www.maledatimes.com ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንትና የቦርድ አባል ውስጥ ግማሾቹ ሴቶች እንዲሆኑ ታዘዘ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንትና የቦርድ አባል ውስጥ ግማሾቹ ሴቶች እንዲሆኑ ታዘዘ

By   /   March 23, 2019  /   Comments Off on ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንትና የቦርድ አባል ውስጥ ግማሾቹ ሴቶች እንዲሆኑ ታዘዘ

    Print       Email
0 0
Read Time:1 Minute, 55 Second

በዩኒቨርሲቲ የፕሬዘዳንትነትና የቦርድ አባልነት ስብጥር ውስጥ ግማሾቹ ሴቶች እንዲሆኑ ለዩኒቨርሲቲዎች መመሪያ መስጠቱን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር አስታወቀ።

ሚንስትሯ ሒሩት ወልደማሪያም (ፕሮፌሰር) ለአዲስ ማለዳ ልዩ እትም መጽሔት እንግዳ ሆነው በቀረቡበት ቃለ ምልልስ እንዳሉት ለሚንስቴሩ ተጠሪ በሆኑት 45 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚገኘው ቦርድ እንዲሻሻል ተደርጓል። በዚህም በሁሉም የዩኒቨርሲቲ ቦርዶች ውስጥ ሃምሳ በመቶዎቹ ሴቶች እንዲሆኑ መደረጉን ሚንስትሯ ገልፀዋል።

በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች፣ አካዳሚክስ ተቋማትና ሌሎች ድርጅቶች ውስጥ የሚገኙ ጠንካራና ውጤታማ ሴቶችን በማፈላለግ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ቦርድ ውስጥ እንዲካተቱ እየተደረገ መሆኑንና በዚህም ከቦርድ አባላት ሦስቱ ሴቶች እንዲሆኑ አቋም ይዘው እየሰሩ እንደሚገኙ ሚንስትሯ ሒሩት አሳውቀዋል።
ከዚህ ቀደም ከኹለት ዩኒቨርሲቲዎች ውጭ ቦርዶች የሚመሩት በወንዶች እንደነበር ያስታወሱት ሒሩት አሁን ላይ 10 ዩኒቨርስቲዎች ሴት የቦርድ ሰብሳቢ እንደተሰየመላቸውም ገልፀዋል።

በተያያዘ የዩኒቨርሲቲ አመራር መመልመያ መስፈርት መሻሻሉን ያነሱት ሚንስትሯ በፕሬዘዳንትነትና ምክትል ፕሬዘዳንትነት ቦታዎች ላይ የሴቶች ቁጥር ከፍ እንዲል እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ አንድ ፕሬዝዳንትና አራት ምክትል ፕሬዝዳንቶች አሉት። ሚንስትሯ ሦስት ምክትል ፕሬዘዳንት ያላቸው አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳሉም ጠቅሰው፤ የተሻሻለው የመመልመያ መመሪያ በእያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ ቢያንስ ኹለት ጠንካራ ሴቶች በፕሬዘዳንትና ምክትል ፕሬዘዳንት ቦታዎች ላይ እንዲሰየሙ የሚያዝ መሆኑን አስገንዝበዋል። ይህም አንድ ዩኒቨርሲቲ ቢያንስ ኹለት ሴት ምክትል ፕሬዘዳንት እንዲኖረው የሚያስገድድ ሲሆን፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ሴት ከሆነች ቢያንስ አንድ ሴት ምክትል ፕሬዝዳንት እንድትኖርም አዲሱ መመሪያ ያሳስባል።

ሚንስትሯ ለአብነት በሚል ‹‹አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንድ ብቻ ሴት በቦርዱ ውስጥ አካቶ አምጥቶ፥ ኹለት አድርጉ ተብሎ ተመልሶባቸዋል›› ሲሉም የመመሪያውን አስገዳጅነት አመልክተዋል። ‹‹ይህ አንድም የፍትሐዊነት ጉዳይ ነው። ሴት ብቁ ከሆነች መብቷ ነው። አመራር መሆን አለባት ምክንያቱም ዩኒቨርሲቲ የወንድም የሴትም ተማሪዎች ማዕከል ነው። ኹለትም የሴት ዕይታና አቅም ጥቅም ላይ መዋል አለበት። የምንፈልገው ለውጥ እንዲመጣ የወንድ አቅም ብቻ በቂ አይደለም›› ሲሉ አቋማቸውን አሳውቀዋል።

ይሁንና ይህ የተደረገው ለኮታና ፆታ ምጥጥን ብቻ ሲባል እንዳልሆነ ያስረዱት ሚንስትሯ ‹‹እኔ በኮታ አላምንም፤ ኮታ መጥፎ ነው›› ሲሉም አክለዋል። ዝም ተብሎ ለኮታ ብቻ በሚል ቢሰራና ኋላ ላይ የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ ባይቻል መልሶ ችግር እንደሚፈጥርም አንስተዋል። ‹‹ሴት ናት እንዲህ ያበላሸችው በሚል መጥፎ ምሳሌ ይሆናል›› ያሉም ሲሆን፣ ‹‹ብዙ ሴት የለም የሚባለው ነገር ውሸት ነው ሞልቷል፤ በየምርቃቱ የምናየው የወርቅ ተሸላሚ ሴት ናት›› ሲሉም ተደምጠዋል።

ሒሩት አያይዘውም የሳይንስና ከፍትኛ ትምህርት ሚንስቴርን እንዲመሩ ጥቅምት 2011 ከተሾሙ ወዲህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሴት መምህራን ኅብረትን እንዳቋቋሙ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። ሴቶች ወደኋላ የቀሩት ትስስር (‹‹ኔትዎርክ››) ስለሌላቸው ነው ብለው የሚያምኑት ሒሩት ዓላማው በማኅበሩ ምክንያት እርስ በእርስ እንዲረዳዱ መሆኑንም አሳውቀዋል። ለሚንስቴሩም የሴቶችን አቅም ለማጎልበት አንድ አደረጃጀት ሆኖ እንደሚያገለግል አንስተዋል። በምርምርና በፕሬዝዳንትነት ደረጃ ብዙ ሴቶች እንደሌሉ በመጥቀስም ማኅበሩ የሴቶችን አቅም እያጎለበተ ወደ አመራርነት ቦታ እንዲመጡ እንደሚያግዝም ተስፋ ጥለውበታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 18 የመጋቢት 7 ቀን 2011

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 6 years ago on March 23, 2019
  • By:
  • Last Modified: March 23, 2019 @ 9:39 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar