የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በየበጀት ርዕሱ በመደበኛ በጀት 10 በመቶ ብቻ በመውሰድ 444 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በሥራ ላይ እንዳላዋለ ታወቀ።
የሚንስቴሩ የ2009 የሒሳብ ኦዲት ግኝት በመንግሥት ወጪ ቁጥጥር ጉዳዮች አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ በተገመገመበት ወቅት እንደተገለፀው፣ በሥራ ላይ ያልዋለው በጀት ከአጠቃላይ በጀቱ ጋር ሲነፃፀር 20 በመቶ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በ2009 በሌላ የበጀት ርዕስ ላይ ከተቀመጠው በጀት 330 ሚሊዮን ብር እላፊ መጠቀሙንም የሚያሳይ ኦዲት ግኝት እንደታየበት ተገልጿል።
ከዚህም በመነሳት በኢትዮጵያ ውስጥ ለቁጥር የሚያዳግቱ የመንግሥት ፕሮጀክቶች በበጀት እጥረት ምክንያት እየተዘጉ ባለበት ሁኔታ ከመደበው በጀት ጥቂት ሊባል የሚችል የበጀት አጠቃቀም እንዴት በሚንስቴሩ ላይ ሊታይ እንደቻለ በቋሚ ኮሚቴው ተጠይቆ፤ ሚንስቴሩ በጀትን በዕቅድ ከመምራት አንፃር ያለበትን ሁኔታ ማብራሪያ እንዲሰጥ ታዟል።
ለቀረበው ጥያቄ ምለሽ ለመስጠት ውጭ ጉዳይ ሚንስቴርን ወክለው የተገኙት በሚንስትር ዲኤታ ማዕረግ የሰው ኃብትና ፋይናንስ ዳይሬክተር አምባሳደር ብርቱካን አያሌው በሚንስቴሩ መረጃ መሰረት የበጀት አጠቃቀሙ 92 በመቶ እንደሆነና ተራፊ በጀት ከመጠን በላይ እንዳይሆንም ከፍተኛ ቁጥጥር መሥሪያ ቤቱ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
በዚህም ምክንያት ዋና መሥሪያ ቤቱ ሥር ባሉ በመላው ዓለም የተሰራጩ 46 ሚሲዮኖችና 14 ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች ወጯቸው የበጀት ዓመቱ ሳያልቅ በየመሐሉ ቁጥጥር እንደሚደረግም ነው ያስረዱት። አያይዘውም ሚንስቴሩ የሚያሳየው ቁጥጥር በፌደራል ዋና ኦዲተርም ምስጋና እንደተቸረው ተናግረዋል።
ከሚንስቴሩ የተሰጠውን ምላሽ ተከትሎ የፌደራል ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ ˝መሥሪያ ቤቱ ራሱን እንዳያታልል˝ ሲሉ መክረዋል። ˝ይህን ያህል የበጀት አጠቃቀም ጉድለት እያለባችሁ በፌደራል ኦዲተር ምስጋና ተችሮናል ማለት የማይመስል ነገር ነው˝ ብለዋል። አሁንም ቢሆን ሚንስቴሩ ከፍተኛ የበጀት አጠቃቀም ጉድለትና የኦዲት ግኝት ያለበት በመሆኑ ትልቅ ሥራ እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል። እየታየ ያለው የበጀት አጠቃቀም ጉድለት በወንጀል የሚያስከስስ ነው ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ሚንስቴሩ ከተሰብሳቢ ሒሳብ ጋር በተገናኘ የኦዲት ክፍተቶች እንዳሉበት ከቋሚ ኮሚቴው የተነሳ ሲሆን፤ ተወራርዷል ከተባለው 43 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ውስጥ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብሩ ማስረጃ እንደሌለው ተገልጿል። በመጨረሻም ዋና ኦዲተሩ መረጃ ሳይኖራቸው እንደተወራረዱ የሚቆጠሩት ሒሳቦች መረጃ እስካልቀረበባቸው ድረስ ተመልሰው እንዲተከሉ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
Average Rating