ከስድስት ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ነባር የቢራ ፋብሪካዎችን በመግዛትና አዳዲስ ፋብሪካዎችን በመገንባት፣ የተለያዩ የቢራ ዓይነቶችን በማምረት ላይ የሚገኘው ሃኒከን ብሪወሪስ አክሲዮን ማኅበር የፍትሐ ብሔር ክስ ተመሠረተበት፡፡
አክሲዮን ማኅበሩ የተከሰሰው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 22ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ሲሆን፣ ክሱ የተመሠረተበት በኤጀንትነትና ምርቶቹን በማከፋፈል አብረውት ይሠሩ በነበሩት አቶ ሰለሞን ግዛው በሚባሉ ግለሰብ መሆኑን የክስ ሰነዱ ያስረዳል፡፡
ማኅበሩ የቀረበበት ክስ 2,747,300 ብር ክፍያ ለመፈጸም ፈቃደኛ ባለመሆኑ እንደሆነም ክሱ ይጠቁማል፡፡
ከሳሽ ከማኅበሩ ጋር በገቡት ውል መሠረት ከሁለት ዓመት በላይ የማኅበሩን ምርቶች በማከፋፈል እንደ ውሉ ሲፈጽሙ የቆዩ ቢሆንም፣ ማኅበሩ ያለ በቂ ምክንያትና ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ውሉን እንዳቋረጠ ክሱ ይገልጻል፡፡
በማኅበሩና በከሳሽ መካከል የነበረው ሕጋዊ ውል መቋረጥ ከነበረበትም፣ መቋረጥ ያለበት የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1820 ድንጋጌ መሠረት መስጠት ተገቢ እንደነበር በክሱ ተመልክቷል፡፡
ነገር ግን ሃኒከን ብሪወሪስ አክሲዮን ማኅበርምንም ዓይነት የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥና ውል ሳይቋረጥ፣ ለከሳሽ በተወሰነ የሽያጭ ቦታ ላይ ተደራቢ በመሆን ሽያጭ ሲያካሂድ መቆየቱንም ክሱ ያሳያል፡፡ ከሳሽ በሚሠሩበት የሽያጭ አካባቢ ተደርቦ በመሥራቱ፣ በቀን ሊያገኙ የሚችሉትን 10,500 ብር ማሳጣቱን፣ ወይም በወር 315,000 ብር ማሳጣቱን ክሱ ያስረዳል፡፡
በተጨማሪም ከሳሽ ከማኅበሩ ለሚወስዳቸው ዕቃዎች ማስያዣ የሚሆንና በየስድስት ወራት የሚቀየር ቼክ ሲሰጡ የቆዩ ቢሆንም፣ ሃኒከን ብሪወሪስ አክሲዮን ማኅበርግን ቼኩን ለባንክ በማቅረብ 372,500 ብር ከመውሰዱም በተጨማሪ፣ በቼኩ ላይ በማስመታቱ ጉዳት እንዳደረሰባቸው ክሱ ያስረዳል፡፡
በአጠቃላይ ከሳሽ ከራሳቸው የከፈሏቸውንና ሊከፈላቸው ይገቡ የነበሩ ክፍያዎችን ጨምሮ፣ በአጠቃላይ ከ2,747,300 ብር ክፍያ እንዲፈጸምላቸው ክስ መመሥረታቸውን የክሱ ሰነድ ያሳያል፡፡
በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 92 መሠረት በመሀላ ተደግፎ የቀረበለትን ክስ የተቀበለው፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 22ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት፣ ሃኒከን ብሪወሪስ አክሲዮን ማኅበርሚያዝያ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
Average Rating