በከተማዋ ኹለት መቶ የሚሆኑ ወላጅ አልባ ህፃነት በጉዲፈቻ የሚያሳድጋቸውን ቤተሰብ እየተጠባበቁ መሆኑን የከተማዋ ሴቶች እና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።
የህፃናት ድጋፍ ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር ገነት ጴጥሮስ እንደተናገሩት ቢሮው በዚህ ዓመት ብቻ በጉዲ ፈቻ እንዲያድጉ 94 ወላጅ አልባ ህፃናትን ለተለያዩ ቤተሰቦች ሰትቷል።
96 ህፃናትን ደግሞ በአደራ መልክ ለአደራ ቤተሰብ እንዳስረከቡ ያሳወቁት ዳይሬክተሯ በቅርቡ ወደ አሳዳጊ ወላጆቻቸው የሚሔዱ 50 ህፃናት እንዳደሉም አክለዋል። ይህም ሆኖ አሁንም በቢሮው የሚገኙና አሳዳጊ ወላጅ ያልተገኘላቸው 200 ህፃናት እንዳሉም አብራርተዋል።
ገነት ለአዲስ ማለዳ እንዳሉት በቢሮው በኩል በየቀኑ በአማካኝ ከሦስት እስከ አምስት ህፃናት በጉዲፈቻ ሲወሰዱ በተመሳሳይ ከሦስት እስከ አምስት ህፃናት ደግሞ ወላጅ አልባ ሆነው በየመንገዱ ይገኛሉ። በዚህም በጉዲፈቻ የሚወስዳቸው ቤተሰብ ለመፈለግ ወደ ቢሮው እንዲመጡ ይደረጋል። ይህ በመሆኑም አሳዳጊ የሌላቸው ህፃናት ቁጥር ሊቀንስ አለመቻሉን አስረድተዋል።
ቢሮው ወላጅ አልባ የሆኑትን ህፃናት ደኅንነትና መብት ለማስጠበቅ በሚል የማኅበረሰብ አቀፍ ድጋፍና እንክብካቤ፣ ህፃናትን ከማኅበረሰቡ ጋር መልሶ የመቀላቀል፣ የአደራ ቤተሰብ እና ጉዲፈቻ እንዲሁም ለህፃናት በማሳደጊያ ማዕከላት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን አሟልቶ እንዲያድጉ እና ኋላም ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የማድረግ አማራጮችን ይዞ እየሰራበት ስለመሆኑም ዳይሬክተሯ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተለያየ ስያሜዎች እየተጠራ ሲፈጸም የኖረ ልማድ ስለመሆኑ የተለያዩ አብነቶች አሉ። ይህ የዳበረ ልምድ በዋናነት ዓላማ የሚያደርገው የጉዲፈቻ አድራጊውን ጥቅም እንጂ የልጁን ጥቅም ባለመሆኑ በዘመናዊ ሁኔታና የህፃናትን መሰረታዊ ጥቅም ማዕከል ባደረገ መልኩ አንዲሆን መንግስት እየሰራበት ነውም ተብሏል። በሕገ መንግሥቱም ሆነ በቤተሰብ ሕጉ ህፃናትን የሚመለከቱ ጉዳዮች የህፃናቱን ደኅንነትን የሚያስቀድሙ እንዲሆኑ ስለመደረጉም ገነት ያስረዳሉ።
ህፃናትን ለውጪ አገራት ዜጎች በማደጎ ወይም ጉዲፈቻ በመስጠት ከሚታወቁት አገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ የነበረች ብትሆንም ህፃናቱ የሚያድጉት በማያውቁት ማኅበረሰብ ባሕልና ወግ ስለሆነና፣ በኢትዮጵያ ህፃናት ላይ የሚሰሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ኅብረተሰቡ ህፃናቱን በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ተቀብሎ የማሳደጉ ልምድ ዳብሯል በሚል እምነት ኢትዮጵያ የውጭ አገር ጉዲፈቻን ማገዷ ይታወሳል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው 2010 በውጪ አገር ጉዲፈቻ ምክንያት ኢትጵያዊያን ህፃናት የማንነትና የስነ ልቦና ቀውስ ውስጥ እየወደቁ ነው በሚል መነሻም ጭምር በመስማማት የውጭ አገር ጉዲፈቻን በአዋጅ መከልከሉ ይታወሳል።
ጉዲፈቻ የሚለው ፅንሰ ሀሳብ ከሌላ ሰው አብራክ የተገኘን ልጅ ከሌላ ሰው የተወለደ ልጅ መሆኑን አምኖና ተቀብሎ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ መብቱን ጠብቆ እንደ ራስ ልጅ ማሳደግን ይመለከታል።
Average Rating