የፌዴራል ዋና ኦዲተር የክልል መንግሥታት ከሚያገኙት ድጎማ በተጨማሪ በጀትና ገቢያቸው ኦዲት የማድረግ ሥልጣን የሚሰጠው ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለውይይት ሊቀርብ ነው።
አሁን እየተሰራበት ያለው የፌደራል ዋና ኦዲተር ማቋቋሚያ አዋጅ 982/2008 ሕገ መንግሥቱን መሰረት ባደረገ መንገድ ማሻሻያ መደረጉን ተከትሎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ እየመከረበት ሲሆን ወይይቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሚቀርብ ታውቋል።
በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 94 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት የፌደራሉ መንግሥት ለክልሎች የሚመድበውን በጀትና ድጎማ ኦዲት የማድረግ ሥልጣን እንዳለው የሚደነግግ ሲሆን፤ በዚህም ረገድ የፌደራሉን መንግሥት ወክሎ ኦዲት የሚያደርገው የፌደራል ኦዲተር መሥሪያ ቤት መሆኑ ተመላክቷል። በዚህም መሰረት በመሥሪያ ቤቱ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 669/2002 ላይ ተካቶ በሥራ ላይ ውሎ ነበር።
ሕገ መንግሥቱ ይህን ይበል እንጂ በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 982/2008 ውስጥ ባለመካተቱ በአሁኑ ሰዓት ክልሎች ከራሳቸው የሚገኘውን ገቢም ሆነ ከፌደራል መንግሥት የሚደረግላቸውን ድጎማዎች በራሳቸው በክልሎች ኦዲተር ኦዲት እንደሚደርጉ ታውቋል። ይህንም ምክንያት በማድረግ የማቋቋሚያ አዋጁ ማሻሻያ አስፈልጎታል ሲል የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የዋና መሥሪያ ቤቱ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አወቀ ጤናው ጨምረው እንደለገፁት፤ ክልሎችን ኦዲት የማድረግ ሥልጣን ለፌደራል ዋና ኦዲተር የተሰጠ ሥልጣን እንደሆነ ከዚህ ቀደም በነበሩት አዋጆች መካተቱን የጠቆሙ ሲሆን፤ በአዋጅ ቁጥር 982/2008 ላይ ግን ባልታወቀ ምክንያት እንዲወጣ እንደተደረገ አክለዋል። ይህንንም ጉዳይ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 94 ንዑስ አንቀጽ 2 ጋር እንዲጣጣም ለማድረግ ማሻሻያው አስፈልጓል እንደ ዋና ኦዲተር ገለፃ።
አዲሱ ማሻሻያ ተግባራዊ ሲደረግ ፤ የፌደራል መንግሥት ለክልል መንግሥታት የሚሰጠውን የበጀት ድጋፍና ልዩ ድጎማዎች ያደርጋል፣ ያስደርጋል። በሌላ በኩል ደግሞ በአዋጁ አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 17 መሥሪያ ቤቱ የድርጅቶችን ሒሳብ ኦዲት የማድረግ ሥልጣኑንና ተግባሩን በአግባቡ ለመወጣት ተጠሪነቱ ለፌደራል ዋና ኦዲተር የሆነ ራሱን የቻለ ተቋም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚወጣ ደንብ ማቋቋም ይቻላል።
የዋና ኦዲተርና የምክትል ዋና ኦዲተር የሥራ ዘመንም ገደብ ያለነበረው ባለመሆኑ በአዲሱ ማሻሻያ አዋጅ ላይ ገደብ እንደሚጣልበት ይጠበቃል። ቀደም ሲል የዋና እና የምክትል ዋና ኦዲተሮች ሥራ ዘመን ስድስት ዓመት እንዲሆንና ከኹለት የሥራ ዘመን በላይ ማገልገል እንደማይችሉ የሚደነግግ ሕግ ቢኖርም አዋጅ ቁጥር 982/2008 ሲፀድቅ ግን እንዲወጣ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል።
ይህ ደግሞ ከተቀሰመው የዓለም ዐቀፍ ተሞክሮ ጋር የማይጣጣምና መሥሪያ ቤቱ በአዲስ ኃይል በመመራት የሚያገኘውን ጥቅም እንደሚያስቀር አወቀ ጤናው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ማሻሻያው አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቅጥጥር ቋሚ ኮሚቴ እየተመከረበት እንደሚገኝና በምልዐተ ጉባኤው እንደሚፀድቅ የፌደራል ዋና ኦዲተር አስታውቋል።
Average Rating