www.maledatimes.com የአውሮፕላን አደጋው ምርመራ ውጤት በዚህ ሳምንት ይፋ ይደረጋል - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የአውሮፕላን አደጋው ምርመራ ውጤት በዚህ ሳምንት ይፋ ይደረጋል

By   /   March 26, 2019  /   Comments Off on የአውሮፕላን አደጋው ምርመራ ውጤት በዚህ ሳምንት ይፋ ይደረጋል

    Print       Email
0 0
Read Time:3 Minute, 27 Second

  1. የአውሮፕላን አደጋው ምርመራ ውጤት በዚህ ሳምንት ይፋ ይደረጋል

የአውሮፕላን አደጋው ምርመራ ውጤት በዚህ ሳምንት ይፋ ይደረጋል
መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን የወደቀበት ሥፍራ

የአሜሪካ መንግሥት ዲፕሎማሲያዊ ጫና እያደረገ ነው

መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ማለዳ አደጋ የደረሰበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ   737-8 ማክስ አውሮፕላን ላይ በመካሄድ ላይ ያለው የአደጋ ምርመራ የመጀመርያ ደረጃ ሪፖርት በተያዘው ሳምንት ይፋ ይደረጋል፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሐሙስ መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ የአደጋ ምርመራ ቢሮ ከኢቲ 302 የመረጃ ሳጥን በተገኘው መረጃ ላይ ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት መሥፈርት መሠረት የትንተና ሥራ በመከናወን ላይ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ የአደጋ ምርመራ ቢሮ፣ የአሜሪካ ትራንስፖርት ሴፍቲ ቦርድ፣ የፈረንሣይ ቢኢኤና የአውሮፓ አቪዬሽን ሴፍቲ ኤጀንሲ ባለሙያዎች፣ ከመቅረፀ ድምፁና የበረራ መረጃ መቅጃ የተገለበጠውን መረጃ በመተንተን ላይ እንደሆኑ ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡ ‹‹የትንታኔው የመጀመርያ ደረጃ ሪፖርት በዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት መሥፈርት መሠረት ይፋ ይደረጋል፤›› ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡

 የመጀመርያ ደረጃ ሪፖርቱ በዚህ ሳምንት ይፋ እንደሚደረግ ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ለአደጋ ምርመራው ሒደት ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የናሽናል ትራንስፖርት ሴፍቲ ቦርድና የቦይንግ ኩባንያ ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ አደጋ ምርመራ ቢሮ ከመቅረፀ ድምፅና ከበረራ መረጃ መቅጃ የተገለበጡ መረጃዎች እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የመረጃ ሳጥኑ መረጃ ቅጂ እንዲሰጥ እስካሁን ፈቃደኝነት እንዳላሳዩ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ‹‹መረጃው ከእጃችን ከወጣ ሌላው ወገን በሚፈልገው መንገድ አቀነባብሮ ሊያወጣው ይችላል፤›› የሚል ሥጋት እንዳለ ተገልጿል፡፡

በሁኔታው የተበሳጩ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እያሳደሩ እንደሆነ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ራይነር የትራንስፖርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት በመሄድ፣ መረጃው ለናሽናል ትራንስፖርት ሴፍቲ ቦርድና ለቦይንግ ኩባንያ እንዲሰጥ በኃላፊዎቹ ላይ ግፊት እያሳደሩ እንደሆነ ታውቋል፡፡ አምባሳደር ራይነር በሁኔታው የተሰማቸውን ቅሬታ ለትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ መግለጻቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ከመረጃ ሳጥኑ የተገኘው መረጃ ቅጂ እንዲሰጣው ከመጠየቅ አልፈው በምርመራ ሒደቱ ላይ ጫና በመፍጠር ላይ ናቸው ያሉት ምንጮች፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ስልክ በመደወል በአደጋ ምርመራ ሒደት ላይ መወያየታቸውን ተናግረዋል፡፡

የመቅረፀ ድምፁና የበረራ መረጃ መቅጃ መረጃ በቢኢኤ ባለሙያዎች ሲገለበጥ የናሽናል ትራንስፖርት ሴፍቲ ቦርድና የቦይንግ ኩባንያ ባለሙያዎች ሒደቱን መታዘባቸውን የገለጹት ምንጮች፣ የኢትዮጵያ አደጋ ምርመራ ቢሮ ሥራውን በአግባቡ በማከናወን ላይ እንደሆነ ገልጸው የመጀመርያ ደረጃ ሪፖርቱ በዚህ ሳምንት ይፋ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የተጠየቀው አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በጽሑፍ በሰጠው ምላሽ፣ የአውሮፕላን አደጋው ከደረሰበት ቀን አንስቶ የአሜሪካ መንግሥት የአደጋ ምርመራ ሥራውን ሌት ተቀን በመደገፍ ላይ እንደሆነ ገልጿል፡፡ የኤምባሲው ፐብሊክ አፌርስ ኦፊሰር አማንዳ ጃኮብሰን አሜሪካን ጨምሮ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ፍላጎት የተፈጠረውን ነገር በመረዳት አስፈላጊውን የማስተካከያ ዕርምጃ መውሰድ እንደሆነ ገልጸው፣ ከዚህ የተለየ አካሄድ ለማንም እንደማይጠቅም ተናግረዋል፡፡ ዓለም አቀፍ መርሆችንና አሠራሮችን በመመከተል የአደጋ ምርመራ ሥራውን የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሆነ ጠቁመው፣ የአሜሪካ መንግሥት አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ ላይ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት አሠራር መሠረት የአሜሪካ መንግሥት በናሽናል ትራንስፖርት ሴፍቲ ቦርድ አማካይነት ተወክሎ፣ እንደ አውሮፕላን አምራች አገር በአደጋ ምርመራ ሒደት ላይ እየተሳተፈ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስትሯን አስተያየት ለማካተት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

የኢንዶኔዥያ ላየን ኤርና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋዎች ተከትሎ በማክስ አውሮፕላን የበረራ ደኅንነት ሥጋት የገባው የዓለም የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ፣ አምራች አገሯን አሜሪካ ጨምሮ አውሮፕላኑ ላልተወሰነ ጊዜ ከሥራ ውጪ እንዲሆን ማድረጉ ይታወሳል፡፡

የቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን መሠረታዊ የንድፍ ችግር እንዳለበት የሚገልጹት የአቪዬሽን ባለሙያዎች፣ ቦይንግ የዲዛይን ችግሩን ለማስተካከል ብሎ በሚስጥር ያስጫነው ኤምካስ የተሰኘው የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር አውሮፕላኑን ለአደጋ እንዳጋለጠው ያስረዳሉ፡፡ የቦይንግ ኩባንያ የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌሩን አስመልክቶ ለደንበኞቹ በቂ መረጃ አለመስጠቱ፣ የላየን ኤር አደጋ ባለፈው ጥቅምት ወር ከተከሰተ በኋላ እንኳ አስፈላጊውን የማስተካከያ ዕርምጃ ባለመውሰዱ ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ሊደገም እንደቻለ ገልጸዋል፡፡

የአሜሪካ የአቪዬሽን ዘርፍ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን የፌዴራል አቪዬሽን አድሚኒስትሬሽን እንዴት ችግር ያለበት የበረራ መቆጣጠሪያ መሣሪያ የብቃት ማረጋገጫ ሊሰጥ ቻለ? የሚል ጥያቄ የሚያነሱት የአቪዬሽን ባለሙያዎች፣ ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን የብቃት ማረጋገጥ ሥራውን ራሱ ቦይንግ እንዲያከናውን ፈቅዷል በማለት እየወነጀሉት ነው፡፡ በኤፍኤኤና በቦይንግ ኩባንያ መካከል ተገቢ ያልሆነ ግንኙነት እንደተፈጠረ በመግለጽ፣ የሥራ ግንኙነታቸው በአግባቡ እንዲጠና ጠይቀዋል፡፡

የአሜሪካ ፍትሕ ዲፓርትመንት የማክስ አውሮፕላን ንድፍ፣ ምርትና የብቃት ማረጋገጫ ሒደት ላይ የወንጀል ምርመራ ሥራ እንደጀመረ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ የትራንስፖርት ዲፓርትመንት በማክስ አውሮፕላን የበረራ ደኅንነት ላይ ገለልተኛ ምርመራ በማካሄድ ላይ ነው፡፡ የአሜሪካ ኮንግረስም በኤፍኤኤና በቦይንግ ኩባንያ ላይ ጥልቅ ምርመራ እንዲካሄድ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

እውነታው ይህ በሆነበት በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ተጠያቂነት ያስፈራቸው አካላት የትኩረት አቅጣጫቸውን ወደ ሌላ ለማዞር የተለያዩ ሥልቶችን እየተጠቀሙ ነው ያሉት ምንጮች፣ በሕይወት የሌሉና ራሳቸውን መከላከል የማይችሉትን አብራሪዎች የአደጋ ምርመራ ሪፖርቱ ከመውጣቱ በፊት ተጠያቂ ለማድረግ መሞከር ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም እንደ ማስረጃ የሚጠቀሱት ሰሞኑን በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የአደጋው ምርመራ ይፋ ከመደረጉ በፊት አብራሪው ላይ የተነሳው ትችት፣ በተለይ የአውሮፕላን አምራቹ ራሱን ከተጠያቂነት ለማሸሽ የሚያደርገው ጥረት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 6 years ago on March 26, 2019
  • By:
  • Last Modified: March 26, 2019 @ 10:30 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar