• ዘይቱ የአደጋ ሥጋት የተደቀነበት በመሆኑ የጤና ፍተሻ ሊደረግበት ነው ተባለ
ለ10 ወራት በሞጆ ደረቅ ወደብ የተቀመጠው የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን 928 ኮንቴነር ዘይት የአደጋ ሥጋት የተደቀነበት በመሆኑ የጤና ፍተሻ ሊደረግበት ነው።
ኮሚሽኑ ከውጭ አገራት ያስገባው 928 ኮንቴነር ወይም 24 ሚልዮን 684 ሺሕ 800 ሊትር ዘይት ከሞጆ ደረቅ ወደብ ከወራት በፊት መውጣት የነበረበት ቢሆንም ላለፉት 10 ወራት በወደቡ እንደሚገኝ አዲስ ማለዳ የደረሳት መረጃ አመልክቷል።
በመንግሥት ድጎማ በንግድ ሚኒስቴር ግዢ ተፈፅሞ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ከተደረጉት የፍጆታ እቃዎች መካከል እስካሁን በሞጆ ደረቅ ወደብ ተቀምጦ የሚገኘው ከ24 ሚልየን 684 ሺሕ 800 ሊትር በላይ ዘይት በብሔራዊ የአደጋና ሥጋት አመራር ኮሚሽን ለተፈናቃዮችና እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያዊያን መዋል የነበረበት ነው።
በወደቡ ለወራት የቆየውን ዘይት ለማውጣትና ለተጠቃሚዎች ለማድረስ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ከኹለት ወራት የባንክ ሒደት በኋላ የዘይቱ የጤነኝነት ሁኔታው መመርመር አለበት፣ እንዲሁም በኮንቴነሩ ውስጥ ሌላ ነገር ሊኖረው ይችላል በሚል ምክንያት እስካሁን ከወደቡ መውጣት አልቻለም። ዘይቱ ጥቅም ላይ ቢውል የሚያደርሰው የጤና ጉዳይ መመርመር አለበት የሚለው ውሳኔ የመጣውም ዘይቱ ለወራት ባልታወቀ ምክንያት ከሞጆ ደረቅ ወደብ ማውጣት ባለመቻሉ ነው ተብሏል። ምርመራ ይደረጋል ስለመባሉ የፌዴራል የአደጋና ሥጋት አመራር ኮሚሽን የሎጀስቲክስ ኃላፊ የሆኑት ሀይደሮስ ሐሰን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የኮሚሽኑ የሎጂስቲክስ ኃላፊ ሀይደሮስ ዘይቱ ከሞጆ ሳይወጣ ሊዘገይ የቻለው የኮሚሽኑ መጋዘኖች ስለሞሉ ነው ብለዋል። ስለዚህም ሲያስረዱ “በኢትዮጵያ የተፈናቃይ ቁጥር በመጨመሩና አራት ቢሊዮን ኩንታልና ሌሎች ቁሶች መጋዝኑን ሞልተውብን ስለነበር ነው” ብለዋል። ኮሚሽኑ ዘይቱ በሞጆ ወደብ ስድስት ወር ነው የቆየው ብሎ ቢያምንም የሞጆ ደረቅ ወደብ 10 ወራት እንዳስቆጠረ በማስረዳት ኮሚሽኑ ቅጣት እንዲከፍል መደረጉን ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት ሀይደሮስ፥ ኮሚሽኑ ለአገር እየሠራ መቀጣት አልነበረበትም ሲሉም የተቋማቸውን ቅሬታ አክለዋል።
አዲስ ማለዳ ኮሚሽኑ በቀጣይስ ዘይቱን ምን ሊያደርግ አስቧል ስትል ጥያቄ ባቀረበችበት መጋቢት 9/2011፣ ሀይደሮስ “ከወደቡ ለማስነሳት በዛሬው ዕለት ልንጀምር ያሰብን የነበረ ቢሆንም የጤና ምርመራ መደረግ አለበት በመባሉ ምክንያት ምርመራው እንዳለቀ እናነሳለን” ሲሉ ተናግረዋል። ክፍተቱ ለምን ተፈጠረ ለሚለውም በኮሚሽኑና በወደብ ባለሙያዎች መካከል ያለመናበብና ግንኙነት ያለመፍጠር ችግር እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኀኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን ተቋም የሞጆ ቅርንጫፍ ደረቅ ወደብ ጤና ኳራንቲን ቡድን አስተባባሪ ወንደወሰን ኃይሉ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ለምግብነት የሚያገለግሉ ማንኛቸውም ምርቶች ምርመራ ይደረግባቸዋል። በዚህም የኮሚሽኑን ዘይት ናሙና አዲስ አበባ ለሚገኘው ብሌስ ላቦራቶሪ አግሮ ቢዝነስ መላኩንም አስረድተዋል።
ውጤቱም ከሦስት እስከ አምስት ቀናት ሊወስድ ይችላል ያሉት አስተባባሪው ውጤቱን እየተጠባበቁ ስለመሆኑም አሳውቀዋል።
ከሳምንት በፊት የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከተባባሪዎቹ የዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ጋር በሰጠው መግለጫ በኢትዮጵያ በድርቅና በመፈናቀል ምክንያት ስምንት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የሰብኣዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ማለቱ ይታወሳል። ለዚህም አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል። ለዚህም የተለያዩ አካላትን ድጋፍ የተጠየቀው ኮሚሽን በርካታ መጠን ያለውን ዘይት ለወራት በደረቅ ወደብ አከማችቶ መገኘቱ ሌላ ጥያቄን አስነስቷል።
ከውጭ አገር የሚገቡ እቃዎችን በቶሎ ያለማንሳት ችግርን በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ሱሌይማን ደደፎ ካሁን ቀደም በስፋት ሲያጋልጡ እንደነበር ይታወቃል፡፡
Average Rating