ዋጋ በላይ ለማሳደሻ ከማውጣቱም በላይ፣ ለአስተዳደርና ለተለያዩ ወጪዎች 544,702,623 ብር ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ፍርድ ቤቱ እንዲሻሻል ትዕዛዝ የሰጠበትን ክስ ለመጠባበቅ ለመጋቢት 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
እነ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው (አራት ሰዎች) በሌላ መዝገብ ከትራክተር ግዥ ጋር በተያያዘ በተመሠረተባቸው ክስ ላይ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ ድርጊቱን አለመፈጸማቸውንና ጥፋተኛም እንዳልሆኑ በመግለጻቸው፣ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን ከግንቦት 1 እስከ 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ እንዲያሰማ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
Average Rating