ʻባቢሎን በሳሎንʼ በኢትዮጵያ የቴአትር ኢንዱስትሪ ታሪክ ውጤታማና መድረክ ላይ ብዙ ከቆዩት መካከል ይመደባል። በርግጥ ቴአትር ተመልካች ሆኖ ባቢሎን በሳሎንን ያልተመለከተ ማግኘት ከባድ ነው።
የቴአትሩ ሥም በተነሳ ቁጥር አንድ የማይረሳ ተዋናይ ቢኖር ዓለማየሁ ታደሰ ነው። ሐረር ተወልዶ ያደገው ዓለማየሁ ታደሰ ወደ ፊልም ኢንዱስትሪ በጥልቀት ከመግባቱ በፊት ሰዎች የበለጠ የሚያውቁት በቴአትሮች ላይ በሚጫወታቸው ገፀ ባሕሪያት ነበር።
ከሌሎች የጥበብ ባለሙያዎች በተቃራኒ ዓለማየሁ የኪነ ጥበብ ባለሙያ እሆናለው ብሎ በልጅነቱ አያስብም ነበር፡፡ ˝ተማሪ እያለሁ አንድም ቀን ተዋናይ እሆናለው ብዬ አላስብም ነበር˝ ይላል ዓለማየሁ ልጅነቱን ሲያስታውስ። ነገር ግን ዕድሜው እያደገ ሲመጣ ይህንን ሐሳቡን ቀይሯል።
የ˝11ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ አስተማሪዎች ስለተባበሩት መንግሥታት ድራማ እንድንሠራ አዘዙን። እኔም የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሆኜ እንድተውን ነበር የተመረጥኩት፤ ከዚያም ይህንን ያዩ ሰዎች በትወናው እንድቀጥልበት መከሩኝ።˝
ዓለማየሁ የተሰጠውን ጥሩ አስተያየት በመቀበል መተወኑን ቀጠለበት።አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በሐረር ቀላዳንባ አርበኞች ትምህርት ቤት የተማረ ሲሆን ኹለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሐረር በመድኀኒዓለም ትምህርት ቤት በሚማርበት ወቅት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስን በመሆን ተውኗል።
ከዚያም በ1980ዎቹ መጀመሪያ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀለ። በወቅቱ ተማሪ በነበረበት ወቅት የቴአትር ተማሪዎች ሲተውኑ መመልከቱ የበለጠ ሙያው ላይ እንዲገፋበት አበረታታው። አሁን ይህ አጋጣሚ ካለፈ 20 ዓመታት ሆኖታል።
ዓለማየሁ በኢትዮጵያ ውጤታማና ታዋቂ ከሚባሉት ተዋናዮች ተርታ ተሰልፏል። እስከ አሁንም በርካታ የሚቆጠሩ ፊልሞችና ቴአትሮች ላይ ዓለማየሁ መሪ ተዋናይ ሆኖ ሰርቷል እየሠራም ይገኛል።
ለብዙ ሰዎች ምሳሌ መሆን ችሏል። ብርቱካን በፍቃዱ፣ ግሩም ኤርምያስ፣ መስፍን ኃይለ እየሱስ፣ ሄርሞን ኃይላይ፣ ቴዎድሮስ ስዩም፣ አብዱልከሪም ጀማል ካስተማራቸው ውጤታማ ተዋናያን መካከል ይጠቀሳሉ። ʻየማለዳ ኮኮቦችʼ በሚባለው የቴሌቪዥን ዝግጅት ላይ ዳኛ ሆኖ በማገልገል ተተኪዎችን ለማፍራትና ልምዱን ለማጋራት አበርክቶ አድርጓል፤ በማድረግም ላይ ይገኛል። በመድረክ ሥራ ያልረገጠው ቴአትር ቤቶች የለም፤ በድርሰት፣ በዝግጅትም በዋነኝነት ደግሞ በትወና ያገለግላል አሁንም ብሔራዊ ቴአትር ውስጥ በማገልገል ላይ ይገኛል።
ይሁን አንጂ ዓለማየሁ አሁንም በሥራው የረካ አይመስልም። አሁንም ብቃቱን የበለጠ ሊያሳይ የሚችበት ፊልሞች እየሠራ መሆኑን ይገልፃል።
ለዓለማየሁ እስካሁን ከተወነባቸው ሥራዎቹ ውስጥ የበለጠ የሚወደው ለመምረጥ ቢቸገርም ከቴአትሮች አንቲገንን፣ ከፊልም ደግሞ በቅርቡ ይወጣል ተብሎ የሚጠብቀውን አትፍረድን መርጧል። ኤርታአሌን ደግሞ ከሠራቸው ዶክመንተሪ ፊልሞች ምርጡ ነው ብሏል።
የሦስት ልጅ አባት የሆነው ዓለማየሁ ከቴአትር ትወና ባሻገር ፊልሞችን ከመፃፍ አንስቶ ፕሮዲዩሰር ሆነ ለኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ዕድገት የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል። ይሁን አንጂ ለዘርፉ የተሰጠው ዕድገት እምብዛም መሆኑን ዓለማየሁ ያነሳል።
˝በተለያየ ወቅት ቢቀያየርም ከመንግሥት የቴአትር ኢንዱስትሪ ትኩረትም ሆነ የፈለገውን ነፃነት አላገኘም። መንግሥት የኪነ ጥበብ ኢንዱስትሪ በማሳደግ ፈንታ የራሳቸውን መልዕክት ማስተላለፊያ መንገድ እያደረጉት ፊልምና ቴአትር ማየት እንደ ቅብጠት ተቆጥሮ የኢትዮጵያ ባሕል እንዳያበላሽ በሚል ታክስ ይጣልበታል˝ ሲል ዓለማየሁ ስለ ኪነ ጥበብ ዘርፉ ዕድገት ያወሳል።
ይህ ዓይነቱ ድርጊት የቴአትርና ፊልም ኢንዱስትሪ ሆነ የኪነ ጥበብ አሉታዊ ተፅዕኖ እያዳሳደረ ዓለማየሁ ይገልፃል። የኢትዮጵያ ፊልሞች በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነታቸው አናሳ ነው የሚለው ዓለማየሁ ለዚህ ፊልም ሰሪዎች የሚያስተምርና የሚቆጣጠር አካል አለመሆኑ ምክንያት ነው ይላል፡፡ ለአብነት በብዙ ሒደቶች የሚያልፈው የቴአትር አሰራርን ዓለማየሁ ያነሣል፡፡
˝አንድ ቴአትር ሲሰራ መጀመሪያ በባለሙያዎች ይታያል ከዚያም ሊጣል ይችላል ካለፈ ደግሞ፤ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች ለደራሲው ይነገረዋል፡፡ ከዚህም በትንሹ ይሞከርና ከዚያም ድጋሚ በባለሙያዎች ታይቶ ካለፈ ለሕዝቡ እንዲቀርብ ይደረጋል˝ ሲል ዓለማየሁ ይገልፃል፡፡
ይህ ዓይነቱ ሒደት በፊልም ኢንዱስትሪ መኖር ቢኖርበትም፤ አሁን ላይ የሚታየው በጓደኝነትና በመተዋወቅ ላይ መሰረት ያደረገ ሥራ ነው ይህ ደግሞ ያልተተቸና ከደረጃ በታች የሆኑ ፊልሞች እንዲሰራፋ ምክንያት ነው ሲል ዓለማየሁ ያነሳል፡፡
˝መንግሥት ለዘርፉ የበለጠ ትኩረት በመስጠት የግሉን ዘርፍ መንግሥት በቦርድና በኮሚቴ በማዋቀር ቴአትሮችን እንዲያስተዳድሩ ዕድል ሊሰጥ ይገባል˝ የሚለው ዓለማየሁ ከመንግሥት ባሻገር ዘርፉን ለማሳደግ ከኅብረተሰቡ በኩል የተሰጠው ትኩረትም አናሣ መሆኑ ያወጋል።
ለአብነትም በቴአትር ዘርፍ ተመረቀው በሙያው መሥራት ያልቻሉ ባለሙያዎችን ያነሳል። ˝የፊልም ኢንዱስትሪ ሌላው ትኩረት የሚሻ የኪነጥበብ ዘርፍ ነው˝ ይላል በፋና ቴሌቪዥን እየተላለፈ ባለው ʻደርሶ መልስʼ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ የሚተውነው ዓለማየሁ፡፡
ይህ ጽሑፍ ከአዲስ ማለዳ እህት መጽሔት ከሆነችው ʻኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪውʼ ተቀንጭቦ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ተመለሶ የቀረበ ነው።
Average Rating