ሕገ ወጥ አሰሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በመርካቶ አካባቢ ምንም ፈቃድ ሳይኖራቸው፣ በርካታ ሴቶችን ወደ ውጭ አገር እንወስዳችኋለን በሚል ሰበብ በአንድ ቤት ውስጥ በማከማቸት ለዝሙት አዳሪነት ጭምር እየተጠቀሙባቸው መሆኑን አዲስ ማለዳ አረጋገጠች።
በጉዳዩ ዙሪያ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአዲስ አበባ አስተዳደር የሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አስፋው መብራቴ፣ በመርካቶ አካባቢ እንደዚህ ዓይነት ወንጀሎች እንደሚፈጸሙ መረጃዎች እንዳላቸውና ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ስብሰባም ነዋሪው ይህንን እንዳረጋገጠላቸው አምነው፣ እንዲህ ዓይነቱን ወንጀል ለማስቀረት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰሩ መሆኑንና እስካሁን ባለው ደረጃ ፍቃድ ሳይኖራቸው የሚሰሩ 1034 ኤጀንሲዎችን በመዝጋት ዘመቻ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ አስተዳደር የሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቢሮ በከተማዋ የሚገኙ ከአንድ ሺሕ የሚበልጡ ሕገወጥ አሠሪ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎችን ማገዱን ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት አስፋው፣ በአዲስ አበባ ፍቃድ ሳይኖራቸው በሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲነት ሲሰሩ መቆየታቸውንና ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጣ ግብረ ኀይል ባደረገው የተደራጀ ቁጥጥር አብዛኛው የዘርፉ ሥራ ለሕገ ወጥነት ተጋላጭ ሆኖ መቆየቱን አስታውቀዋል። በተመሳሳይ 20 መሰል ተቋማት ሐሰተኛ ማስታወቂያዎችን በመለጠፍ ሕዝብ ሲያምታቱና ሲያጭበረብሩ መቆየታቸውን የቢሮው ምክትል ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ፍቃድ ባወጡበት ቦታ አለመገኘት፣ አላግባብ ገንዘብ መቀበል፣ ሕጋዊውን የፈቃዱን መስፈርት ሳያሟሉ በሥራ ላይ መገኘት ኤጀንሲዎቹ የተገኘባቸው ችግር ሲሆን፣ አብዛኞቹም እየታሸጉ ነው ተብሏል። ለተቀጣሪ ሠራተኞች ስለ ክፍያና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ግልጽ የሆነ መረጃ አለመስጠትም ለውዝግብ ምንጭ መሆኑን ቢሮው አደረግኩት ባለው ማጣራት እንደደረሰበት ያስታወቀ ሲሆን፣ እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ሕዝቡም ሕጋዊ የሆኑትን ለይቶ እንዲጠቀም እና በሕገወጦች ላይ ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበርም ጥሪ ቀርቧል።
የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መርካቶ ፖሊስ ጣቢያ መርማሪ የሆኑት ኮማንደር ኤርሚያስ፣ እንደዚህ ዓይነት የወንጀል መዝገቦች እጃቸው ላይ መኖሩን ለአዲስ ማለዳ ገልጸው፣ ጉዳዩ በምርመራ ላይ በመሆኑ መረጃ ለመስጠት ያስቸግራል፤ ምርመራውን ጨርሰን ክስ ስንመሰርት የምናሳውቃችሁ ይሆናል ብለዋል።
Average Rating