www.maledatimes.com ተጨማሪው በጀት ከብድር ፖሊሲው ጋር ይጋጫል ተባለ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ተጨማሪው በጀት ከብድር ፖሊሲው ጋር ይጋጫል ተባለ

By   /   March 23, 2019  /   Comments Off on ተጨማሪው በጀት ከብድር ፖሊሲው ጋር ይጋጫል ተባለ

    Print       Email
0 0
Read Time:1 Minute, 51 Second

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተወስኖ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላከው የፌደራል መንግስት የ2011 ተጨማሪ በጀት ከኢትዮጵያ የብድር ፖሊሲ ጋር ይጋጫል ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተቃውሞ አነሱ።

የሚንስትሮች ምክር ቤት የካቲት 23/2011 በነበረው 64 መደበኛ ስብሰባ ለተያዘው በጀት ዓመት የ34 ቢለዮን ብር የሚጠጋ ተጨማሪ በጀት ላይ የይሁንታ ውሳኔ ባማሳለፍ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቤት ያፀድቅለት ዘንድ ለምክር ቤቱ እዲቀርብለት መወሰኑ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ ባሳለፍነው ማክሰኞ የተጨማሪ በጀቱን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ለመምራት ምክር ቤቱ ስብሰባ ተቀምጧል። በወቅቱም ከምክር ቤት አባላት የተቃውሞ አስተያየቶች ተነስተዋል። የበጀቱ ምንጭ ከውጭ ዕርዳታ እና ከዓለም ዐቀፍ አበዳሪ ተቋማት የተገኘ ብድር መሆኑን ያስታወሱት የምክር ቤቱ አባላት፣ በጀቱ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ለመደበኛ ወጪ መዋሉን መነሻ አድርገው የቅሬታ ድምፆችን አሰምተዋል።

የኢትዮጵያ የብድር ፖሊሲ እንደሚደነግገው ከብድር የሚገኘው ገቢ ለካፒታል ወጪ እንጂ ለመደበኛ ወጪ መዋል አይችልም።

የኢትዮጵያ የብድር ፖሊሲ ይህን ይበል እንጂ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው የ2011 ተጨማሪ በጀት ከታቀደው 33 ቢሊዮን 986 ሚሊዮን በላይ ብር ውስጥ 33 ነጥብ 7 ቢሊዮን የሚሆነውን ለመደበኛ ወጪ እንዲውል መመደቡ የታወቀ ሲሆን፤ ቀሪ 240 ሚሊዮን ብር የሚሆነውን ብቻ ለፌደራል የካፒታል ወጪ እንዲውል የበጀት ድልድል መደረጉ ታውቋል። ይህም ለአባላቱ የተቃውሞ ሀሳብ አንድ መነሻ ሆኖ ተወስዷል።

የተጨማሪ በጀቱ አሁን ላይ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የዋጋ ግሽበት ከማባባስ የበለጠ ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሚታ የለውም የሚልም ሀሳብ ከምክር ቤት አባሉ አበበ ሙላት ተሰምቷል።

ተጨማሪው በጀት እንዲፀድቅ ያስፈለገበት ምክንያት በካፒታል በጀት ሥራዎች ተሰርተው ክፍያቸው ላልተከፈሉ ፕሮጀክቶች ክፍያ ለመክፈል፣ በተያዘው ወር መጨረሻ ለሚካሔደው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ወጪን ለመሸፈንና የኢትዮጵያ መንግሥት በሽርክና ላቋቋመው የቱሉ ካፒ የወርቅ ልማት የመንግሥት ድርሻ የሆነውን የመንገድና የኤሌክትሪክ ዝርጋታ ለመሸፈን እንደሆነ ታውቋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ሻምበል ግርማ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ከአሁን በፊት በሕዝብና ቤት ቆጠራ ጋር በተያያዘ ችግሮች እንደነበሩ አስታውሰው አሁንም ምንም አይነት ሪፎርም እንዳልተደረገበት ተናግረዋል። ሻምበል ባልተረጋጋ አገርና ባልተለወጠ አሰራር ይህን ያህል ገንዘብ መበጀት ትክክል ነው ብለው እንደማያምኑም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል መንግሥት የተጀመሩት የግንባታ ሥራዎች ሳይጠናቀቁ አዲስ ፕሮጀክቶችን በመንግሥት በኩል እንደማይጀመር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) የተናገሩ ቢሆንም ለቱሉ ካፒ የመንገድ ግንባታ በጀት ድልድል መደረጉ ተገቢ አይደለም የሚል ተቃውሞም ከምክር ቤቱ አባላት ተነስቷል። ተያይዞም ለወርቅ ልማቱ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ የተበጀተው ገንዘብ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛ የገንዘብ ዕዳ እያለበት አዲስ በጀት መመደብ ሌላ ክፍተት ይፈጥራል ሲሉ ወይንሸት ታደሰ የተባሉ የምክር ቤት አባል ተናግረዋል።

ይሁንና የበረከቱ የተቃውሞ አስተያየቶች የተስተናገዱበት የ2011 የፌደራል መንግሥት ተጨማሪ በጀት በሙሉ ድምፅ ለሚመለከተው የቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 6 years ago on March 23, 2019
  • By:
  • Last Modified: March 23, 2019 @ 10:15 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar