የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በመንግሥትና በሕዝብ ላይ ከ768.7 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል በማለት በቀድሞ የኢትዮ ቴሌኮም የቀድሞ ኤንጂፒኦ ዳይሬክተር ላይ አቅርቦ የነበረውን ክስ አሻሽሎ አቀረበ፡፡
ዓቃቤ ሕግ ክሱን ያሻሻለው ክስ የተመሠረተባቸው አቶ ኢሳያስ ዳኘው ቀደም ብሎ በቀረበባቸው ክስ ላይ ያቀረቡትን የቅድመ ክስ መቃወሚያ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት በመቀበሉና ክሱ እንዲሻሻል ትዕዛዝ በመስጠቱ ነው፡፡
ዓቃቤ ሕግ በመጀመርያ ክሱ ላይ አቶ ኢሳያስ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 33 እና 411 በመተላለፍ፣ በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆንና የመንግሥትን ሥራ በማያመች መንገድ መርተዋል በማለት ሁለተኛ ክስ አድርጎ አቅርቦባቸው ነበር፡፡
ነገር ግን ፍርድ ቤቱ እንዲያሻሽል በሰጠው ትዕዛዝ ‹‹ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን›› የሚለውንም በመተውና አንቀጹንም ወደ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 እና 407 በመቀየር፣ ሥልጣንን ያላግባብ መገልገል ወንጀል በማለት አሻሽሎ አቅርቧል፡፡
በመሆኑም አቶ ኢሳያስ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም፣ ራሳቸውን ለመጥቀምና ዜድቲኢ የተባለውን የቻይና ቴሌኮም ኩባንያ ለመጥቀም ግዥ እንዲፈጽም ማድረጋቸውን አካቶ ቀርቧል፡፡
ለዩኒቨርሲቲዎች የኔትወርክ ግንባታ አገልግሎት ያለ ጨረታና ከተቋሙ የግዥ መመርያ ውጪ የ44,510,971 ዶላር ወይም 768,704,469 ብር ግዥ እንዲፈጸም በማድረግ፣ በተቋሙ ላይ ጉዳት አድርሰዋል በማለት ክስ ዓቃቤ ሕግ ማቅረቡን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የተሻሻለውን ክስ የተቀበለው ፍርድ ቤቱ ለተከሳሹ እንዲደርሳቸው ካደረገ በኋላ፣ በተሻሻለው ክስ ላይ አስተያየት ካላቸው ለመጠባበቅ ለሐሙስ መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
Average Rating